“የፌደራል አወቃቀሩ የሃገራዊ ምክክሩ አጀንዳ ሊሆን ይገባል»

አንጋፋው ፖለቲከኛና ምሁር ዶ/ር አለማየሁ አረዳ፤ የሰሞኑ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው በዘለቁት የክልሉ አደረጃጀት የወሰን አከላለል ጉዳዮች ላይ ለአዲስ አድማስ ሃሳባቸውን አጋርተዋል- የኋላ ዳራ እየተፈተሹና ታሪካዊ እውነታዎችን እያጣቀሱ።
ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛው አለማየሁ አንበሴ ጋር ሰፊ ቃለ-ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር አለማየሁ አረዳ ያልዳሰሱት ችግር የለም። ያላነሱት ክልል አይገኝም። ችግሮቻችንን ብቻ ሳይሆን መፍትሄዎችን ይጠቁማሉ። የመንግስት ባለሥልጣናትም በክልል አደረጃጀቶች ጉዳይ ላይ በጥድፊያ ከመወሰን ይልቅ ህዝብ ማወያየትና ጥናት ማድረግ ብልህነትም ተገቢ መሆኑን ይመክራሉ።


ከዶ/ር አለማየሁ አረዳ ጋር የተደረገውን ቃለ-መጠይቅ እነሆ ሃሳብ አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኝ ድልድይ ነው። በአሁኑ ወቅት በየቦታው የሚነሱ የማካለልና የክልል እንሁን ጥያቄዎች ለምን ጎልበት አሉ? በ1983 ዓ.ም የተጀመረው በዘውግ ክልሎችን የማደራጀት ያስከተለው መዘዝ ነው ማለት ይቻላል?
1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት አደረጃጀት ታሪክ ውስጥ ለየት ያለ ሁኔታ የተፈጠረበት ዘመን ነው፡፡ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ በአሃዳዊ ስርዓት ውስጥ ሃገራዊ ብሔርተኝነት የጎለበተበትና ማዕከላዊነት የጠነከረበት መንግስታዊ ሥርዓት ነው የነበረው፡፡ በወቅቱ አሃዳዊ ሥርዓት ነው ስንል ሁሉም ስልጣን ተማክሎ፣ ከማዕከል ወደየ ክፍለ ሃገሩ ትዕዛዝና መመሪያ የሚወርድበት ነበር ማለታችን ነው፡፡

የአሠብ ልዩ አስተዳደርን ጨምሮ ሁሉም ክፍለ ሃገሮች በማዕከላዊነት ተጠርንፈው የሚመሩ ነበሩ፡፡ የሃብት ክፍፍሉም ቢሆን ፍትሃዊ አልነበረም፡፡ 1983 ላይ ስንመጣ ግን ራሱ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሙ ወደ ነገዳዊ ብሔረተኝነት ተቀየረ፡፡ የወቅቱ ርዕዮተ ዓለም መነሻው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ብሔረሰቦች መብት ሳይከበር ስለኖረ አሁን መከበር አለበት የሚል ነበር። የብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደርና ሉአላዊነት መከበር አለበት የሚለው ሃሳብ ነበር በወቅቱ ጎላ ብሎ የወጣው።

በዚያም የተነሳ አወቃቀሩ ማዕከላዊ (አሃዳዊ) ከሆነ አስተዳደር ይልቅ ያልተማከለ አስተዳደር እንዲከተል የሚል አቋም በፖለቲከኞቹ ተያዘ። ነገር ግን እነዚህ ያልተማከሉ አስተዳደሮች ሲፈጠሩ ገና ህገመንግስቱም አልተረቀቀም ነበር፡፡ ዋነኛው ጉዳይ በአሃዳዊ ስርዓት ውስጥ የሃብትና የስልጣን ክፍፍሉ ፍትሃዊ አልነበረም፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት አልተከበረም፣ አስተዳደራዊ ስርዓቱ ቀልጣፋና ተደራሽነት ያለው አልነበረም፤ የልማቱን ሥራ ማሳለጥ፣ ባህልና ቋንቋን የማሳደግ የመሳሰሉ መብቶች ያልተከበሩበት ነው የሚለው ነበር መነሻ የሆነው፡፡ የፌደራል አወቃቀር ሲመጣ እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ያቃልላል ተብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት እነዚህ ችግሮች በእርግጥ ተቃለሉ ወይ? ለምሳሌ ክልሎች ተከልለው ቢመሰረቱም፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት (Autonomy) የተወራለትን ያህል ነበር ወይ? አስተዳደሩ ራሱ በሚፈለገው ደረጃ ቀልጣፋ ብቃት ያለውና ተደራሽ ነበር ወይ? ብለን ስንጠይቅ፣ የእውነት እንዳልሆነ ነው የምንገነዘበው

See also  የጁንታው ርዝራዠች ሴራ ምን ሊሆን ይችላል?

፡፡ ምክንያቱም ፌደራላዊ የተባለውን አወቃቀር ስናየው በሁለት ዘርፍ ተከፍሎ አንደኛው የኢህአዴግ የሚባሉትን አራት ክልሎች የያዘ ሲሆን፤ ያልተማከለ ነው ቢባልም ግን በህወኃት-ኢህአዴግ ፓርቲ ሥር ተማክሎ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በጠበቀ መልኩ የሚመራ ስለነበረ፣ በውስጥ አሃዳዊነት የተጠረነፈ ነበርና ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ያቃለለ የፌደራል አወቃቀር በአራቱ ክልሎች ውስጥ ነበር ማለት ያስቸግራል፡፡ የተቀሩት ክልሎች በአጋር ፓርቲዎች የሚመሩ ናቸው ቢባልም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሕወኃት ተፅዕኖ ውጪ አልነበሩምና እንደታዘዙ የሚኖሩ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡
ለምንድን ነው ሁነኛ የፌደራል አወቃቀር መፍጠር ያልተቻለው?

Addisadmass
https://bit.ly/3pAXP8a

Leave a Reply