የቆቦ መያዝ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄ አስነስቷል። የመጀመሪያው የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር አመራሮች እንደ ወትሮው ጮቤ የረገጠ መግለጫ አለማውጣታቸው ሲሆን ሌላው ትህነግ ዜናውን ይፋ ያደረገው መንግስት ቆቦን ለቆ መውጣቱን ይፋ ካደረገ ሁለት ሰዓታት በሁዋላ መሆኑ ነው። ለጦር ሜዳ ውሎ ቅርብ የሆኑ “ተሳበ፤ ተበተነ፣ ተመታ ዝም ብሎ የጀግኖቹን ዕቅድ ማየቱና ማገዙ ይሻላል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። መከላከያ በሌላ ግንባር እየገፋ ነው።

የትህነግ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸውም ሆኑ የድርጅቱ የሳይበር ሚዲያዎች ” የኢትዮጵያ ጦር ወደ ኤርትራ ድንበር አቅንቷል። ከኤርትራ ሃይል ጋር ሆኖ ሊወጋን ነው። ዓለም ይድረስልን ወይም ያውግዝልን” የሚለውን ጥሪ ከቆቦን መያዘው በማስበለጥ መወትወታቸው ጦርነትን ለሚያውቁ ” የትልቅ ሰው ምክር ስሙ” የሚል አስተያየት እንዲሰጥ አድርጓል።

ጥይት እንደ በረዶ እየረጩ፣ ህጻናትን ከፊት አሰልፈው ወደ ውጊያ የገቡት የትህነግ ሃይሎች ቀድመው ሲንቀሳቀሱ በአየር ሃይል ተመተው ስለነበር በሌሊት ያለ የሌለ ሃይላቸውን አሰልፈው ወደ ቆቦ ማምራታቸው በዜና፣ በመግለጫና በምስል ታይቷል። መከላከያ ቆቦን ለቆ መውጣቱ ያበሳጫቸው ዜጎች ምስሉን እያሽከረከሩ ዜናውን ቢያራቡም፣ ትንሽ ቀናት ጠብቁ ሲሉ የተደመጡ ቃላቸው እውነት እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችሉ መረጃዎች እየወጡ ይመስላል።

“የቆቦ ጉዳይ ትህነግ እየከፈለ የሚያሰራቸው እነዚህን ግለሰቦች በሚፈለገው መጠን አለማስደሰቱን አለማስጮሁ ለሚገባቸው ነገ ምን እንደሚሆን ለመረዳት አይከብድም” የሚሉ “የትልቅ ሰው ምክር ስሙ በነዚህ አትወሰዱ” ይላሉ

የመጣውን ስፍር ቁጥር የሌለው ሃይል በመሳብ ካሳሳ በሁዋላ መከላከያ ከፋኖና ከአማራ ልዩ ሃይል ጋር ተናቦ በመልሶ ማጥቃት ቆቦና አካባቢዋን አስመልሷል። ይህ ብቻ አይደለም ትናንት እንዳልነው ለጊዜው ስሙ ባልተገለጸ አቅጣጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ሃይል ዘመቻ ከፍተዋል። ይህን ተከትሎ ትህነግ ሃይሉን ከቆቦ በመቀነስ ወደሳሳበት አካባቢ ሲያመላልስ አየር ሃይል እግር በግር እየተከተለ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱን የመረጃው ምንጭ አመልክተዋል።

ከሌላ አቅጣጫ ሊወጉን ነው ዓለም ያውግዝልን …

የትህነግ ደጋፊ ሚዲያዎች ሳይቀሩ የቆቦን ዜና በወጉና በሚታወቁበት የዜና አዘጋገባቸው መሰረት ያልዘገቡት ቀድመው ያወቁት ነገር እንዳለ ያጠራጥራል። መከላከያ ከጥምር ጦሩ ጋር ሆኖ በወሰደው ማጥቃት መንግስት ዝምታን ቢምረጥም ቆቦና አካባቢዋ ዳግም በመከላከያ እጅ ሆነዋል።ውጊያው ቀጥሏል።

