«የሳይበር ዘመቻው ማጠንጠኛ ‘የትግራይ ዘር ማጥፋት’ የሚል የሐሰት ትርክት ነው» ጌት ፋክት

“በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የሳይበር ጦርነት ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ቀድሞ ከያዘው እቅድ ጋር የሚተሳሰር መሆኑን ባደረኩት ምርምራ አረጋግጫለሁ” ሲል ጌትፋክት የተሰኘው የሲቪክ ተቋም አስታወቀ።

የሳይበር ዘመቻው ማጠንጠኛ “የትግራይ ዘር ማጥፋት” የሚል የሐሰት ትርክት መሆኑን ጠቁሟል።

የጌትፋክት ሳይንቲስቶችና የዳታ ተንታኞች በማህበራዊ ትስስር ገጾች አማካኝነት በዓለም ላይ ሲሰራጭ የነበረው ‘የሳይበር ዘመቻ’ መነሻና አዝማሚያዎች ላይ ጥናት ማድረጋቸውን ተቋሙ አስታውቋል።

የማህበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ጦርነቱን አስመልክቶ ለሰጠው ምላሽ ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ ገልጿል።

ጌትፋክት በምርመራው ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ከወታደራዊ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት የሌላቸው አካላት ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ለመፈጸም አስቀድሞ ከያዘው እቅድ ጋር በማቀናጀት የሳይበር ዘመቻ ያካሂዱ እንደነበር የሚያሳዩ “አስደንጋጭ” መረጃዎችን ማግኘቱን አመልክቷል።

በግኝቱ መሰረት ጥቅምት 23 እና ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት 17 የትዊተር አካውንቶች መከፈታቸውንና ከተከፈቱት አካውንቶች በአንዱ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ማምሻውን የመጀመሪያው የሀሰት ክስ መረጃ መሰራጨቱን ጠቁሟል።

የጥቅምት 25ቱ የትዊተር መልዕክት “ለትግራይ ዘር ማጥፋት” ዘመቻ ማስጀመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልና ሀሳቡ ከዛ ቀን በፊት ጥቅም ላይ አለመዋሉን ነው ጌትፋክት ያስታወቀው።

ይህም የሚያሳየው የሀሰት ውንጀላው ዘመቻ በይፋ የተጀመረው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ በሚገኙ ወታደሮች ላይ ከፈጸመው አሰቃቂ ግድያ (አብዛኞቹ በተኙበት የተገደሉ ናቸው) በፊትና በኋላ መጀመሩን ነው፤ ዘመቻው የኢትዮጵያ ሃይል ለሕወሓት ጥቃት ምላሽ ከመስጠቱ በፊት ለዓለም አቀፍ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ማዕከላት ቀድሞ ተሰራጭቷል ሲል ተቋሙ ገልጿል።

በተደረገው ጠለቅ ያለ ምርመራ ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በፈጸመበት ዕለት 184 የሚጠጉ ተጨማሪ የትዊተር አካውንቶች እንዲሁም በአጠቃላይ 201 የሚሆኑ የትዊተር አካውንቶች በተመሳሳይ ቀን መከፈታቸውን አመልክቷል።

የጥቃቱ ዕለት የተከፈቱት የትዊተር አካውንቶች ብዛት የሀሰት ትርክቱን ለማጉላት በአንድ ቀን ብዙ አካውንቶች የተከፈቱበት መሆኑን አስታውቋል።

See also  ጻድቃን - በትግራይ የሽግግር መንግስት ለመመስረት የተቋቋመውን ኮሚቴ አወገዙ

ከሰሜን ዕዝ ጥቃት ማግስት 156 አዲስ የትዊተር አካውንቶች ተከፍተው 357 ትዊቶች የዘመቻው ማጠንጠኛ የሆነውን የሀሰት ትርክት በትዊተር ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ መሰራጨታቸውን ገልጿል።

ከጥቅምት 25 እስከ ሕዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም 1 ሺህ 633 የሚሆኑ አዲስ አካውንቶች መከፈታቸውንና በተጠቀሰው ጊዜ ዘመቻውን የተመለከቱ 75 ሺህ 581 መልዕክቶች ትዊት መደረጋቸውን አመልክቷል። (ይሄ ቁጥር ማጋራቶች፣ ምላሾችና መውደዶችን አያካትትም)
ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ በየቀኑ የሚከፈቱ አዲስ የትዊተር አካውንቶች ቁጥር በ80 ከመቶ ቢቀንስም በማህበራዊ ትስስር ገጹ የሚደረጉ ዳግም ማጋራቶች (ሪትዊትስ) ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

