ትህነግ “የዘርፍከውን መልስ ተብሏል”- “አልዘረፍኩም ሳበድር የከረምኩት ነው” ብሏል

መቐለ ከተማ ከሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) መጋዘን ” … የትግራይ ኃይሎች መቐለ በሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን በኃይል በመግባት 12 የነዳጅ ታንከር 570,000 ሊትር ነዳጅ ዘርፈዋል ” ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ አሜሪካ “የተሰረቀው ነዳጅ ጉዳይ አሳሰበኝ” ስትል ሩሲያ በቀጥታ አውግዛለች። ራሱ ድርጅቱ ዕርዳታ ማከፋፈል ሲቆም የሚደርሰው አደጋ የከፋ መሆኑንን በማመለከት ” ነዳጄን መልሱ” ብሏል። ትህነግ በበኩሉ ያበደርኩትን ነው የወሰድኩት ብሏል።

የአለም ምግብ ፕሮግራም ዝርፊያውን ካወገዘ በሁዋላ በትህነግ የተዘረፈበት 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ እንዲመለስለት የጠየቀው ካልተመለሰ የሰብአዊ ድጋፍ ለማከናወን እንደሚፈተን አጥብቆ በማስጠንቀቅ ነው።

ዋና ዳይሬክተሩ ዴቪድ ባስሊ ለሰብአዊ ድጋፍ አገልግሎት ለማዋል በመቀሌ የተቋሙ መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የነበረውንና በትህነግ ታጣቂዎች የተዘረፈውን ነዳጅ አስመልክቶ መግለጫ አሰራጭተዋል።

በመግለጫቸው በዝርፊያው ሳቢያ ምግብ፣የአፈር ማዳበሪያ፣ መድሃኒትና አስቸኳይ የዕርዳታ ቁሳቁሶችን ለማሰራጨት እንደማይችል፣ ጀነሬተሮችንም ማስነሳት እንደሚሳነው ዘርዝረዋል።

መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ ሲል አሳልፎት የነበረው የተኩስ ማቆም ውሳኔ ባለፉት ወራት በትግራይ ክልል አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

በድርጅቱ የመቀሌ መጋዘን በቅርቡ ከማዕከል የተጓጓዙ ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ የያዙ አስራሁለት ታንከሮችን የተዘረፉት ረቡዕ ማለዳ ነው። የታጠቁ ሃይሎች በሃይል ገብተው ዘረፋውን እንዳካሄዱ ተረጋግጧል። አሜሪካ የነዳጅ ዝርፊያውን “አሳሰበኝ” ስትል ሩሲያ ኮንናለች። ድርጊቱ ተቀባይነት እንደሌለው በይፋ አስታውቃለች።

በትግራይ ክልል 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ  ዜጎች ለከፋ አደጋ እንደሚጋለጡ ያመለከቱት የዓለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዘረፋውን የፈጸመው ትህነግ ነዳጁን እንዲመልስ ምክንያት አስቀምጠው አስጠንቅቀዋል።

See also  "የእሳት ፖለቲካ" - አዲስ አበባን እየበላ ነው

ትህነግ “ዘርፈሃል” ከተባለ በሁዋላ ባወጣው መግለጫ ያበደረውን መውሰዱ “ሌባ” እንደማያሰኘው አመልክቶ ነዳጁን የወሰደው ለማህበረሰብ አገልግሎት እንደሆነ ዘርዝሯል። ለዓለም ምግብ ፕሮግራም ከስድስት መቶ ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ አበድረው እንደነበርም አመልክተዋል።

ትህነግ ለህዝብ አገልግሎት ሲል ነዳጁን መውሰዱን ቢገልጽም መንግስት ግን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አማካይነት ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው ሰብዓዊ ዕርዳታ ለታለመለት ዓላማ እየዋለ ስለመሆኑ ማስተማመኛ ይሰጠኝ ሲል ጥያቄውን አስፍቶ አቅርቧል። ትህነግ ነዳጁን የዘረፈውም ለጀመረው ጦርነት ዝግጅትና ማከናወኛ እንደሆነ አመልክቷል።

በቆቦና በአካባቢው ለከፈቱት ጥቃት ማስፈጸሚያ እንዲሆን ነዳጁን መዘረፉ ብቻ ሳይሆን ዝርፊያውን ለማስቆም የሞከሩ የሰብዓዊ እርዳታ ባለሙያዎችን አስሮ እንደነበር ሪፖርት እንደደረሰው ጠቅሶ  የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በመግለጫው ይፋ አድርጓል።

ትህነግ በመግለጫው ለትግራይ ዕርዳታ ፈላጊዎች የሚሆን ነዳጅ ለዓለም ምግብ ድርጅት ማበደራቸውን ድርጅቱም እንደሚመለስ ስምምነት እንደነበር አመልክቷል። በዚህም ምክንያት ሌባ ሊባል እንደማይችል ሞግቷል።

