“መንግሥት ቢያጠቃ ለምንድን ነው በቆቦ በኩል የምናጠቃው? የአላማጣን እና የግራ ካሱን ተራራ ልንገፋ?” አምባሳደር ባጫ ደበሌ

በሰሜን ኢትዮጵያ ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ስማቸው ሲነሳ ከነበሩት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መካከል ጄኔራል ባጫ ደበሌ አንዱ ናቸው።

ከወራት በፊት ከጦር ሠራዊት አመራርነታቸው ወጥተው በአምባሳደርነት የተሾሙት ጄኔራል ባጫ፣ ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ጎረቤት እና የምሥራቅ አፍሪካ ኃያል አገር በሆነችው ኬንያ አምባሳደር ሆነው በቅርቡ ሥራቸውን ጀምረዋል።

ከወታደራዊው ኃላፊነት ወጥተው በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከተሰማሩ በኋላ አምባሳደር ባጫ ደበሌ የመጀመሪያውን ቃለ ምልልሳቸውን ከቢቢሲ ጋር አድርገዋል።      

ቢቢሲ፡ ህወሓት በቅርቡ ለተለያዩ አካላት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከመንግሥት ተወካዮች ጋር በምስጢር ተወያይቻለሁ ብሎ ነበር። ይህ እውነት ነው? ከሆነ ውይይቱ የት ተደረገ? እነማን ተገናኙ?

አምባሳደር ባጫ፡ ይህ በምስጢር ተገናኙ የሚባለውን ነገር አላውቅም። ህወሓት የሚናገው ነገር በሂሳብ ነው። አንድ እና አንድ ሁለት ነው ይላል። ከፈለገም አንድ ሺህ ነው ይላል። ስለዚህ ህወሓት ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲል የፈለገውን ነገር ይላል። በምስጢር የተገናኙበትን ሁኔታም አላውቅም፤ ሁለተኛ ደግሞ ቦታውንም አላውቅም።

በምስጢር የሚገናኙበት ምንም ምክንያትም የለም። ምክንያቱም በግልጽ ድርድር ያስፈልጋል ተብሎ ኮሚቴ ተዋቅሮ እያለ፣ በድብቅ የሚኬድበት ምንም ምክንያት ያለ አይመስለኝም።

ቢቢሲ፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የአሁኑን ጦርነት የትግራይ ኃይሎች ጀመሩ ሲል ይከስሳል። ምን ማስረጃ አለው?

አምባሳደር ባጫ፡ ህወሓት ቆቦን ይዤያለሁ ብሎ ሲያወጅ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱን አለመጀመሩ ለማወቅ ይቻላል። ጦርነት ተቀሰቀሰብኝ የሚል ኃይል በምን ቅጽበት ነው የኢትዮጵያን ሠራዊት፣ ዋጃን ፊት ለፊቱ አድርጎ መከላከል የያዘን የኢትዮጵያ ሠራዊት፣ በቆቦ በስተቀኝ ደግሞ የዞብል አምባን መሠረት አድርጎ መከላከል የያዘን የኢትዮጵያን ሠራዊት፣ በአንድ ጊዜ ንዶ ቆቦን የሚይዝበት ተዓምራዊ ኃይል የሚኖረው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ማጥቃቱን ቢጀምር ኖሮ ህወሓት ቆቦን ሊይዝ አይችልም። ምክንያቱም አንድ ሰው፣ ሁለት ሰው ሦስት ሰው አይደለም የምትልከው። በውጊያ ሕግ አንድን ጠላት ስታጠቃ የኃይል የበላይነት ሊኖርህ ይገባል። እኛ ልናጠቃ ብንፈልግ ኖሮ እኮ በዚያ አካባቢ የኃይል የበላይነት ፈጥረን ነው የምነገባው።

ስለዚህ ህወሓት በዚያ አካባቢ ያሰለፈው አዲስ ያመጣው ኃይል ስድስት አርሚ ነው። አንዱ አርሚ ሦስት ክፍለ ጦሮች አሉት። ወደ 18 ክፍለ ጦር ነው እዚያ ያሰለፈው ማለት ነው። ስለዚህም የኃይል የበላይነት አለው ማለት ነው። ከእኛ የኃይል የበላይነት ነበረው። 

ቢቢሲ፡ በቆቦ ግንባር ብቻ ማለት ነው ይኼ?

