ጃን ሞስኮቭ ቤተ-መጽሃፍት – ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

⁽⁽ ማንበብ ሙሉ ሰዉ ያደርጋል የሚል አንድ የቆዬ አባባል አለ። በርግጥም ማንበብ ሙሉ ሰዉ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሀገርና ሙሉ ተስፋ እንዲኖረን በማድረግ የተሻለ ትዉልድ እንዲፈጠር ያደርጋል።
ነገር ግን ኢትዮጵያኖች ብሎም አፍሪካኖች የማንበብ ባህላችን ገና ያልዳበረና “አፍሪካዊያን እንዳያዉቁት የምትፈልገዉን ሚስጥር መጽሐፍ ዉስጥ ደብቀዉ” ተብሎ እስከሚሳለቅብን ድረስ ኋላ ቀር እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም።

ይሄ ብቻ አይደለም አፍሪካዊያን ምሁራን ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ ስለማያነቡ ተመልሰው ወደ መሃይምነት ይቀየራሉ በሚል ገፋ ያለ ትችት ውስጥ ወድቀናል፡፡
እውነት ነው ፥ ተማሪዎች ፈተና እንደጨረሱ ለፈተና የተዘጋጁበትን ሞጁል ሲያቃጥሉ፣ ሲቀዱ ይስተዋላሉ፡፡ ከምረቃ በኋላም ትችት ቢሰነዘርም ለትችቱ መነሻው ይሄ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

ነገር ግን ዲግሪ ለተወሰነ የትምህርት ስልጠና ዘርፍ የሚሰጥ ማስረጃ እንደመሆኑ መጠን ምሁራንም ሆኑ ማንኛውም ሰው ማንበብ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ተምሮ ከማያነብ ሰነፍ ይልቅ ባለመማሩ የማያነብ መሐይም የተሻለ ተስፋ አለዉና።

ሰላም ጤና ይስጥልን ውድ የናይል አንባብያን በዚህ ርዕስ ዙሪያ የተሽረከርነው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በየጊዜው በባሕር ዳር ከተማ ከሚፈጥራቸው ጸጋዎች ውስጥ አንዱን ልናስተዋውቃችሁ በመውደዳችን ነው፡፡ ለዛሬው ስለ ጃን ሞስኪቭ ቤተ-መጽሃፍት ልንነግራችሁ ፈቅደናል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የንባብ አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ለመስጠት በዉቧ ከተማ ባሕር ዳር እምብርት ላይ ባለ ግርማ ሞገስ ህንፃ ከተንጣለለ ግቢ ጋር አስደናቂ ቤተ-መፃህፍት በመገንባት ለዩኒቨርሲቲዉና ለአካባቢዉ ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በፈረንጆች አቆጣጠር በ1959 የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪ የነበሩት ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ (ቀ.ኃ.ሥ.) (ጃንሆይ) በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ጉብኝት አካሂደዉ ነበር፡፡ ከሞስኮ አቻቸዉ ከኒኪታ ክሩሽቸቬ ጋር ባደረጉት ዉይይት ሶቪየት ህብረት ኢትዮጵያን በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሚቻልበት ስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡

በዚህም መሰረት ሶቪየት ህብረት አንድ የቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት ለኢትዮጵያ ለመገንባት ወሰነች፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ትምህርት ቤት በፈረንጆች አቆጣጠር ታህሳስ 30/1961 በባሕር ዳር እንዲገነባ የመሰረት ድንጋይ በንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ተጣለ፡፡

See also  በአባቷ የቀብር ስነስርዓት ላይ ለጓደኛዉ የታገቢኛለሽ ወይ? ጥያቄ ያቀረበዉ ግለሰብ አነጋጋሪ ሆኗል

ትምህርት ቤቱም በ18 ወራት ተገንብቶ በፈረንጆች አቆጣጠር ሰኔ 11/1963 አጼ ኃይለስላሴ በተገኙበት የፖሊቴክኒክ ትምህርት ቤቱ ተመርቆ ስራ ጀመረ፡፡ በሶቪየት ህብረት እርዳታ የተሰራ በመሆኑ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ትምህርት ቤቱን የሞስኮቭ ትምህርት ቤት እያሉ ይጠሩት ነበር፡፡