መከላከያ ከቆቦ ለምን ወዶ እንደወጣ ወደፊት በባለሙያዎች ምክንያቱ የሚነገር ቢሆንም፣ ነገሩ የሆነው በገፍ የመጣውን ሃይል ገጥሞ መታኮስ ዘመኑን የማይመጥን፣ ከአንድ በስነልቦናው ኢትዮጵያዊ ከሆነ ሰራዊት የማይጠበቅ፣ ከታክቲክም አንጻ የማያዋጣ በመሆኑ ይህን ሃይል መሳብና መበተን ግድ እንደነበር ዜናውን የነገሩን አጠር ያለ ፍንጭ ሰጥተውናል።

የቆቦን መያዝ እጅግም ሳያጎላና ትልቅ ድል ሳያደርግ በሌላ አቅጣጫ ውጊያ ሊከፈትበት እንደሆነ ጠቅሶ “ድረሱልኝ” ያለው ትህነግ በሌላ አቅጣጫ በትክክል ምን እንደገጠመው እስካሁን ይፋ አልሆነም። እሱም አላስታወቀም። መከላከያና ፋኖ እንዲሁም የአማራ ልዩ ሃይል ከአፋር ነበልባሎች ጋር በመሆን የተቀናጀ ኦፕሬሽን ላይ መሆናቸው ታውቋል።

አቶ ጌታቸው የምስራቅ ግንባር ሃይል ከኤርትራ ሃይል ጋር እንዲቀላቀል ትዕዛዝ መሰጠቱን ጠቅሰው የጻፉት ነው

በፍልሰት ስም ከትግራይ አስቀድመው አማራ ክልል የገቡና በተለይም ቆቦ የነበሩ ከተማዋን አስቀድመው እንደወረሩ መረጃ እየወጣ ነው። በዚህ ምነሻ ይምስላል የወልደያና የደባርቅ አስተዳደርን እንደጀመሩት አማራ ክልል ውስጥ “ጸጉረ ልውጥ ተከታተሉ” የሚለው ዜና መልኩን እንዳይስት ስጋት ተፈጥሯል። ትህነግ ተስፋ ስለቆረጠ ነገሪችን በጥንቃቄ ማስኬድ፣ ተፈናቃዮችን በአግባቡ ከከተማ በማራቅ መቆጣጠር እንደሚገባ እየመከሩ ያሉም አሉ።

” ኢትዮጵያዊነት ማለት ፅናት ነው! በፅናታችን ሀገራችንን እንታደጋለን” ሲል አጭር መግለጫ ያሰራጨው የመከላከያ ሚኒስቴር ” የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠባቂ በመሆኑ ሀገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነቱን በከፍተኛ ጥንቃቄ እየፈፀመ ነው” በማለት ከወድያና ወዲህ ለሚወረወሩ ሃሜት መሳይ ትንተናዎች ማርከሻ መልዕክቱን አስተላልፎ ነበር።

መንግስት ” የሰላሙን መንገድ የረገጠው ትህነግ …” እያለ መግለጫ መደጋገሙ በርካቶችን ቢያናድድም፣ አካሄዱ ክልሎች እያወጡ ካለው መግለጫ ጋር ተዳምሮ ለሚወሰደው መራር እርምጃ ለዓለም ማህበረሰብና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት አንድበት መለጎሚያ እንደሆነ ስለ ዲፕሎማሲ የሚያውቁ እየተናገሩ ነው።

የመረጃ ምንጫችን እንዳሉት መከላከያ በተጠና ስትራቴጂ በሌላ ግንባር ወደ ትግራይ እምብርት እየሄደ እንደሆነ ገልጸዋል። ዝርዝሩን ባያብራሩም ትህነግ ቆቦ ከመግባቱ ሳያስደስተው ያስደነገጠው ይህ እንደሆነ ራሱ አምኖ ” ድረሱልን” ሲል መወትወቱ የዜናው ማረጋገጫ ሆኖ ተወስዷል።

መከላከያ የሞራልና የልዕልና ደረጃውን ገልጾ ለዜጎቹ ይህን ብሏል።

አሸባሪው ኃይል የትግራይን ወጣት እየማገደ በሕዝብ ማዕበል ማጥቃቱ እኔ እየመራሁ የማልዘርፋት ሀገር ትፍረስ እኩይ ተግባሩና ፀረ ህዝብ ባህሪው አንፃር የሚጠበቅ ነው። በተቃራኒው እኛ ግን የመላው አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵዊያን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ተቀብለን የምንፈፅም ህዝባዊና ፕሮፌሽናል ብሔራዊ ኃይል ስለሆንን መላውን ህዝባችንና የትግራይን ጨቅላ ህፃናት ከከንቱ እልቂት የመታደግ ሞራላዊና ህጋዊ ግዴታ አለብን፡፡