አምባሳደር ባጫ፡ በቆቦ ግንባር አዲስ ያሰለፈው ማለት ነው። አንድን ማጥቃት ስታደርግ ደግሞ የኃይል የበላይነት ከሌለህ አጥቅተህ የምትፈልገውን ግብ መያዝ አትችልም። ስለዚህ እኛ የምናጠቃ ቢሆን ኖሮ፣ የኃይል የበላይነት እንፈጥራለን፣ ወያኔ መልሶ በማያጠቃበት ሁኔታ ነው የምናጠቃው እና ቆቦን መልሶ የሚይዝበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ምናልባትም በተገላቢጦሽ መኾኒን እና የመሳሰሉትን ከተሞች መቆጣጠር እንችል ነበር።

ለማጥቃት ለማጥቃቱ እኛ እኮ ከደብረ ሲና ስናስወጣቸው የኃይል የበላይነት ፈጥረን የውጊያ ቀጣይነትን ጠብቀን፣ ብረት በግለቱ ነው የሚቀጠቀጠው እና መቀለ ማድረስ ይቻል ነበር።  

ግን ደግሞ ያንን ትተን ለሰላም ሲባል፣ ሕዝብ እንዳያልቅ፣ ሕጻናት እንዳያልቁ ሲባል አላማጣ ነው ጦርነቱ የቆመውና የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ያወጀው። ስለዚህ እኛ አላጠቃንም። እኛ ብናጠቃ ልክ ከደብረሲና እንዳስወጣናቸው እዚህም እንደሱ ነበር የምናደርገው። ስለዚህ ወያኔ ራሱ አጠቃ፣ ራሱ ተጠቃሁ አለ።

See also  አቡን ማትያስ [አባ ተክለማርያም አስራት] እንዴት እንመናቸው?

ተመትቶ ወደቀ ስለተባለው አንቶኖቭ አውሮፕላን ምን የሚታወቅ ነገር አለ?5 መስከረም 2022

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መንግሥት እና ህወሓት ወደ ድርድር እንዲመጡ ጫና ማሳደር ይችላል?2 መስከረም 2022

ከወራት የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ ጦርነቱ ለምን አገረሸ?1 መስከረም 2022

ቢቢሲ፡ በዚህ ጦርነት የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ዘልቆ የመግባት እቅድ አለው? መከላከያ መቀለ ቢገባ የመጨረሻው ግቡ የሚሆነው ምንድን ነው?

አምባሳደር ባጫ፡ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት መቀለን ነው የምቆጣጠረው፣ የሆነ ቦታን ነው የምቆጣጠረው ብሎ አቅዶ የተነሳው ጦርነት የለውም። ምክንያቱም ወያኔ የፈጠረውን በፀረ ማጥቃት የመጣውን ኃይል ማጥፋት ነው። በግልጽ የምነግርህ ወያኔ ከበረታ የኢትዮጵያን ሠራዊት ደምስሶ ኢትዮጵያን ያፈርሳል። እኛ ደግሞ ከበረታን ወያኔን አጥፍተን እፎይታ እናመጣለን። ጦርነት ነው። ይህንን ነው የምትጠብቀው። አንዱ ያሸንፋል። እኛ ጦርነቱን የመቀስቀስ ግብ አልነበረንም፤ ቢሆን ኖሮ በደንብ ተዘጋጅተን፣ የት መድረስ አለብን፣ ምን ማድረግ አለብን የሚል ነገር ትወስናለህ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቢያጠቃ ለምንድን ነው በቆቦ በኩል የምናጠቃው? የአላማጣን እና የግራ ካሱን ተራራ ልንገፋ? ለምንድን ነው በዚያ በኩል የምናጠቃው? [መልክዓ ምድሩ] በዚያ እንድታጠቃ አይጋብዝም።

