የኢትዮጵያ የስንዴ ኤክስፖርት ዜና አዲስ የማጥላላት ዘመቻ አስነሳባት

በሶማሌ ክልል አንድ ዞን ብቻ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ይጠበቃል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሞኑ “ኢትዮጵያ ከውጭ ሀገር ስንዴ ገዝታ ልታስገባ ነው” በሚል በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የተሰራጩ ዘገባዎችን አስተባበሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ‘ኢትዮጵያ በድርቅ ልትመታ ነው’ በሚል የሚሰማው ዜና፤ ሀገሪቱ “ስንዴ ለውጭ ገበያ አቀርባለሁ” በማለቷ የተከፈተባት “የማጥላላት ዘመቻ አካል ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት መንግስታቸው ሲያካሄደው የቆየውን የዘንድሮውን “የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር” መጠናቀቅ በማስመልከት ዛሬ እሁድ ነሐሴ 8፤ 2014 በድሬዳዋ ከተማ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ነው። አብይ በዚሁ ንግግራቸው “ኢትዮጵያን ድርቅ ያጠቃታል” እንደሚለው ዘገባ ሁሉ “ኢትዮጵያ ስንዴ ገዝታ፤ ስንዴዋ በጀልባ ተጭኗል” የሚል ዜና ከሰሞኑ መሰማቱን ጠቅሰዋል።

“ኢትዮጵያ ስንዴም አልገዛችም፤ ድርቅም አይመታትም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከእነዚህ ዘገባዎች ጀርባ ያሉት ኃይሎች ዋና ዓላማቸው ችግር መናገር የሆነ “ሟርተኞች” ናቸው ሲሉ ተችተዋል። “ዋናው የድርቅ እና የስንዴው ዓላማ፤ ስንዴ ኤክስፖርት እናደርጋለን ስላልን፤ ቀድሞ የማጥላላት ዘመቻ አካል ነው። ‘ስንዴ ኤክስፖርት እናደርጋለን እያሉ ስንዴ ያስገባሉ’፤ ስንዴ ኤክስፖርት እናደርጋለን እያሉ በድርቅ ተመቱ’ ለማለት እንዲያመቻቸው ነው” ሲሉም ከዘገባዎቹ ጀርባ አለ ያሉትን የተደበቀ አጀንዳ ጠቁመዋል።

ከትላንት በስቲያ አርብ ከኦዴሳ አጠገብ በሚገኝ የዩክሬን ወደብ መልህቋን የጣለች አንድ መርከብ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓጓዝ ስንዴ መጫን መጀመሯን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበው ነበር። የዩክሬንን የመሰረተ ልማት ሚኒስቴርን የጠቀሰው የአሶሴትድ ፕሬስ ዘገባ፤ መርከቧ የምታጓጉዘው ስንዴ 23 ሺህ ሜትሪክ ቶን ገደማ እንደሆነ አመልክቷል።

ከሩሲያ ጋር በገባችበት ጦርነት እየታመሰች ካለችው ዩክሬን የእህል ምርት ማጓጓዝ የተጀመረው፤ በጦርነቱ ምክንያት በዓለም የተከሰተውን የምግብ እጥረት ለማቃለል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በቱርክ አደራዳሪነት ሁለቱ ተፋላሚ ሀገራት በደረሱበት ስምምነት መሰረት ነው። የዩክሬን የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ኦሌክሳንደር ኩብራቶቭ “ብሬቭ ኮማንደር” የተሰኘችው መርከብ 23 ሺህ ቶን ስንዴ ጭና ከፒቭዴኒ ባህር ወደብ ለመነሳት ዝግጁ መሆኗን በዛሬው ዕለት በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

መርከቧ ወደ ጅቡቲ ከተጓዘች በኋላ በድርቅ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን የሚከፋፈለውን እርዳታ በዚያ እንደምታራግፍ የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቃባይ ስቴፈን ዱጃሪች ተናግረዋል። የተመድ እርዳታውን በኢትዮጵያ ለማከፋፈል ያቀደው በዓለም የምግብ ድርጅት አማካኝነት ነው። ዜናው ከኢትዮጵያ ኢንሳይደር የተወሰደና የተጨመረበት ነው።

See also  ዐቢይ አሕመድ አዲስ ዓመትን ከሠራዊቱ ጋር ለማክበር ማይጠብሪ ግንባር ገቡ

በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን እየለማ ካለሁ የኩታ ገጠም እርሻ ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይጠበቃል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን እየለማ ካለሁ የኩታ ገጠም እርሻ ከ8 ሚልየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ በሶማሌ ክልል በፋፈን ዞን ከ127ሺህ ሄክታር የሚበልጥ ኩታ ገጠም እርሻን የጎበኙ ሲሆን ከዚህም ከ8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያስገኝ ይጠበቃል ብለዋል።

ይህ ቀደም ሲል ተዘንግተው የቆዩ ስፍራዎች ወደ ምርታማነት የመለወጣቸው ማሳያ ነው ያሉ ሲሆን እነዚህ ጥረቶች ሊጠናከሩና ሊስፋፉ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም አስተሳሰባችን እና ተግባሮቻችን ሙሉ በሙሉ በምርታማነት እና ልማት ላይ ማተኮር አለባቸው ማለታቸውን ከማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

(ኢዜአ)

Leave a Reply