የወያኔ አዲሱ የፖለቲካ ስልት!- ለአማራ

አሮጌዉና ለጊዜዉም ቢሆን አብልቶት የነበረዉ የወያኔ የፖለቲካ ስልት አማራን በአንደኛ ደረጃ ጠላትነት መፈረጅና የጨቋኝና ተጨቋኝ ትርክትን በማንበር ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ለአማራ ያላቸዉ አመለካከት በጎ እንዳይሆን ማድረግ ነበር። ይህ የፖለቲካ ስልት ለወያኔ በተለይም ላለፉት 27 አመታት ተጨባጭ ዉጤት አላመጣለትም ማለት አይቻልም፣ አምጥቶለታል። ዛሬ ላይ አማራ ክልል ዉስጥ የሚታዩት ዋና ዋና ችግሮችና ከአማራ ክልል ዉጭ በሚኖረዉ አማራ ላይ የቀጠለዉ ግድያ፤ ዝርፍያና መሳደድ የወያኔ ፖለቲካ ትሩፋቶች ናቸዉ።

ይሁን እንጅ አሁን ላይ ወያኔ ይህ አሮጌ የፖለቲካ ዘይቤዉ ብዙም የሚያስኬደዉ እንዳልሆነ ቁጭ ብሎ እንደገመገመ አንድ የፖለቲካሀ-ሁን ላነበበ ሰዉ በቀላሉ ለመገንዘብ አይከብደዉም። በተለይም የወያኔ መሪዎች አማራ ጠላቴ ነዉ፤ ከአማራ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን በሚል የፃፉዋቸዉና የተናገሯቸዉ ንግግሮች መለስ ብለዉ ሲያይዋቸዉ ከባድ ዋጋ እንዳስከፈላቸዉ ወያኔዎች በደንብ ገምግመዋል።

ስለሆነም ቢያንስ ታክቲካሊ ለአማራ የነበረንን አተያይና አያያዝ እንቀይር የሚል ዉሳኔ ላይ ደርሰዋል። ጉዳዩንም በቃ ካሁን በፊት የመጣንበትን መንገድ ዘግተን በአዲስ መንፈስ ከአማራ ጋር ግንኙነታችን ይታደስ፤ ያለፈዉ ይበቃል አይነት ፕሮፓጋንዳ ተጀምሯል፤ ይሄንን ጉዳይ ወያኔዎችና ሚዲያወቻቸዉ አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉበት ይጠበቃል።

አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ነገር አለ። ወያኔ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰዉ እንዲሁ አይደለም። በደንብ አሰቦበት፣በተለይም በዉጭ አገር ከሚኖሩ አንዳንድ አማራን እንወክላለን ከሚሉ ወገኖች ጋር በቀጥታ እንዲሁም በአገር ዉስጥ ከሚገኙ አንዳንድ ወንድም/እህቶች ጋር ቢያንስ በተዘዋዋሪ መንገድ የተመከረበት አጀንዳ ነዉ ብየ አምናለሁ። ይሄን የምለዉ እንዲሁ ሳይሆን በነዚህ ሁለት ወገኖች የሚካሄደዉን የተናበበ የፕሮፓጋንዳ ስራ በመገምገም ነዉ።

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት አንድ መሰረታዊ ጥያቄ አለ። ይሄዉም ወያኔ እንዴት ወደዚህ አይነት የአቋም ለዉጥ ( አማራ ወዳጀ ነዉ) ሊደርስ ቻለ? አንዳንድ የአማራ ወንድም/እህቶችስ እንዴት አማራን በቀዳሚ ጠላትነት ፈርጆ አሳሩን ሲያበላዉ ከኖረ ፣ ዛሬም ድረስ በወረራ እያሰቃየዉ ካለ ድርጅት ጋር ተባብረዉ ለመስራት ፍላጎት አደረባቸዉ? የሚለዉ ነዉ።

