የአሸባሪው ህወሓት የጭካኔ በትር ሲታወስ

አሸባሪው ህወሓት በአፋርና አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን በወረረበት ወቅት በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አስከትሏል።

በዚህም ንጹኃን ወገኖችን ለሰው ልጆች በማይገባ አኳኋን ረሽኗል፤ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፤ ለከፋ አካል ጉዳት ዳርጓል፤ ህፃናትና እናቶችን አስገድዶ በመድፈር የጭካኔ በትሩን አሳርፏል።

በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ እና ሌሎች የሕዝብና የመንግሥት መገልገያ መሰረተ-ልማቶች ላይም የከፋ ዝርፊያና ውድመት አድርሷል።

የኢትዮጵያዊያን የማንነታቸው ጥግ የሆኑ ቤተ-እምነቶችን ሳይቀር አውድሟል፣ አርክሷል፣ ቅዱሳን መጽሐፍትንም አቃጥሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በተለያዩ የግንባር ቦታዎች በመዘዋወር የአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ኃይሎች በሰው ልጆች ብሎም በአገርና በሕዝብ ሃብትና ንብረት ላይ ያደረሰው ሰፊ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ሲዘግብ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

በደረሱበት ሁሉ አጥፊና የሕዝብ ጠላት መሆናቸውን በተግባር ያሳዩት የሽብር ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች ከፍተኛ ጉዳት ካደረሱባቸው መካከል በሰሜን ወሎ መርሳ ከተማ እና በአፋር ክልል ካሳጊታ ይጠቀሳሉ።

በመርሳ ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ አድና መኮንን፤ “በእቅፍ ተንከባክቤ በማሳደግ ለቁምነገር ያበቃኋትን ልጄን ‘ከስድስት ወር ልጇ’ ነጥለው ገደሏት፤ ይኸው እኔም ህፃኑን ታቅፌ በሀዘን እርር ብያለሁ” ሲሉ ልባቸው በሃዘን መድማቱን መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

በሽብር ቡድኑ ወራሪዎች የተገደለው የ15 ዓመት ታዳጊ ልጃቸውም ቤተሰቡን ለመቀየር ትልቅ ራዕይ እንደነበረው ያነሳሉ፡፡

የህወሃት አሸባሪ ቡድን በመርሳ ከተማ የስድስት ወር ህፃን እናትና ወንድሟን “የደበቃችሁት ብር አለ እና ብሩን ካላመጣችሁ” በሚል ሰበብ በግፍ ገድለዋቸዋል፡፡

የሟቾቹ እናት ወይዘሮ አድና መኮንን በሽብር ቡድኑ ሁለት ልጆቻቸው ተገድለውባቸው ብቻቸውን የልጅ ልጅ ታቅፈው የሰቆቃ ጊዜ እያሳለፉ መሆኑን ይገልፃሉ፤ ሀዘናቸውም ከፊታቸው ይነበባል፡፡

በአፋር ክልል ካሳጊታ ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ አነስተኛ መንደር የሚገኙ ንጹኃን ወገኖችም የሽብር ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች የጭካኔ በትር አርፎባቸዋል።

የካሳጊታ ነዋሪ የሆኑት አቶ አሊ በቱ መሃመድ፤ የሽብር ቡድኑ በእነዚህ አካባቢዎች ለዓይን የሚቀፉና ለጆሮ የሚከብዱ ዘግናኝ ተግባራትን በመፈፀም የአረመኔነት ጥጉን አሳይቷል ይላሉ።

“አሸባሪው ህወሓት በካሳጊታ የገደላቸውን ንፁኃን እንቅበር ብንል እንኳን ከልክሎናል” ብለዋል።

See also  ሸገር ዳቦ - በሰዓቱ ማድረስ የሚችልበት አቅም እንደሌለው አስታወቀ

አሸባሪው በካሳጊታና አካባቢዋ የፈጸመው ግፍ በሰው ልጅ ላይ ይደረጋል ተብሎ የማይታሰብ “አረመኔያዊ ድርጊት” መሆኑንም ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በርካታ ንጹኃንን በግፍ እየገደለ፣ የአርሶ አደሩን እንስሳት እንደዋዛ እያረደ፣ ሀብት ንብረቱን እየዘረፈና እያወደመ ሕዝቡን ለመከራ ዳርጓል።

በራያ ቆቦ የዞብል ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አለም አከሎ፤ የሽብር ቡድኑ ኃይሎች ዞብል ከተማ በገቡበት ወቅት የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን በመስበር የእለት ምግብ የሚሆን እንጀራ፣ ሊጥና መሰል ቁሳቁስ ሳይቀር በመዝረፍ ዜጎች ላይ በደል መፈጸማቸውን ይናገራሉ።

የካሳጊታ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ወሊያ አብዱ በበኩላቸው፤ የህወሓት ወራሪዎች የመኖሪያ ጎጇቸውን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ ህፃናትን መግደላቸውን ገልጸዋል።

ጭካኔ ባህሪው የሆነው አሸባሪው ህወሓት ንጹኃንን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉ ሳያንስ በክብር እንዳይቀበሩም ጭምር ማድረጉን የሐራ ከተማ ነዋሪ ሆኑት ሸኽ ሲራጅ መሀመድ ይናገራሉ።

የሽብር ቡድኑ ከ40 በላይ ንጹኃን ወገኖችን በመረሸን ሥርዓተ-ቀብራቸው እንኳን እንዳይፈጸም በማድረግ የጅብ ሲሳይ አድርጎብናል ሲሉ ይገልፃሉ።

አሸባሪውን የህወኃት ኃይል በመፋለም ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር አኩሪ ተጋድሎ ከፈጸሙ አካላት መካከል ተጠቃሽ የሆኑት የድሌ ሮቃ ከተማ ነዋሪው አርሶ አደር ሐሰን ከረሙ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሓት ለ27 ዓመታት አገርን መበዝበዙ ሳያንስ አገሪቱን እኔ ካልገዛሁ በሚል ንጹኃን ዜጎችን በጭካኔ መግደሉንና በአገር ሃብትና ንብረት ዝርፊያና ውድመት ማስከተሉን ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅትም የሽብር ቡድኑ በአገርና ንጹኃን ወገኖች ላይ ያደረሰው የሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ቁስል ሳይሽር ኢትዮጵያ ለሰላም የዘረጋችውን እጅ በመግፋት በዳግም ወረራ ተጠምዷል።

(ኢዜአ)

Leave a Reply