ትምህርት ቤቱ በ1992 ዓ.ም ከፔዳጎጂ ኮሌጅ ጋር በመሆን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ፈጠሩ፡፡ በዚህም የድሮዉ የፖሊቴክኒክ ትምህርት ቤት የቴክኖሎጂ ተቋም የሚል መጠሪያን አገኘ፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ተቋም ቤተ-መፃህፍትም አመሰራረት ከፖሊ ቴክኒክ ትምህርት ቤቱ ጋር የተያያዘ ነዉ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ተቋሙ ለዘመኑ መጣኝ ፣ ግዙፍ እና ዘመናዊ ቤተ-መፃህፍት አስገንብቶ ለተጠቃሚዎች አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን የዚህ ግዙፍ ቤተ-መፃህፍት ስያሜም ሁለት ስሞችን በማዋሀድ የተፈጠረ ነዉ፡፡

እነዚህም ተቋሙ እንዲሰራ ያደረጉትን የወቅቱ የሀገሪቱ መሪ ስም አጼ ኃይለስላሴ (ጃንሆይ) እና ተቋሙ በአካባቢዉ ማህበረሰብ ይጠራበት የነበረዉን የድሮ ስም ሞስኮቭ ትምህርት ቤት በማዋሀድ ለማስታወሻነት ይሆን ዘንድ “ጃን ሞስኮቭ” ላይበራሪ በማለት መጠሪያ ስሙ እንዲሆን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተወስኗል፡፡

ጃን ሞስኮቭ ቤተ-መፃህፍት በአሁኑ ሰዓት የተቋሙ የዲጂታል ቤተ መፃህፍትን ጨምሮ በመያዝ የተሟላ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለተጠቃሚዎች እየሰጠ ሲሆን ግዙፍ እና በጠቅላላው ለዩኒቨርሲቲዉም ሆነ በተናጠል ለባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ተቋም ኩራት የሆነ ባለ አራት ወለል ህንፃ በዉስጡ እያንዳንዳቸዉ እስከ 500 ሰዎችን የሚይዙ 3 ታላላቅ አዳራሾች፣ እስከ 50 ሰዎችን የሚያዙ 5 ያህል ትንንሽ አዳራሾች ሲኖሩት በጠቅላላ ከ2000 ተጠቃሚዎች በላይ በአንድ ጊዜ ለማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ የተገነባ ነዉ፡፡

በጃን ሞስኮቭ ቤተ-መጽሃፍት በርካታ አገልግሎቶች የሚሰጡ ሲሆን ለአብነት ያህል የ24 ሰዓት የንባብ አገልግሎት፣ የዉሰት አገልግሎት፣ የማጣቀሻ አገልግሎት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ የዲጂታል አገልግሎት ወዘተ. ይጠቀሳሉ፡፡

ቤተ-መፃህፍቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች ያሉትና በዋናነት በ2 ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለ ነዉ፡፡ እነዚህም የቴክኒካል እና የቴክኒካል ያልሆኑ ክፍሎች ሲኖሩት የየራሳቸዉ አስተባባሪዎች የተመደበላቸው ናቸው፡፡

የቴክኒካል ክፍሉ የካታሎግ እና አኮዚሽን ክፍልን በዋናነት የያዘ ሲሆን የቴክኒካል ያልሆነ ክፍሉ ደግሞ የፍተሻ እና ሰርኩሌሽን ክፍልን የያዘ ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዲጂታል ቤተ-መፃህፍት የe-books አገልግሎትን እና የምርምር ፅሁፎችን በቤተ-መፃህፍቱ ሲስተም በኩል ለተጠቃሚዎች ያደርሳል፡፡

See also  የሜቴክ የቀድሞ የስራ ሀላፊዎች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላለፈባቸው

የቤተ-መፃህፍቱ ተጠቃሚዎች መብቶችን በተመለከተ በአጭሩ ለመግለፅ ያህል፦ ማንኛዉም ቋሚ እና ኮንትራት የአካዳሚክ ቅጥር መምህራን ከተመደቡበት የትምህርት ክፍል ደብዳቤ ሲያቀርቡ በቅደም ተከተላቸዉ እስከ 10 (አስር) እና 5 (አምስት) መፃህፍትን መዋስ ይችላሉ፡፡

ተማሪዎችን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲዉ በሁሉም ፕሮግራም ትምህርታቸዉን ለሚከታተሉ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ለእያንዳናዳቸዉ 5 (አምስት) የማዋሻ ፓኬቶች ይሰጣቸዋል፡፡

የቀን የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ደግሞ የ1ኛ እና 2ኛ ዓመት ተማሪዎች 2 (ሁለት) መፃህፍትን እንዲሁም የ3ኛ፣ 4ኛ እና ተመራቂ ተማሪዎች በሙሉ 4 (አራት) መፃህፍትን መዋስ ይችላሉ፡፡ በአንፃሩ በዩኒቨርሲቲዉ ተመዝግበዉ የተከታታይና የርቀት ትምህርት የሚከታተሉ የድግሪ ተማሪዎች መታወቂያቸዉን እያሳዩ የንባብ አገልግሎት ብቻ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ የአስተዳደር ሰራተኞችን በተመለከተ ቋሚ የአስተዳደር ሰራተኞች 2 (ሁለት) መፃህፍትን መዋስ ሲችሉ ኮንትራት የአስተዳደር ሰራተኞች ደግሞ ዋስ ሲያቀርቡ 2 (ሁለት) መፃህፍቶችን መዋስ ይችላሉ፡፡

በሌላ በኩል የዉጭ ተጠቃሚዎች ከአንድ ወር ላልበለጠ ጊዜ በግል ወይም በቡድን የጥናትና ምርምር ስራን ለማከናወን የድጋፍ ደብዳቤ ለሚያቀርቡ በነፃ የንባብ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የቤተ-መፃህፍት አባል ለመሆን አገልግሎት ለሚጠይቁ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወይም ድርጅቶች በቤተ መፃህፍቱ የተዘጋጀዉን ፎርም ሞልተዉና የዓመት የአገልግሎት ክፍያ ብር 300 (ሶስት መቶ) ብር ከፍለዉ ሲያጠናቅቁ ለተወካያቸዉ 5 (አምስት) ፓኬቶች እንዲሰጣቸዉ ተደርጎ በዉሰት አገልግሎት ደንቡ መሰረት ይስተናገዳሉ፡፡

የቤተ መፃህፍት አባል ለመሆን አገልግሎት ለሚጠይቁ ግለሰቦች የዋስትና ማረጋገጫ ሲያቀርቡና የዓመት አገልግሎት ክፍያ ብር 50 (ሀምሳ) ብር ከፍለዉ ሲያጠናቅቁ ከንባብ አገልግሎት በተጨማሪ 2 (ሁለት) ፓኬቶች እንዲሰጣቸዉ ተደርጎ በዉሰት አገልግሎት ደንቡ መሰረት ይስተናገዳሉ፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጅ ተቋም “ጃን ሞስኮቭ” ቤተ-መፃህፍት በዩኒቨርሲቲው ከሚገኙ ታላላቅ አብያተ መጻፍት ውስጥ አንዱ እንጂ ብቸኛው አይደለም፡፡

ሌሎችን በቀጣይ ህትመቶቻችን እያረፍን የምናወርብ ሲሆን ማንበብ ሙሉ ሰዉ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሀገርና ሙሉ ተስፋ እንዲኖረን በማድረግ የተሻለ ትዉልድ እንዲፈጠር ያደርጋል እንዳልነው አስቀድመን ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋልና ወደ ጃን ሞንኪቭ ብቅ ብለው መጽፍትን ይተዋወቁ፡፡ ⁾⁾


(ምንጭ: ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ሕትመት + setu birhan)

See also  በአንድ ዓመት 20 ድሮኖችን የሠራው ኢትዮጵያዊ

Leave a Reply