ምክንያቱም ከፍተኛ የሆኑ መሬቶች ከፊት ለፊት ነው ያሉት። እና ደግሞ ይኼ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ የሚፈጥረው ጉዳት ከፍተኛ ስለሚሆን እንደ ማጥቂያ አቅጣጫ አንመርጠውም። የሚመረጡ ሌሎች ቦታዎች ስላሉ ማለት ነው። ስለዚህ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔው ህወሓት ጠመንጃ እስካላስቀመጠ ድረስ ሁሉንም ዓይነት ርምጃ ይወስዳል።

ቢቢሲ፡ መቀለ መቆጠጠርም ቢሆን?

አምባሳደር ባጫ፡ ማንኛውንም ዓይነት፣ መቀለ ምንም አይደለም። መቀለ ከተንቤን ከአክሱም ከሽረ የተለየ ነገር የለውም።

ቢቢሲ: መቀለን መቆጣጠር ስል የህወሓትን ከሥልጣን አውርዶ አዲስ አስተዳዳሪ መሾም ማለቴ ነው።

አምባሳደር ባጫ፡ መንግሥት እርሱ ዕቅድ የለውም። አካባቢው ጦርነት ቀጠና ስለሆነ ህወሓትን የያዘው ሥልጣን ስለሌለ፣ የሚወርድበት ሥልጣን የለውም። ዋናው ነገር የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት የተከፈተበትን ጥቃት ደምስሶ፣ ህወሓትን አስገድዶ ወደ ውይይቱ ማምጣት ነው። አለበለዚያ ግን ጨርሶ ማጥፋት ነው የሚሆነው።

ቢቢሲ፡ ባለፈው ሳምንት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከኤርትራው አምባሳደር ጋር ውይይት ማድረጎትን ተመልክተናል። ባለፉት ቀናት ደግሞ የትግራይ ኃይሎች፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሠራዊት ጥቃት ከፈቱብን ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በድጋሚ ኤርትራን ያሳተፈ ጥቃት ከፍቷል?

አምባሳደር ባጫ፡ እኔ ኤርትራን ያሳተፈ ጥቃት አላውቅም። …የኤርትራ ሕዝብ ራሱን የመከላከል መብት አለው። የኤርትራ መንግሥት ራሱን የመከላከል መብት አለው።… አሁን መንግሥት ከኤርትራ መንግሥት ጋር አደረገ ስለሚባለው ትብብር ለማሳየት አይደለም እኔ ከአምባሳደሩ ጋር የተገናኘሁት።

የኤርትራው አምባሳደር በየነ ርዕሶም፣ እዚህ አገር ረዥም ጊዜ ቆይተዋል። የአፍሪካ አምባሳደሮች ዲን ናቸው። ስለዚህ እርሳቸው የአፍሪካ አምባሳደሮች ዲን ከሆኑ ደግሞ የመጀመሪያው ‘ከርተሲ ኮል’ [ትውውቅ] የሚደረገው ከእርሳቸው ጋር ነው። ከእርሳቸው ጋር መጀመሪያ ከተገናኘሁ በኋላ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች ጋር እገናኛለሁ።

ስለዚህ ከእርሳቸው ጋር መገናኘቴ ህወሓት በጀመረው ጦርነት ላይ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትሰለፍ ጥሪ ለማቅረብ አይደለም። ጥሪ ለማድረግ ከሆነ እኔ ቅርብ አይደለም ያለሁት። ወይንም ደግሞ ክቡር አምባሳደር በየነ ርዕሶም ቅርብ አይደሉም። እርሳቸውም አይጠየቁም። የኤርትራ መንግሥት ለኢትዮጵያ መንግሥት ቅርብ ስለሆነ መንግሥታት ይነጋገራሉ። ስለዚህ ይህ የአጋጣሚ በመሆኑ ወደዚያ ባይተረጎም።