በእኔ ግምገማ ወያኔ ወደዚህ ደረጃ የደረሰዉ የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን ምክር እንደገና ያጤነዉ ይመስለኛል። ፕ/ር ፍቅሬ ስለ ” ኦሮሞና አማራ ከአንድ የዘር ግንድ ስለመገኘታቸዉ” በሚያትተዉ መፀሀፉ በግልፅ እንደነገረንና እኔም የገዛሁት ሀሳብ ቢኖር ፣ በኢትዮጵያ የረዥም ታሪክ ሂደት አማራ ገዝቶ አያዉቅም፣ገዝቷል ከተባለም ገዥዎቹን ብንቆጥር ዋነኛ ገዥ የነበረዉ ኦሮሞ ነዉ ይላል። ይልቁንስ እንደ ፕሮፌሰሩ እምነት አማራን ገዥ ያስባለዉ፤ አማራ የደገፈዉ ማንም ቢሆን መንገስ ይችላል፣አማራ ያልደገፈዉ ደግሞ በስልጣን አይሰነብትም”። ይህ አባባል በአጭሩ ሲጠቃለል አማራ የገዥነት አባዜ አልነበረዉም፣ገዥም አልነበረም፣ነገር ግን ሌሎችን በማንገስም ይሁን እንዳይነግሱ በማድረግ ፣ከፈለገም ከንግስና ማንሳት የዳበረ አቅምና ልምድ አለዉ እንደማለት ነዉ።

See also  በ30 ቢሊዮን ብር ወጪ 3 የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ለባለሃብቶች ክፍት ሆኑ

የፕሮፌሰሩ ትንታኔ እዉነት ይመስላል። አሁን ወያኔ የገባዉ ነገር ይሄዉ ነዉ። ለነገሩ እኮ ወያኔ ይሉኝታ ቢስ ሁኖ እንጅ እሱም እንዲነግስ ትልቁን ሚና የተጫወተዉ አማራ እንደነበር ይታወቃል። የጎንደር፣ወሎ፣ሽዋና ጎጃም ገበሬ ከኢህአዴግ ጎን ባይሰለፍ ኖሮ ወያኔ ለ27 አመት በኢትዮጵያ ምድር ባልነገሰ ነበር። አንጋሹ አማራና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በቃ ባሉት ጊዜ ደግሞ ከንግስናዉ አዉርደዉታል። በዚህ በኩል በተለይም ሀምሌ 5/2008 ዓ.ም ጎንደር ላይ የፈነዳዉ ፀረ-ወያኔ አመፅ፣ የወያኔ ንግስና ዕድሜ እንዳሳጠረዉ ይታወቃል። ለዚህ ነዉ ወያኔ ከንግስናዉ ከተገፋ በሁዋላ ጠላቴ አማራ ነዉ የሚለዉን ትርክቱን ወደ አማራ ኢሊት ያወረደዉ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ በተለይም የጎንደር ኢሊት ማለት የጀመረዉ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወያኔ አማራን ከፋፍሎ ለመምታትና ለማዳከም ያስችለኛል ያለዉን” ጎንደርንና ጎንደሬዎችን ነጥሎ የመምታት ስትራቴጀ ” ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህ በኩል ብዙም ባይሆኑ ስትራቴጅዉን የተቀበሉና ለመተግበር ቁርጠኛ የሆኑ ተከታዮችን አፍርቷል። እነዚህ የዚሁ ስትራቴጅ አሰቀጣዮች አካላት በአገር ዉስጥም ሆነ በዉጭዉ አለም ይገኛሉ። ደግነቱ አይችሉም!!!

አንዳንድ የአማራ ወንድም/እህቶችስ እንዴት የአማራን ህዝብ በቀዳሚ ጠላትነት ፈርጆ ሲሰራ ከኖረና ዛሬም ድረስ እየሰራ ካለዉ ወያኔ ጋር መግባባትና አብረዉ ለመስራት ፍላጎቱ አደረባቸዉ የሚለዉን ነጥብ ደግሞ በዉል ማጤን ያስፈልጋል።

እስካሁን ባለኝ ግምገማ አንዳንዶቹ ወደዚህ አቋም የደረሱት ለብልፅግና መንግስት ካላቸዉ ስር የሰደደ ጥላቻ የሚመነጭ ይመስለኛል። ነገር ግን ብልፅግናን መጥላት የግድ ወያኔን መዉደድ ያስከትላል ወይ? አንዳንዶቹ ደግሞ ፖለቲካ ሰራን ብለዉ የምንታገለዉ ብልፅግናንም ወያኔንም ነዉ በሚል ለድክመታቸዉ ሽፋን ሊሰጡት ይሞክራሉ። እስኪ በሞቴ በአሁኑ ወቅት የአማራ ህዝብ በአንድ ጊዜ ወያኔንም ብልፅግናንም የሚታገልበት ኮዝና አቅም አለዉ?