ህወኃት ያኔ ጥንት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ስልጣኔና የዘመነ ጦር መሳሪያ ባልነበረበት ጊዜ ጦርነትን በሰው ማዕበል ገጥመህ ማሸነፍ ወረት በነረበት ወቅት እንደሚደረገው ከግብረ-ገብ፣ ከሞራልና ህጋዊነት በእጅጉ በተጣረሰ አኳሃን ገና በሰውነታቸው ያልጠነከሩ ጨቅላና ለጋ ህፃናት ከኋላ በሃይል እየገፋ በሚገባ ሰልጥኖ እስከ አፍንጫው ከታጠቀ የመከላከያና ጥምር ኃይል ፊት እያሰለፈ የእሳት እራት አድርጎ በማስፈጀት የሞት ቀኑን ለማዘግየት ታሪክ ይቅር የማይለውን ጭካኔ በገዛ ወገኑ፤ ወገናችን የትግራይ ህዝብ ላይ እየፈፀመ ነው፡፡

ስለዚህም ሰራዊታችን በህግ የተቋቋመ፣ በህግ የሚመራና በህዝብ በተመረጠ መንግስት የሚታዘዝ ሲያለማ እደሚሞገስና እንደሚሸለም ሁሉ የተሰጠው ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮ በሚገባ ሳይፈፅም ሲቀርና ሲያበላሽ በሀገሪቱና ዓለም አቀፍ ህጎች የሚጠየቅና የሚዳኝ ሀገራዊ ኃይል ነው፡፡ ስለሆነም ህግን ተከትሎ ወገኑን ከሰቆቃና እልቂት ለመታደግ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋእትነት በጀግንነት በመክፈል የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም ያስከብራል፡፡

የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተከፋይ፤ ጉዳይ አስፈፃሚና በወንጀል የሚፈለግ ህገ-ወጥ ሽፍታ ስለሆነ የኃላፊነትና የተጠያቂነት መንፈስ አይሰማውም፡፡ በባህሪው ምክንያት ሊሰማውም አይችልም፤ ስለዚህም ነው እንደፈለገ የሚዋሸውና የግፎች ሁሉ ጥግ የሆነ ተግባር በገዛ ወገኑ ላይ የሚፈጽመው፡፡ ስለሆነም ህዝባችንን ከዚህ አሬመኔ ቡድን ቀንበር ለማላቀቅና ከከንቱ ጭፍጨፋ ለማዳን ህዝባችንና ለሀገራችን ይጠቅማል የተባለውን ሁሉ በመስዋዕትነታችን እውን ለማድረግ በከፍተኛ ብቃትና የላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ነን፡፡

ህዝባችን ከፍጅት ለመታደግ ሲባል መሆን የሚገባውን ሁሉ አጠቃላይ ሁኔታን በማያበላሽ አግባብ ቀጣይም ሊኖር እንደሚችል መታወቅ ይኖርበታል፡፡

እኛ ታላቅና ታሪካዊ ኃላፊነት ካለበት የመከላከያ ኃይል በሚጠበቅ አግባብ፣ ሁለተናዊ በሆነና ነገን አሻግሮ በሚመለከት እሳቤ እንዲሁም በወታራዊ ሳይንስና ጥበብ የምናደርገው እና እናንተ በጋለ ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ዛሬ፣ አሁን፣ እዚችው እዲሆን የምትፈልጉትን ሁሉ “አፍ በእጅ በሚያስይዝ” አስተማማኝና ዘላቂ በሆነ ድል ይታረቃል፡፡

ዛሬም ሆነ እስከ ወዲያኛው የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለመጉዳት የሚደረግ ከሰማይ በታች ያለ ፈተና ሁሉ እንደማንፈተን ታውቃላችሁ! ታምኑናላችሁም! ለኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ህዝቦች ደህንነት፣ የግዛት አንድነትና ለሀገረ መንግስቱ ቀጣይነት በመቆም የምንከፍለው መስዋእትነት ክብርና ኩራታችን ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ማለት ፅናት ነው! በፅናታችን ሀገራችንን እንታደጋለን!!

Leave a Reply