ሕልም ሳይኖራቸው ፍቺ የሚጠይቁ ወበከንቱዎች

ምላሹን የምንጠብቀው ከትግራይ ወገናችን ነው። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከትግራይ ወንድሞቹና እህቶቹ ጎን ቆሞ ይህን የናቡከደነፆር መንፈስ ተሸካሚ የሆነውን ቡድን ግባ መሬት ለማፋጠን ኃይሉን ሊያስተባብር ይገባል።

የክፋት እርምጃ፤ የክፉዎች መራገጫ፤

ታሪክ በየዘመኑ ብጤ ክስተት አያጣም። በዚህ በእኛ ዘመንም «ግራ በገባቸው ግራ ገቦች» አማካይነት መልካቸው ለወጥ ያለ ቢመስልም የባህርይ ተመሳስሎ ያላቸው በርካታ ታሪኮች መሳ ለመሳ ሲፈጸሙ እያስተዋልን ነው። ሕልም ሳይኖራቸው ፍቺ የሚጠይቁ፤ ቅዠትን ከሕልም መለየት የተሳናቸውና ራእይ ለማየት ውስጣዊ ዐይናቸው የታወረባቸውና በደመ ነፍስ እየተመሩ የሚቅበዘበዙ የአገሬ ወበከንቱዎች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም።

የሕዝባችን ዋና የስቃይ ምንጭ ከሆኑት መከራዎቻችን መካከል አንደኛውና ዋነኛው ይኸው አገራዊ ችግር እንደሆነ ለማመን አይከብድም። ቅዠታቸው ሲበረታ እየተንፈራገጡ፣ ማንጎላጀጁ ሲበረታባቸውም በማሸለብ ጊዜ ከገዙ በኋላ ዕድሜያቸውን ለማራዘም አፈር ልሰው ሲነሱም እያስተዋልን ነው።

እነሆ ማስረጃችን!

ናቡከደነፆር (ቅድመ ልደተ ክርስቶስ 613 – 570 ዓ.ዓ) የባቢሎን ንጉሥ ነበር። እየሩሳሌምን ሁለት ጊዜያት የወረረው ይህ ጨካኝ፣ ሞገደኛና ሕዋሱ በእብሪት ይንቀሳቀስ የነበረው የከለዳዊነት ዝርያ ያለበት አምባገነን ገዢ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልም እንዳለመ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይተርክልናል። ታሪኩን ጨምቀን እናስታውስ።

«ናቡከደነፆር ሕልም አለመ።መንፈሱም ታወከበት። እንቅልፍም ከእርሱ ራቀ። ሕልሙን እንዲነግሩትም የሕልም ተርጓሚዎችን፣ አስማተኞችን፣ መተተኞችንና ኮከብ ቆጣሪዎችን ወደ እርሱ አስጠራ። እንዲህም አላቸው- ‹ሕልም አልሚያለሁ፤ ሕልሙንም ለማወቅ መንፈሴ ታውኳል› አላቸው። እነርሱም፡- ‹ሕልምህን ንገረን እኛም ፍቺውን እናስታውቃለን› በማለት መለሱለት። ንጉሡም በቁጣ ተሞልቶ እንዲህ አላቸው፡- ‹ሕልሙንና ፍቺውን ባታስታውቁኝ አካላችሁ እንዲቆራረጥና ቤቶቻችሁም የፍርስራሽ ክምር እንዲሆኑ እወቁቱ›…ለሁለተኛም ጊዜ መልሰው ሕልሙን እንዲነግራቸው ግድ አሉት። …ንጉሡም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡- ‹ጊዜውን ለማስረዘም እንደሆነ ገብቶኛል፤ ስለዚህ ሕልሙንና ፍቺውን ፈጥናችሁ ስላላሳወቃችሁኝ እንድትገደሉ ትዕዛዝ አውጥቼባችኋሁ። ›…ጠቢባኑም መገደል ጀመሩ። »