ብቻ ገራሚ ነዉ።ለሁሉም በዚህ አሰላለፍ ዉስጥ ለገባችሁ ወገኖቸ ያለኝ ምክር በጊዜ ሰልፋችሁን እንድታስተካክሉ ነዉ። ብልፅግናን በልኩ መታገል ይገባል፣ እንድትታገለዉ የሚያስችሉህ በርካታ ምክንያቶችም አሉ። እነዚህን በወጉና በቅጡ እንዲሁም ወቅት ሲፈቅድ መታገል ይገባል። ሆኖም ብልፅግናን ለመታገል/ለመጣል ሲባል ብቻ ከአማራ ህዝብ ታሪካዊ ጠላት ጋር በቀጥታም ሆነ ስልታዊ በሆነ መንገድ አብሮ መሰራት/ለመስራት መሞከር ዉጤቱ አደገኛ ነዉ።

See also  ኢንሳ የኮንዶሚኒየም ዝርፊያን ትስስር በምርመራ አጋለጠ፣ እጣው ውድቅ ሆነ

በመጨረሻም ሁኔታዎች እንደገና የሚያረጋግጡልን ነገር ቢኖር የአገራችን በተለይም የአማራ ፈተና ከዉስጥና ከዉጭ መሆኑን ነዉ። እንደ አማራ ዉጫዊ ፈተናዉ የወያኔ ድርጊት ሲሆን የዉስጡ ደግሞ አማራ ሁነዉ ከአማራ ታሪካዊ ጠላት ጋር ፍቅር ዉስጥ ለመዉደቅ እየሞከሩ ያሉ ወገኖች መኖራቸዉ ነዉ። በእንደዚህ አይነት ወቅት ከባዱ ፈተና ደግሞ ከዉስጥ የሚከሰት ፖለቲካዊ በሽታ ነዉ። ይህ ሁኔታ የአመራሩን አጠቃላይ ሁኔታ ይፈትነዋል፤ሰራዉንም ያከብድበታል። መከራ እኮ ነዉ የገባነዉ ጎበዝ!

እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለብን ሀቅ አለ። ይሄዉም ትላንትም፣ዛሬም ሆነ ነገ የአማራ ህዝብና የትግራይ ህዝብ አብረዉ ኑረዋል ለወደፊቱም አብረን እንኖራለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ስለሆነም ምንም እንኳ አብዛኛዉ የትግራይ ህዝብ በወያኔ መራሹ ወረራ ተሳታፊ ቢሆንም እንዲሁም ወረራዉን ያወገዘ ባይሆንም፣ ሁኔታዎችን ስለምንረዳ እንደ ህዝብ የጠላትነት ስሜት እንዲፈጠር አንፈልግም። የአማራ ህዝብ ጥላቻዉና አብሮ ለመኖር የሚከብደዉ ከወያኔ መራሹ የትግራይ ስርዓት ጋር ነዉ። በመሆኑም የአማራ ህዝብ ሰላም፤ ዝምድና እና አብሮ መኖር የሚፈልገዉ ከትግራይ ህዝብ ጋር እንጅ ከወያኔና እሱ ከሚመራዉ ስርዓት ጋር አይደለም። ይህ እንዲሆን ደግሞ የወያኔን ጉዳይ መልክ ማስያዝ ቀዳሚ አጀንዳችን ሊሆን ይገባል።

ድል ለመከላከያ ሰራዊታችንና በሱ ስር ለሚመሩ ሁሉም የፀጥታ ሀይሎቻችን!!!

ሰላም ለኢትዮ- ኤርትራ!! Chchu Alebachew

Leave a Reply