ለሁሉም ትግራዋይና የትግራይ ተቆርቋሪ

ሰብኣዊ እርዳታ ያለምንም መደነቃቀፍ እንዲገባ፣ ለተደራሽነቱም የሚያስፈልግ በቂ ነዳጅ ወደ ትግራይ እንዲገባ በተደረገበት፣ መንግስት ለሰላምና ውይይት ያለምንም ቅድመሁኔታ ዝግጁነቱን ባረጋገጠበት፣ የመንግስት አገልግሎት ለመጀመር እንወያይ በተባለበት ቅፅበት፣ ህወሓት የትኛውን የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ነው ጦርነት የከፈተው? የሚሉ ጥያቄዎችን በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል፡፡

ሁሉም ትግራዋይ ሊያውቀው የሚገባ ቁም-ነገር፣ ኣሁንም ቢሆን የትግራይን ጉዳይ በዘላቂነትና ህዝብን በሚጠቅም መልኩ እልባት ማግኘት የሚችለው፣በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው!!

በበኩሌ እንደ አንድ ትግራዋይ፣ በተይ ደግሞ ፊደል እንደቆጠረ ግለሰብ፣ ህዝቤ ሰላም፣ ልማትና ዕድገት እንዲያገኝ ለማሰብና ሀሳቤን እውን ለማድረግ ጠንክሬ ለመስራት የማንንም ፍቃድ አያስፈልገኝም፡፡ ስለ ህዝቤ፣ በተለይ ደግሞ የሀገሩን ተስፋና የህዝቡ መሪ መሆን የሚችለውን ወጣቱ ትውልድ፣ ለተወሰኑ የፖለቲካ ኪሳራ ላጋጠማቸውና ዕድሜያቸውን ለጨረሱ ግለሰቦች መንበረ-ስልጣን ለማራዘም ሲባል፣ ወደተከታታይና ትርጉም የለሽ ጦርነት እየማገዱ ሲቀጥፉት ከማየት በላይ የሚያስጨንቅ እና የሚያሳዝን ጉዳይ የለም፡፡

ለሁሉም ትግራዋይና የትግራይ ተቆርቋሪ፣ እነሱ የሚሰጡትንና የሚሉትን የተሳሳተ አጀንዳ ወደጎን በመተው፣ ኣጀንዳህ ህዝብ ይኹን፡፡ በማስከተል፣ ብቻችሁን ስለህዝባችን መወሰን ይብቃችሁ፣ ወጣቶቻችን ለልማትና ዕድገት እንፈልጋቸዋለን፣ ትርጉም በሌለው ጦርነት ገብተው እንደቅጠል እንዲረግፉ አንፈቅድም! የሚል ፅኑ አቋም ሊኖርህ ይገባል፡፡

ከሰላም አማራጭ ውጪ የሚኖረውን ማንኛውም አማራጭ፣ የተረፈንን ህይወት፣ ኣካልና ንብረት የሚያሳጣን፣ ካለፈው ጦርነት በባሰ ከፍ ወዳለ ኪሳራ የሚጥለን ነው፡፡ የጦርነት አማራጭ፣ ህዝብችን ሊያገኛቸው የሚገቡ የመንግስት አገልግሎቶች በፍጥነት ምላሽ እንዳያገኙ፣ ተጀምረው የነበሩ የሰብአዊ እርዳታዎች ያለመደነቃቀፍ በፍጥነት እንዳይዳረሱ ከማድረግ አልፎ፣ የህዝባችን ችግር ባጠረ ጊዜ መፍትሔ እንዳያገኝ የሚያደርግ ነው፡፡

ያለ ጦርነትና ተጨማሪ መስዋእትነት ልዩነቶቻችንን በመወያየትና በመነጋገር፣ በሰለጠነ መንገድ ወደ ጠረጴዛ ዙርያ በማምጣት መፍታት እየተቻለ፣ በምን መለክያ የሰው ህወት የሚበላና የህዝብ ስቃይ የሚያራዝም አማራጭ መውሰድ ይቻላል?

እስኪ ሁላችን የትግራይ ጉዳይ ይመለከተናል የምንል ተጋሩ የሚቀጥሉት ጥያቄዎችን መልስ እንስጥባቸው፡፡
➢ ከትግራይ ህዝብ ፍላጎትና ምኞት ውጪ፣ ህወሓት ለምን የጦርነት መንገድን መረጠ? “ጅራፍ ራሱ መቶ ራሱ ይጮሃል” እንዲሉ! ለምንስ ራሳቸው ጥቃት ከፍተው ጥቃት ተከፈተብን የሚል ያረጀ ያፈጀ የማደናገርያ ስልታቸውን አቀረቡ?
➢ የፌደራል መንግስት “ጦርነት ኣይጠቅምም፣ እንደማይጠቅምም ደጋግመን አይተነዋል፣ ሰላማዊ መንገድ ይሻላል” ባለበት ወቅት ህወሓት ይህን ውድቅ በማድረግ ጦርነት ለምን መረጠ?

See also  አቶ አንዱአለም አራጌ የሚኮንነው የትኛውን ፕ/ር ብርሀኑ ነው?

➢ ሰብኣዊ እርዳታ ያለምንም መደነቃቀፍ እንዲገባ፣ ለተደራሽነቱም የሚያስፈልግ በቂ ነዳጅ ወደ ትግራይ እንዲገባ በተደረገበት፣ መንግስት ለሰላምና ውይይት ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ዝግጁነቱን ባረጋገጠበት፣ የመንግስት አገልግሎት ለመጀመር እንወያይ በተባለበት ቅፅበት፣ ህወሓት የትኛውን የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ነው ጦርነት የከፈተው? የሚሉ ጥያቄዎችን በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ የምንረዳው፣ የህወሓት ቡድን ስለህዝቡ ምንም ደንታ የሌለው፣ ጥያቄው ስለህዝብ ሳይሆን ስለግልና የቡድን ጥቅምና ፍላጎቶች ብቻ የሚያስብ፣ በዛ ልክ የሚንቀሳቀስና በትግራይ ወጣቶች ህይወት እድሜውን ለማራዘም የሚባዝን ፀረ-ህዝብ የሆነ ኃይል ነው፡፡

ስለኾነም ሁሉም ትግራዋይ እና የትግራይ ወዳጆች፣ ይህ ጥሬ ሀቅ ተረድተን፣ ህወሓት የጀመረውን ጦርነት በአስቸኳይ አቁሞ ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲመጣ ጫና እንድንፈጥር ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ፣ ምሁራን፣ ዲያስፖራ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት መሪዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች በሙሉ መዝሙራችሁ የሰላም መዝሙር እንዲሆንና ጦርነት ቆሞ በመንግስት የቀረበውን የሰላምና የውይይት ሐሳብ እውን እንዲሆን የምትችሉትን ሁሉ ጫና እንድታደርጉ በድጋሜ ጥሪዬን አቅርባለሁ፡፡

ዶር አብርሃም በላይ የኢፌዱሪ የመከላክያ ሚኒስትር
ዶክተር አብርሃም በላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር

Leave a Reply