See also  የጦርነቱ ጅማሬ ምልክቶች - የአሜሪካ ድጋፍና ኢትዮጵያ ላይ ያለው ጫና

ቢቢሲ፡ የሰላም ጥረቶች የከሸፉት የኢትዮጵያ መንግሥት መሠረታዊ ግልጋሎቶችን ባለማስጀመሩ እና ከበባው ባለመነሳቱ ነው ሲሉ የትግራይ ኃይሎች ይከስሳሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት የአገልግሎቶቹን አለማስጀመር እንደ መደራደሪያ አድርጎታል?

አምባሳደር ባጫ ደበሌ፡ …ለትግራይ ውሃ፣ ኤሌትሪክ እና ሁሉን ነገር የማስገባት ጉዳይ የመንግሥት ግዴታ ነው። እነሱ ስለጠየቁ የሚሆን ስላልጠየቁ የማይሆን ነገር አይደለም። እነሱ ትግራይን በጠበመንጃ አጥረው፣ የጦርነት ቀጠና አድርገው፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት የፈጠረ የማያዳግም እርምጃ ይወሰድበታል ሲሉ አውጀዋል።

እንዲህ ጦርነት አውጀህ የትኛውን የባንክ አገልግሎት ነው የምትከፍተው? የቴሌኮም ሠራተኞችን ነው ወደ እዚያ የምትልከው? የመብራት ኃይል ሠራተኛ የውሃ ሠራተኛ ልትልክ ነው?

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በነበረበት ወቅት እንደዚህ ዓይነት ሥራዎችን ሊያስቀጥሉ የሄዱትን ሠራተኞች እኮ ገድለዋል። አንድ ሁለት ሦስት አይደለም። ሁሉም ቦታ የተሰማሩትን አጥፍተዋቸዋል። መድኃኒት ሲላክ ለራሳቸው ተጠቅመዋል…ስለዚህ እንዴት አድርጎ ነው አንድ ጦርነት ባለበት ቀጠና፣ ይህንን ሲጠይቁት የነበረውን ነገር የምትሟላው? . . . 

ቢቢሲ፡ ለድርድሩ መክሸፍ እና ለጦርነቱ ድጋሚ መጀመር ገፊ ምክንያቶች ታድያ ምንድን ናቸው?

አምባሳደር ባጫ ደበሌ፡ ወያኔ። ወያኔ ያለ ጦርነት አይኖርም። ወያኔ ሁለት ትልልቅ ነገሮች አሉት። እያቀያየረ የሚጠቀምባቸው ሁለት ካርዶች አሉት። አንዱ ካርድ ቅጥፈት፣ ውሸት ነው። አንድን ውሸት በሌላ ማለት ነው። እርሱም አሁን ባለንበት ሁኔታ ጦርቱን ሲጀምሩ ዋሹ። ሁለተኛም ደብረ ሲና ያደረሳቸውንም ጦርነት ሲጀምሩ መንግሥት አጠቃኝ ብለው ጀመሩ። ደብረ ሲና ደረሱ።

ሦስተኛው ደግሞ አሁን እኛ ስለእነርሱ ማጥቃት ምንም እሳቤ ሳይኖረን 18 ክፍለ ጦር አሰማርተው፣ 18 ለስድስት ማለት ነው። ምናልባት ስድስት ክፍለ ጦር ነው ቆቦ አካባቢ ሊኖር የሚችለው ብዬ ነው የማስበው። ከዚያ ያነሰም ሊሆን ይችላል። ይህንን ሁሉ ክፍለ ጦር ቆቦ አስቀምጠው ከዓለም ምግብ ድርጅት ነዳጅ ሰርቀው፣ ምግብ ሰርቀው፣ ሕጻናትን አሰልፈው ወደ ጦርነት ገቡ።

