ሰዎች የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ወይም የማይገባቸውን አገልግሎት ከመንግስት ወይም መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ለማግኘት የተለያዩ እውነተኛ ያልሆኑ መረጃዎችን የያዙ ሰነዶችን ሲያቀርቡ ይስተዋላሉ፡፡
በተለይም ሀሰተኛ የማንነት መታወቂያ፣ የጋብቻ ፣ የልደት፣ የሞት፣ የትምህርት እና የስራ ምስክር ወረቀቶች፤ የውክልና ምስክር ወረቀት፣ የህክምና ማስረጃዎች፣ የባንክ ሲፒኦ፣ ቼኮች፣ የአሽከርካሪ ፈቃድ፣ የፍርድ ግልባጭ ወዘተ በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ወይም በሀሰት ከሚዘጋጁ የሰነድ አይነቶች የተወሰኑት ናቸው፡፡

እኚህን እና ሌሎች ሀሰተኛ ሰነዶችን ማዘጋጀትና መገልገል በሀገር ኢኮኖሚ እንዲሁም በዜጎች መብትና ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ የወንጀል ድርጊት ነው፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የወንጀል ህጉን ከማስከበር እና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ እያከናወናቸው ካሉ በርካታ ተግባራት መካከል አንዱ ሀሰተኛ ሰነድን አዘጋጅተው ወይም ተገልግለው በሚገኙ ሰዎች ላይ የህግ ተጠያቂነትን ማስፈን ነው፡፡ በዚህም መሰረት ሀሰተኛ ሰነዶችን ባዘጋጁ እና በተገለገሉ አያሌ ሰዎች ላይ ክስ በመመስረት እንዲቀጡ ማድረግ ችሏል፡፡
ይሁንና ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰነዶቹ የሚዘጋጁበት መንገድ እየዘመነ መምጣቱ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚስተዋለው ቸልተኝነቶች ተጨምሮበት ወንጀሉ ከመቀነስ ይልቅ እየተበራከተ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡
በዚህም ምክንያት ብዙዎች የማይገባቸውን ጥቅም አግኝተዋል፤ በመንግስት እና የህዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወደዚህ ደግሞ ህግን በሚያውቁ የሕግ ባለሙያዎች ሳይቀር ሀሰተኛ ሰነዶች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ከወራቶች እና ከቀናት በፊት ክስ መስርተን ወደ ፍርድ ቤት ያቀረብናቸው ጉዳዮች ዋቢ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ያመላክታል፡፡

በመሆኑም ፍትሕ ሚኒስቴር፡-

•የማይገባቸውን ጥቅም ለማገኘት ሀሰተኛ ሰነዶችን በማቅረብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የሚያታልሉ ግለሰቦች ከዚህ አይነት ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፤
• በሀሰት የተዘጋጁ ሰነዶችን በዝግጅት ሂደት ላይም ይሁን ለአገልግሎት መቅረቡን ያየ ወይም ያወቀ ማንኛውም ግለሰብ በአቅራቢያ ለሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ የበላይ ኃላፊ ጥቆማ እንዲሰጥ፤

• ተቋማት ለተገልጋይ የሚሰጡት አገልግሎት በትክክልም ለሚገባው የተሰጠ መሆኑን የሚያረጋግጡበትን አስተማማኝ ዘዴ እንዲያለሙ እና እንዲተገብሩ፤
• የፍትሕ ተቋማት (የዐቃቤ ሕግ ተቋማችንን ጨምሮ) የሚቀርቡላቸውን ጥቆማዎች እና ክሶች በተገቢው በማስተናገድ ሀሰተኛ ሰነድ መርገጫ እንዲያጣ የማድረግ ኃላፊነታችውን እንዲወጡ፤

• ተቋማት ሀሰተኛ ሰነዶችን በመፍጠር፣ ወይም በመስጠት ወይም ሰነዶችን በተገቢው የማጣራት ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ ከወንጀለኛ ጋር የሚያብሩ ሰራተኞች ላይ ተገቢውን የክትትል ስርዓት ዘርግቶ እርምጃ በመውሰድ ከፍትሕ ጎን እንዲቆሙ ይጠይቃል፡፡

ምንጭ፡-የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር

Leave a Reply