«ከህወሓት ጋር ለሚያደርገው ውይይት የቦታ ይገባኛል ጥያቄ በቅድመ ሁኔታነት መቅረብ አይችልም»

በሃሚድ አወል

የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር ለሚያደርገው የሰላም ውይይት “የቦታ ይገባኛል ጥያቄዎች” በቅድመ ሁኔታነት መቅረብ እንደማይችሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። በወልቃይት፣ ጠገዴ እና በሁመራ አካባቢ ያለው ጉዳይ “በምክክር ኮሚሽኑ የሚፈታ” እንደሚሆንም አገልግሎቱ ገልጿል።

ይህ የተገለጸው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 14፤ 2014 በሰጡት መግለጫ ላይ ነው። ዶ/ር ለገሰ በዚሁ መግለጫቸው፤ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት፣ የደቡብ ክልል የአደረጃጀት ጥያቄዎች እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር ወሰን ማካለል ጉዳዮችን ዳስሰዋል።

አንድ ሰዓት ገደማ ከፈጀው በዚህ መግለጫ አብዛኛውን ጊዜ የወሰደው ግን የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እና እሱን ለመፍታት ይደረጋል የተባለው የሰላም ውይይት ነው። የሰላም ውይይቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መደረስ እንዳለበት የገለጹት ዶ/ር ለገሰ፤ ይህንኑ ስምምነት ተከትሎ ከሚደረገው “ጥልቀት ያለው ፖለቲካዊ ውይይት” በኋላ የይገባኛል ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚያገኙ አክለዋል።

“አወዛጋቢ የሆኑ የይገባኛል የሚሉ ጉዳዮች ስላሉ እነዚህ የይገባኛል እና ሌሎች ከዚህ ጋር የሚያያዙ ብሔራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጉዳዮች በምክክር ኮሚሽኑ አማካኝነት የሚፈቱ ይሆናል። በወልቃይት እና ጠገዴ፣ በሁመራም አካባቢ ያለው ጉዳይ በግልጽ መንግስት አስቀምጧል። የትኛውም የይገባኛል ጥያቄ እና ይመለከተኛል የሚባሉ ጉዳዮች ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው የሚፈጸሙ ናቸው” ሲሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

“እነዚህ ጉዳዮች በምክክር ኮሚሽኑ እንደዚሁም ደግሞ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በሚያደርጓቸው ውይይቶች እና በአጠቃላይ በህዝብ የሚወሰኑ ነው የሚሆኑት” ያሉት ዶ/ር ለገሰ፤ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ “ወደ ሰላም መጥቶ ለመወያየት ቅድመ ሁኔታ መሆን አይችልም። ሊሆንም አይገባም” ሲሉ በጉዳዩ ላይ የፌደራል መንግስት አቋም ምን እንደሆነ ግልጽ አድርገዋል።

የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ነሐሴ 12፤ 2014 በሰጡት መግለጫ፤ በአወዛጋቢው የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ ላይ የፌደራል መንግስት ወቅታዊ አቋም ምን ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። አቶ ጌታቸው በትግራይ ቴሌቪዥን በተላለፈው በዚሁ መግለጫቸው፤ የምዕራብ ትግራይ ጉዳይም ሆነ የትግራይ ሉዓላዊነት በፊደራል መንግስቱ “ይረጋገጣል የሚል የዋህነት የለንም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

See also  አዲስ አበባ - ለመምህራን ይከፈል የነበረውን የቤት አበል ከብር 850 ወደ ብር 3 ሺህ እንዲሻሻል ተወሰነ

Leave a Reply