ከወልድያ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት የተላለፈ ውሳኔ

የከተማውን አሁናዊ ሁኔታ መነሻ ከተማ በማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የሰዓት እላፊ ገደብ ማውጣቱ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ክልከላዎችን ማስቀመጥ በማስፈለጉ የከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ ምክር ቤት የሚከተሉትን ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

  1. ከፀጥታ መዋቅሩ ውጭ በከተማችን በየትኛውም ቦታ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በፍጹም የተከለከለ ነው፡፡
  2. ከተፈቀደላቸው የመንግስት የፀጥታ አባላት ውጭ የሰራዊቱን አልባሳትን መልበስ የተከለከለ ነው፡፡
  3. ሀሰተኛ ወሬ በመልቀቅ የከተማውን ማህበረሰብ የሚያውኩ አሉባልታዎችን በሚዲያዎችና በአገልግሎት መስጫ ተቋማት በማሰራጨት ህዝቡን ማዋከብ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
  4. በከተማችን የህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ባንክ ቤት፣ ሱቆች፣ ሆቴሎች፣ ካፌና ሬስቶራንቶች፣ የንግድ ተቋማት እና የመሳሰሉትን መዝጋት ፍጹም የተከለከለ ነው፡፡
  5. ማንኛውም የግል ተሸከርካሪ ለፀጥታ ስራ ትብብር ሲጠየቅ የመተባበር ግዴታ አለበት። ነገር ግን ተሸከርካሪን የሚሸሽግ፣ የሚያሸሽ፣ ሆን ብሎ ተበላሸ በሚል ላለመተባበር ጥረት የሚያደርግ ግለሰብ እና ድርጅት ተጠያቂ ይሆናል።
  6. የመኖሪያ ቤትና የመኝታ አልጋ የሚያከራይ ግለሰብ የተከራዮቻችሁን ማንነት የመለየትና የታደሰ መታወቂያ ስለመያዛቸው የማረጋገጥ ግዴታ ሲኖርባችሁ አጠራጣሪ ጉዳይ ሲኖር ለጸጥታ አካል ሪፖርት የማድረግ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ በግልፅ እናሳስባለን
  7. ፀጉረ ልውጥ ሰው የሚያገኝ ግለሰብ በቅርቡ ለሚገኝ የፀጥታ አካል የመጠቆምና የማቅረብ ኃላፊነት ይኖርበታል
  8. ከነሀሴ 29/2014 ዓ.ም ጀምሮ የቀበሌ መታወቂያ መስጠት የተከለከለ መሆኑን እናሳውቃለን።
  9. ማንኛውም የመንግስት እና የግል ታጣቂ አካባቢውን በብሎክ አደረጃጀት ውስጥ በመካተት በየደረጃው ያለ የፀጥታ አካላት በሚሰጠው ስምሪት አካባቢውን የመጠበቅ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት
  10. አግባብነት የሌለው የዋጋ ንረት መፍጠር፣ በሸቀጦችና በግብርና ምርቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ጨምሮ ህዝቡን ማስቃየት፣ በማንኛውም ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መገኘት በህግ ያስጠይቃል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩትን ውሳኔዎች ማንኛውም አካል የማክበርና ኃላፊነቱን የመወጣት ግዴታ ያለበት መሆኑንና ይህን ውሳኔ የማያከበር ግለሰብም ሆነ ድርጅት ላይ የፀጥታ መዋቅሩ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንደሚወስድ በአጽእኖት እናሳውቃለን፡፡

የወልድያ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት

ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም.

ወልድያ

See also  የኢቲቪ "ጋዜጠኛ" በአደገኛ ዕፅ ዝውውር በቁጥጥር ሥር ዋለ

Leave a Reply