ይህ የቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በግላጭና በገሃድ ሲተገበር እያስተዋልን ነው። በኢትዮጵያ ላይ ተጠናክሮ እየተፈጸመ ያለው የጨካኞቹ የአሸባሪ ቡድኖች ተግባር ከሥር መሠረቱ ቢፈተሽ ከዚህ እውነታ የሚርቅ አይሆንም። አሸባሪዎቹ የሕወሓት «ግፍ ግዱ» እብሪተኞች እና ከጀርባው ያዘላቸው ብጤዎቹ ለምንድን ነው በታሪካችን ገጾች ውስጥ ተሰምቶም ሆነ ተነቦ በማይታወቅ የክፋትና የሴራ ቅንብር መከራ እያዘነቡብን ያለው? ለምንስ ነው በንጹሐን ዜጎች የደም ግብር የራሳቸውንና የሥልጣናቸው ዕድሜ ለማራዘም የሚፍጨረጨሩት? መልሱ አጭርና ግልጽ ነው። ሕልማቸውና ፍችው ተሰወሮባቸውና አስተሳሰባቸውም ቆሞ ስለቀረ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠሩት ሕልም ኖሯቸው ሳይሆን ቅዠታቸውን እየመነዘሩ በማምታታት ተክነው ነው። ከድርጅቱ ውልድት እስከ ጉልምስና እየናወዙ ያሉትም በዚሁ የቅዠት ማዕበል እየተላጉ ነው።

See also  “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ ለምን?”

ቅዠት ያባንናል፣ ከአልጋ ላይም ገፍትሮ ይጥላል። ለመሆኑ ሕወሓትና ውላጆቹ የንጹሐንን ደም በከንቱ የሚያፈሱት፣ የራሳቸውንም ጀሌዎች የሚያስጨርሱት፣ የድህነት ሀብታችንን የሚያወድሙትና ለባዕድ ቅጥረኝነት ራሳቸውን ለተዋራጅነት ያቀረቡት ለየትኛው ሕልማቸው ፍቺ ፈልገው ይሆን? የትኛውን ራእያቸውንስ ለማስፈጸም ነው? አላወቁት ከሆነ ይወቁት፡- ቅዠት ለእውር ድንብር የሌሊት መባተት መዳረጉና የጨለማ ጉዞ መሆኑን አልገባቸው ከሆነ ይግባቸው፣ አልገባ ካላቸውም ለአገር ሉዓላዊነት የሚከፈለው ሁሉ ተከፍሎ ቅዠታቸው እንደሚመክን ይወቁት። ይህ የህልውና ማስከበር ጉዳይ እንኳንም ለእኛ ለባለጉዳዮቹ ቀርቶ ለሰፊው የዓለማችን ማኅበረሰብም ውሎ አድሮ ግልጽ ስለሚሆን የታሪክ ምስክር ሆኖ በጉልህ መጠቀሱ የሚቀር አይሆንም።

የአረር ድምጽ ካልሰሙና ጭሱን ካልታጠኑ በስተቀር መኖር የማይችሉት አዛውንቶቹ የሕወሓት መሪዎችና ጀሌዎቻቸው እንኳን በእኛ ዘንድ ቀርቶ አለንላችሁ እያሉ በቅዠት ምኞት ከሚያደነባብሯቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሳይቀር ሊጠየቁ ከሚገባቸው ጥያቄዎች መካከል ዋናውና ቀዳሚው ጉዳይ «ሕልማችሁ ምንድን ነው? ራእያችሁስ ለትግራይ ሕዝብ ምን ለማስገኘት ነው? የሕልሙ ፍቺ የባህርያችሁ መለያ በሆነው የጦርነት ሱስ ስለመፈታቱስ እርግጠኝነታችሁ እስከምን ድረስ ነው?» እየተባሉ ሊሞገቱ ይገባል።

ነብየ እግዚአብሔር ዳንኤል የናቡከደነፆርን ሕልም እና የሕልሙን ምሥጢር ገላልጦ በነገረው ጊዜ በፈጣሪ ፊት ንሰሃ የገባ ለመምሰል መሞከሩ አልቀረም ነበር። «ምንትስ መንኩሳ አመሏን አትረሳ» እንዲሉ አንዴ ጥፋቱ ከፀባዖት ተቆርጦለታልና ውሎ ሳያድር የራሱን ምስል አስቀርጾ በግዛቱ ውስጥ ያሉት ዜጎች በሙሉ ላቆመው ሐውልት ወድቀው እንዲሰግዱለት በአዋጅ እንዳስገደደ እናነባለን።