ስለዚህ ውሸትና ጠመንጃ ይዞ ነው ያለው። ሁለቱ ናቸው መጫወቻ ካርዶቹ። ጠመንጃውን በውሸት ይደግፋል። ውሸቱንም በጠብመንጃ ይደግፋል።. . .በተጨማሪም ሁልጊዜ ወደ ድርድር ሲገባ አደናቃፊ ቅድመ ሁኔታዎችን ያመጣል። ምክንያቱም ወደ ድርድር ከገባ ጠመንጃ ሊያስቀምጥ ነው። ህወሓት ደግሞ ጠመንጃ አስቀምጦ እንቅልፍ አይወስደውም። ስለዚህ ዋናው የዚህ ችግር ባለቤት ህወሓት ነው። ህወሓት ደግሞ የኢትዮጵያ ችግር ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድ ችግርም ነው።

ቢቢሲ፡ ጦርነቱ መልሶ ከተጀመረ በኋላ ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጦርቱን ለማስቆም ሙከራዎችን እያደረጉ ነው?

አምባሳደር ባጫ፡ በግልጽ የምናውቀው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሁሉም ኃይሎች ተኩስ አቁመው ወደ ድርድር መግባት አለባቸው ማለቱን ነው። ነገር ግን የሚጠበቀውን ያህል ውግዘት የለም።

…ተጠቅቻለሁ ብለህ ዘለህ አማራ ክልል መግባት የመጠቃት ምልክት አይደለም፤ የማጥቃት አንጂ። ይኼ እየታየ ለሕዝብ የተላከ እህል እየዘረፈ፣ ነዳጅ እየዘረፈ፣ ይኼ ለጦርነት እና ለከፍተኛ ማጥቃት ዝግጅት መሆኑ ይታወቃል።

See also  ኢትዮጵያ - የከፋ ድርቅ ሚሊዮኖችን ለችግር መዳረጉ ተገለጸ "ሸሽተው እየተፈናቀሉ እንደሚገኙም ነው"

ይህንን ማውገዝና ጠመንጃውን አስቀምጦ ወደ ድርድር እንዲገባ ተጽዕኖ መፍጠር ተገቢ ሆኖ እያለ፣ እኔ ከዓለም ማኅበረሰብ ‘እንደው ሁሉም ወገኖች’ የሚል ካልሆነ ሌላ አላየሁም። ሁሉም ዝምታን ነው የመረጠው።

. . . የዓለም ማኅበረሰብ የአፍሪካ ቀንድን ሰላም፣ ወይንም ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ ሰላም የሚፈልግ ከሆነ፣ ጠመንጃውን እንዲያስቀምጥ መደረግ አለበት። ስስለዚህ የዓለም ማኅበረሰብ ይህንን ተጽዕኖ ማድረግ አለበት። ነገር ግን ለጊዜው እኔ በግልጽ ያየሁት ነገር የለም።

ቢቢሲ፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲጀመር እርሶ ጄኔራል ነበሩ። በጦርነቱ ላይ የኢትዮጵያን ሠራዊት በመምራት ተሳትፈዋል። አሁን ደግሞ ዳግም ጦርነቱ ሲያገረሽ ዲፕሎማት ሆነው ኬንያ መጥተዋል። ይህ እርሶ ላይ የሚፈጥረው ስሜት ምንድን ነው?

አምባሳደር ባጫ ደበሌ፡ እኔ የሚፈጥርብኝ ስሜት፣ በአሁኑ ጦርነት እዚያ አለመሆኔ በጣም አሳዝኖኛል። ግን ደግሞ ይህም ትልቅ ተልዕኮ ስለሆነ ይህንኑ ተልዕኮዬን እቀጥልበታለሁ።

መጀመሪያ ጥሪ ተደርጎ ከመከላከያ ከወጣን በኋላ ነው ከጓደኛዬ ጋር የተመለስነው። ስመለስ እኔ በደስታ እግዚአብሔር ልዩ ነገር እንደፈጠረልኝ በግልጽ ተናግሬያለሁ። ያኔ ስሜቴ እርሱ ነው። ኢትዮጵያን መከላከል ስለሆነ ማለት ነው።

ምክንያቱም ከእነዚህ ሰዎች ጋር እኔ ረዥም ዓመት ኖርያለሁ። ስለዚህ የሚሰሩትን ነገር በደንብ አድርጌ አውቃለሁ። በዚያ ላይ አገርን ለመበተን ሲሮጡ፣ እነሱ ጠመንጃ ሲመዙ፣ ቢያንስ ይህንን ለመከላከል መሰለፌ በጣም ደስታን ሰጥቶኛል፤ ግዳጄን ተወጥቻለሁ ብዬ ነው የማስበው በዚያ ሰዓት።

ቢቢሲ፡ የአምባሳደርነት ሹመትዎ እንደተሰማ፣ ይህ ለእርሳቸው ሹመት አይደለም ዲሞሽን [ዝቅ መደረግ] ነው ያሉ ነበሩ። እርስዎ እንደዚያ ተሰምትዎታል?  

አምባሳደር ባጫ ደበሌ፡ ኢትዮጵያን ለማገልገል ዲሞሽን አይደለም። ወደ ኋላ ልውሰድህና ያልኩትን ላስታውስህ። ልክ ለውጡ እንደመጣ በሰጠሁት ቃለ ምልልስ ላይ ‘ተመለስና አገርህን አገልግል ብትባል ምን ሃሳብ አለህ?’ ተብዬ ተጠይቄ ነበር። መልሴም ‘እኔ ባለሁበት ፖዚሽን ሳይሆን፣ እንደ አንድ ተራ ወታደር ኢትዮጵያን አገለግላለሁ’ ነበር ያልኩት።

አሁንም ኢትዮጵያ ጭንቅ ላይ ነው ያለችው። እኛ የምንሰራበትን፣ የእኛን ምቾት ፈልገን፣ እዚህ መስራት አለብን፣ እዚያ መስራት አለብን፣ ብለን የምንመርጥበት ጊዜ አይደለም። አሁንም እዚህ ቦታ ላይ ገብተህ አገልግል ከተባልኩ፣ አይደለም አምባሳደር፣ ተራ ጥበቃ ሆኜ ኢትዮጵያን አገለግላለሁ።

. . . እኔ እያለሁ ወጣቶች ናቸው እያለቁ ያሉት። ስለዚህ አገራችን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለች፣ እዚህማ አልሰራም ከእኔ ብቃት በታች ነው። እኔ እነደዚህ ዓይነት ሰው ነኝ እና እዚህ አልሰራም የሚባልበት ወቅት አይደለም አሁን። ያንን ለልጆቻችን እንተውላቸው።

ልጆቻችን ቦታ እየመረጡ ካልፈለጉ የሚተዉበትን ሁኔታ እንፍጠርላቸው። ያንን የምንፈጥረው እኛ ደግሞ፣ ወደላይም፣ ወደ ታችም፣ ወደጎንም እየሄድን ሁሉም ቀዳዳ መሸፈን ትችላለህ በሚባልበት ቦታ ሁሉ ገብተን በመሸፈን ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ነው።

ስለዚህ እኔ በተመደብኩበት ቦታ በጣም ደስተኛ ነኝ። በጣም በሚገርም ሁኔታ እዚህ አገር ትልቅ ሥራ ነው ያለው። አሁን ለእናንተ ይኼ ይኼ ነው ብዬ አልነግራችሁም። ነገር ግን እኔ እዚያ ከተሰለፈው ሠራዊት ባልተናነሰ የምትሰራበት ከፍተኛው ግንባር ነው ይኼ። ስለዚህ በደስታ እሰራለሁ አገሬን አገለግላለሁ።

  ቢቢሲ  አምባሳደር ባጫ ደበሌ

Leave a Reply