ይሁንና ጥቅምት 23 እና 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተከፈቱ የትዊተር አካውንቶች በተከታታይ ወራት የዘመቻው ሀሳብ እንዲስፋፋ ምክንያት መሆናቸውን ነው ጌትፋክት በምርምራ ግኝቱ ላይ የገለጸው።

የትዊተር ዳግም ማጋራት በከፍተኛ ፍጥነት በጨመረበት ወቅት በትግራይ ክልል በጥቅምት 25 እና ሕዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም መካከል በክልሉ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት(ኢንተርኔት ወይም ስልክ) አልነበረም” ብሏል።

በዚህ ሁኔታ የሀሰት ትርክቱ መረጃ ማነው የአይን እማኙ? ማንስ ነበር መረጃውን ለዓለም ሲሰጥ የነበረው? የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ያስነሳል ሲል ነው ጌትፋክት ያመለከተው።

ጌትፋክት ዘመቻውን አስመልክቶ የተከፈቱ የትዊተር አካውንቶች በጥልቀት በፈተሸበት ወቅት የዘመቻው የመጀመሪያ ሁለት ወራት የትዊተር መልዕክቶች ከፍተኛ ድርሻ የሚይዙት ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አመልክቷል።

ሜልቦርን (አውስትራሊያ)፣ ኮሎራዶ(አሜሪካ)፣ ኢንሺዴ(ኔዘርላንድስ) እና ኢስሊንግተን (ለንደን) መልዕክቶቹ ሲተላለፉባቸው ከነበሩት መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጿል።

እ.አ.አ በ2021 ጥር እና የካቲት ወራት መካከል በየቀኑ ዘመቻውን የተመለከቱ 50 ሺህ መልዕክቶች በትዊተር ገጽ ላይ በድጋሚ ማሰራጨት ሲሰራጩ ነበር።

በወቅቱ በታንዛንያና ኬንያ የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የትዊተር ተከታይ ያላቸው የውጭ አገር ዜጎች ዘመቻውን የተመለከቱ መልዕክቶች (ሀሽታጎች) በትዊተር ሲያሰራጩ (ትዊት ሲያድርጉ) እንደነበርና ይሄም ዓለም አቀፍ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ድምጽ እንዲያገኝ አድርጎታል ነው ያለው ጌትፋክት።

ዘመቻው ጥቅምት 23 እና 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽቶች ማለትም ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በፈጸመበት፣ የኤሌትሪክ ሃይል በተቋረጠበትና ሰራዊቱ ለደረሰበት ጥቃት ምላሽ ከመስጠቱ በፊት የተጀመረ ነው።

See also  አሚና መሐመድ - አገራዊ ንግግሩን አጎሉ፤ ዕርዕስ ዋጋው ስንት ነው?

ይህም ከወታደራዊ ጉዳዮች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ አካላት የሳይበር ጥቃትን ሲያስተባበሩና ሲመሩ እንደነበር በግልጽ ያሳያል ሲል ጌት ፋክት ገልጿል።

ዘመቻው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳትና ሕዝብ ሕወሓት ከፈጸመው የኃይል ጥቃት ላይ ትኩረት እንዳያደርግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክቷል።

“እነዚህ በማስረጃ የተረጋገጡ ግኝቶች የዘር ማጥፋቶችና ግጭቶች መከላከል ስራ ያሳስበናል ለሚሉ ወገኖች የማንቂያ ደወሎች ናቸው፤ ድርጅቱ የትዊተር አካውንቶቹ ሆን ተብሎ፣ ቀድሞ ታስቦበት እና በተደራጀ መልኩ ለዘመቻው መዋላቸውን በማስረጃ አረጋግጧል።

ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች እና ፖሊሲ አውጪዎች ግጭቶችን በማባባስ ንጹሃን ዜጎች እንዲሞቱና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነውን ሐሰተኛ መረጃዎችን በመገናኛ ብዙሃን አማራጮች በማሰራጨት ለፍርሃትና ጥላቻ ትርክቶች የማዋል ድርጊት ለመቆጣጠር ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ጌትፋክት ጥሪ አቅርቧል።

ጌትፋክት ለአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ኢትዮጵያን አስመልክቶ እውነት ላይ የተመሰረተ መረጃዎችን በመስጠት በአሜሪካና የተቀረው ዓለም በአገሪቷ ጉዳይ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ የኢትዮጵያን ዜጎች ድምጽ እንዲሰሙ፣ የኢትዮጵያን ሉዓዊንት እንዲያከብሩ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጥረቶች የመደገፍ ተልዕኮ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

(ኢዜአ)

Leave a Reply