ይህ የእብሪቱ ዋንጫ ገንፍሎ ከመፍሰሱ የተነሳ በቤተመንግሥቱ ሰገነት ላይ እየተንጎራደደ «እኔ በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥቴ መቀመጫ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?» እያለ ሲመጻደቅ፡- «ድምጽ ከሰማይ ወጥቶ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፣ መኖሪያህም ከምድረ በዳ አራዊት ጋር ይሆናል። እንደ በሬም ሣር ትበላለህ» ተብሎ የሕያው አምላክ የቁጣ ቅጣት እንደወረደበት ታሪኩ ይነግረናል።

እውነትም እንደተባለው ለሰባት ዓመታት ያህል ከሰዎች ተለይቶ እንደተሰደደ፤ መኖሪያውም ከምድረበዳ አራዊቶች ጋር እንደነበረና «ጠጉሩም እንደ ንስር፣ ጥፍሩም እንደ ወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ በምድረበዳ ውስጥ እንደ በሬ ሣር በላ» ተብሎ ፍጻሜው ተተርኳል (ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 3 – 4)።

See also  ጠርጥር! ጥርጣሬህንም ቢሆን ጠርጥር!

የአሸባሪው ትህነግ አኗኗርና ፍጻሜው ከዚህ ታሪክ በምን ይለያል? ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ አገር እንዲመራ ሁሉን ቻይ አምላክ ዕድል ቢሰጠውም ልክ ከላይ እንደገለጽነው ባለታሪክ በእብሪት እያቀረሸ ሕዝቡን መዘባበቻ በማድረግ መዋቅራዊ የዘረፋ ሰንሰለት ዘርግቶ ለ27 ዓመታት ያህል የግፍ ጽዋ ሲያስጎነጨን እንደከረመ ደጋግሞ ሲገለጽ ባጅቷል።

ግፍ ይዋል ይደር እንጂ ዋጋ ማስከፈሉ ስለማይቀር ይኼው ትህነግ ይሉት ጉድ ከመንበረ ሥልጣኑ ተባሮ እትብቱ ወደተቀበረት ወደ ትውልድ ቀዬው እና እየዳኸ ወዳደገበት የደደቢትና የተንቤን በረሃዎች እንደተባረረ፤ የናቡከደነፆር ታሪክ እንደሚነግረንም የክብር መጎናጸፊያውን ተገፎ እንደ መጽሐፉ ቃል እንደ በሬ «ሣር ለመጋጥ» እንደተገደደ ያልመሸበት ዜና መዋዕሉ የትናንት ትዝታችን ነው።

«ክፉን እስከ ክንፉ» መባል ቢገባውም ምህረት ተደርጎለት፣ የመጀመሪያ ጥፋቱ እንዳልታየ ታልፎለትና ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ተቆጥሮለት በይቅርታ ቢታለፍም «ያዳቆነ ሠይጣን» እንዲሉ ልቡን የደፈነው የእብሪት ሞራ ህሊናውን አሳውሮት በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ይቅር የማይባል ግፍና በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ወረራ ፈጽሞ የደረሰው እልቂትና ውድመት የሚዘነጋ አይደለም። ከአንዴም ሁለቴ ብሎም ለሦስተኛ ጊዜ የፈጸመው ሣልሳዊ ወረራም ሌላው የቡድኑ የእብሪት ጫፍ መገለጫ ነው።

እንደ «ሙት ቀስቃሽ መናፍስት ጠሪ» የሞቱ ገድሎቹን፣ የሻገቱ የትናንት «ጀብዱዎቹን» እና መወየብ ብቻም ሳይሆን እንደ ምናምንቴ ነገር ዘመኑ አንቅሮ የተፋውን «የኮሚኒስቶች መገለጫ የሆነውን የዴሞክራሲ አብዮት ፍልስፍና» የሙጥኝ እንዳለ ግባ መሬቱ ሊፈጸም የመቃብሩ ዳርቻ ላይ ተገፍትሮ የመድረሱ ምሥጢርም ሌላ ሳይሆን ይኼው የእብሪቱ ውጤት ነው።

አሸባሪው ቡድን ሕልምም ፍቺም የለውም የምንለው ለማለት ስለተፈለገ ወይንም የፕሮፓጋንዳ ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን እውነታ ስለሆነ ነው። የቅዠት ሕልