ትህነግ 250 ሺህ ተዋጊ ኃይል ይዞ ከ44 ሺህ የእኛ ሰራዊት ጋር ተዋግቶ አላሸነፈም፡፡ ለ8 ወራት በውጊያና አሰሳ ላይ በመቆየት ከትግራይ የወጣውን ሐይላችንን መልሶ መቋቋም ባላደረገበት ሁኔታ ከ500 ሺሕ በላይ በሆነ የተዋጊ ማዕበል ተረባርቦበት ሊያንበረክከው አልቻለም፡፡

መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም

የክቡር የጦር ኃይሎች ጠ/ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መልዕክት ፡-

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን አመራሮችና አባላት፤
እንኳን በርካታ ፈተናዎችን በድል አድራጊነት ወደ ተሽጋገርንበት የ2015 አዲስ አመት አደረሰን፤ አደረሳችሁ!

ከቀደመው 2013 የተሻገረውን ጨምሮ 2014 ዓ.ም በአንድ በኩል ሀገራችን በርካታ ፈተናዎችንና የሕልውና አደጋዎችን የተጋፈጠችበት፤ በሌላ በኩል በሕዝባችን፣ በመሪዎቻችን፣ በመከላከያና በፀጥታ ሃይሎች የተቀናጀ ትግል ፈተናዎቹን በፅናት ያለፍንበትና ዓመቱን በድል አድራጊነት የተሽጋገርንበት ወቅትም ነው፡፡

ምንም እንኳን በአዲሱ 2015 ዓ.ም መባቻ አካባቢ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም አግኝቶ የሀገር ግንባታ ላይ ማተኮር መቻሉ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው የትህነግ ጁንታዎች የመንግስታችንን የተኩስ አቁም ውሳኔ ጥሰው ውጊያ ቢከፈቱብንም የትግራይን ወጣት ለጦርነት ከመማገድ ውጪ በተቀዳጀናቸው ድሎች የተገኙትን ውጤቶች መቀልበስና ቀጣዩን የዕድገት ግስጋሴያችንን መግታት ከቶውንም አይቻላቸውም::

ትህነግ 250 ሺህ ተዋጊ ኃይል ይዞ ከ44 ሺህ የእኛ ሰራዊት ጋር ተዋግቶ አላሸነፈም፡፡ ለ8 ወራት በውጊያና አሰሳ ላይ በመቆየት ከትግራይ የወጣውን ሐይላችንን መልሶ መቋቋም ባላደረገበት ሁኔታ ከ500 ሺሕ በላይ በሆነ የተዋጊ ማዕበል ተረባርቦበት ሊያንበረክከው አልቻለም፡፡

ትህነግ ሰሜን ሸዋ ደርሶ “ጦርነቱን ጨርሰነዋል” ብሎ በፎከረበት ወቅት የአራት ኪሎ ቤተ-መንግሰት በዓይኑ ላይ እንደዞረ በሠራዊታችን ክንድ ክፉኛ በመደቆስ ተሳቆ ተመለሰ እንጂ የቋመጠለትን ስልጣን አላገኘም፤ ወደፊትም አያገኝም!!

እኛ ወታደሮችም ብንሆንም የሰላምን አማራጭ እናስቀድማለን፡፡ ሰላም ለሀገር ዕድገትና ለሕዝባችን ሕይወት መለወጥ አስፈላጊ መሆኑን ስለምናምን ጦርነት ካልተከፈተብን ወደ ጦርነት አንገባም፡፡

የሀገራችንን ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣልና ሕዝባችንን ለማጎሳቆል ያለመ ኃይል ከየትኛውም አቅጣጫ ውጊያ ከከፈተብን ግን በአጭር ጊዜና በአነስተኛ ኪሣራ መመከት የሚያስችል ቁመናና ዝግጁነት ላይ እንደምንገኝ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማረጋገጥ እወዳለሁ!!!

ሁላችንም እንደምናውቀው የውጪና የውስጥ ጠላቶቻችን ተባብረው በቀጥታ ውጊያዎች፣ ሕዝብ ከሕዝብ በሚያጋጭ የሴራ ፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲና በስነ-ልቦና የተቀናጀ ጦርነት ከከፈቱብን ቆይተዋል፡፡
በተለያዩ ግንባሮች የተከፈቱብንን እነዚህን ውጊያዎች ለመመከት ሠራዊታችን ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል፡፡ ሕዝባችንም ሠራዊታችንን በሰው ኃይል፣ በቁሳቁስ፣ በገንዘብና ከሁሉ በላይ ደግሞ በሞራል በከፍተኛ ደረጃ ደግፏል፡፡

የሕዝባችንን ሁለ-ገብ ድጋፍና የሠራዊታችንን የዓላማ ፅናት በማቀናጀት በሳል አመራር የሠጡ የሀገራችን መሪዎች፣ የጦር አዛዦች፣ የፀጥታና የደህንነት ኃይሎች የጠላቶቻችን ከበባ በመበጣጠስና አከርካሪያቸውን በመሰበር አንፀባራቂ ድሎችን እንድንጎናፀፍ አስችለውናልና ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ባደረግነው ተጋድሎ አዲስ አበባ ሊገባ ነው ብለው ጋላቢዎቹና ፕሮፖጋንዲስቶቹ ከበሮ ሲደልቁለትና ኢትዮጵያ አለቀላት ብለው ሕዝባችንን ሲያሸብሩ የነበሩባቸው ሁኔታዎች ተቀይረው የትህነግ ጁንታዎች ለስልጣንና ለአዲስ አበባ እንደቋመጡ ከሰሜን ሸዋ ቀጥቀጠን መልሰናቸዋል፡፡ ሌሎች የውጪ ጠላቶቻችን ተልዕኮ አስፈፅሚና ጋሻ-ጃግሬዎች የሆኑ ቡድኖች በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች ሁከት ሲፈጥሩና ሰላማዊ ዜጎችን የመጨፍጨፍ አረመኔያዊ ተግባር ሲፈፅሙ የቆዩ ፀረ-ሰላም ኃይሎችንም አዳክመን ሀገርን ለማፍረስ አደጋ ወደማይሆንበት ደረጃ ያወረድንበት ዓመት ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን የሆነው አልሻባብም የመከላከያ ሠራዊታችንና የፀጥታ ኃይሎቻችን ተጣምረው ባሳረፉበት ጠንካራ ምት ዳግም ኢትዮጵያን በማይተነኩስበት ደረጃ ተቀጥቅጧል፤ ትምህርትም እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡

የሕዳሴ ግድባችን 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከተሳካ የግድቡ ግንባታ ወሳኝ ደረጃ እንደሚደርስ የተገነዘቡት ታሪካዊ ጠላቶቻችን ወደዚህ ወሳኝ ምዕራፍ እንዳንሽጋገር የክረምቱ ወራት ከመድረሱና በክረምቱ ወቅት አቅማቸው የፈቀደውን የማደናቀፍ ሙከራዎች ሁሉ አድረገዋል፡፡

በቤንሽንጉል፣ በጋምቤላ፣ በአራቱ የወለጋ ዞኖች፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በምዕራብ ጉጂ እንዲሁም በደቡብና በአማራ ሀገር ለማተራማስ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ አልሸባብ በምስራቅ ኢትዮጵያ፣ ከሸኔና ከትህነግ ኃይሎች የተውጣጡ አሸባሪዎች በመሃል አገር ለጥፋት ተግባር ተንቀሳቅሰዋል፡፡ እነዚህን ሁሉ አደጋዎችና የሴራ ድሮች በፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሀይሉ ክትትልና በሳል አመራር ተበጣጥሰው መክነዋል: ለዚህም ነው 2014 የፈተና ጊዜና ፈተናዎቹንም በድል ተወጥተን ወደ 2015 የተሸጋገርንበት ዘመን ነው የምንለው፡፡

የጠላቶቻችንን ሀገርን የማተራመስና የማፍረስ ሕልም በተቀናጀ ትግልና ተጋድሎ በመመከታችን ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ የሆኑ የልማት ውጥኖችን እውን እያደረገች ትገኛለች፡፡ ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን በርካታ ውስብስብ ችግሮችንና ጫናዎችን ተሻግሮ ግንባታውን 83 በመቶ ላይ በማድረስ የ3ኛው ዙር የውኃ ሙሌትና የ2ኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ስራ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል፡፡ ይህ ድል ብቻ ሳይሆን ከድሎች ሁሉ የላቀ የድል ድል ነውና እንኳን ደስ አለን እንኳን ደስ አላችሁ፡፡

በዚሁ አጋጣሚ በዘመናዊ ትጥቅና በሰው ሀይል አደረጃጀቱ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት መወጣት ወደ ሚችልበት ደረጃ የተሸጋገርው ሠራዊታችን በቀጣይም ዝግጁነቱን ባልተቋረጠ ሁኔታ እየሳደገ፤ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣ ጠላትን እንደሚመክት ለህዝባችን እያረጋገጥኩ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የዕድገትና የኢትዮጵያ ከፍታ ዘመን እንዲሆንልን መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!!

“መከታ” መፅሔት

Leave a Reply