መከላከያ ትግራይን ለቆ ሲወጣ የነበረ ክምችት፣ መንግስት ለዕርዳታ በሚል ከሚልከውና በወረራው ንግስት ወቅት ትህነግ ዘርፎ ወደ ትግራይ ያዘዋወረው፣ እንዲሁም ልክ መሳሪያ በተለያዩ ሰዋራ ቦታዎች እንደሚቀበረው ሁሉ ነዳጅም በተመሳሳይ ከመሬት በታች ለረዥም ጊዜያት ይከማች እንደነበር፣ ከሁሉም በላይ የገሪቱ ትልቁ የነዳጅ ዲፖ የሚገኘው እዛ ስለሆነ ዕርዳታ ለማዳረስ ትህነግ የሚያቀርበውን የነዳጅ ጥያቄ መንግስት ሳይቀበል መቅረቱ ይታወሳል። ይህን የሚያውቀው የዓለም የምግብ ድርጅትም ሆነ ሌሎች ድርጅቶች መንግስትን ከመኮነን ውጭ በትግራይ ያለውን ነዳጅ ስለመጠቀም በይፋ ተናግረው አያውቁም።

የዘርፊያው ዜና ይፋ መሆኑን ተከትሎ ትህነግ 600 ሺህ ሊትር ነዳጅ ማበደሩን ይፋ ማድረጉ “አከማችቷል” በሚል የሚቀርበበትንና ሲያስተባብል የነበረውን ጉዳይ ባደባባይ ቅጥፈት እንደሆነ የሚያጋልጥ መሆኑ እየተነገረ ነው።

ዜናውና የትህነግ መልስ በነዳጅ ችግር ምክንያት እርዳታ ማከፋፈል አልተቻለም በሚል የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርና የትህነግ አባል ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ሲያቀርቡ የነበረውን ስሞታም የሚያቆሽሽ እንደሆነ ተያያዞ እየተጠቆመ ነው።

አሜሪካ ትህነግ ምንም ሲፈጽም “አሳስቦኛል” ከማለት ውጭ ሌላ ቃል መተቀም ስለማትወድ “ የነዳጅ መዘረፍ ጉዳይ አሳስቦኛል” ስትል መግለጫ አውጥታለች። ሩሲያ በበኩሏ ድርጊቱን ሙሉ በሙሉ ተቃውማለች።

See also  የአፍሪካና የአውሮፓ ህብረት ሀገራት አሸባሪው ትህነግ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ተጠየቀ -"ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የፈጸመው ወንጀል ይጣራ"

ትህነግ በዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ የነበረ 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉ አስነዋሪና ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን መናገራቸውን ኢዜአ አስታውቋል።

በመቀሌ በሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ የነበረ 12 ታንከር ወይም 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ በህወሃት መዘረፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ መግለጻቸው ይታወቃል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሌይ ህወሃት የዘረፈውን ነዳጅ በአፋጣኝ እንዲመልስ የጠየቁ ሲሆን፤ በነዳጁ መዘረፍ ምክንያት የሰብዓዊ ርዳታዎችን ለማሳለጥ እንቸገራለን ብለዋል።

በዚህ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን፤ በመጋዘኑ ውስጥ የነበረው የምግብና የነዳጅ ክምችት በአስችጋሪ ሁኔታ ለነበሩ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል እንደነበር ጠቅሰዋል።

በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግር ሰለባ ለሆኑ የትግራይ ማህበረሰብ መድረስ የነበረበት እርዳታ በሽብር ቡድኑ መዘረፉ ተቀባይነት የሌለውና አስነዋሪ ተግባር ነው ብለዋል።

ዘራፊዎቹ ነውረኛ ድረጊታቸውን ክደው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የትግራይ ህዝብ ለችግር ተዳርጓል የሚል የተለመደ ልፈፋቸውን እንደሚቀጥሉና የህዝብ ተቆርቋሪ ለመምሰል እንደሚሞክሩም ነው የገለጹት። በትህነግ የሽብር ቡድን የተፈጸመውን ዝርፊያ የትኛውም የዓለም ማህበረሰብ የማይደግፈው ድርጊት ነው ብለዋል።

የተፈጸመውን ድርጊት ማውገዝ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ አንዳንድ ድርጊቱን በዝምታ የሚያልፉ አካላትም እውነታው በገሃድ መውጣቱ እንደማይቀር ማወቅ አለባቸው ማለታቸውን የኢዜአ መረጃ ያስረዳል።

“አብረው ሲሰሩ ነበር ምን አጣላቸው” ሲሉ የጠየቁም እጅግ በርካታ ናቸው። መንግስት ድርጊቱን “የጦር ወንጀል ነው” በሚል በትግራይ ዕርዳታ ለሌላ ተግባር ስለሚውል ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል። በተጨማሪም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አማካይነት ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው ሰብዓዊ ዕርዳታ ለታለመለት ዓላማ እየዋለ ስለመሆኑ ማስተማመኛ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል።

Leave a Reply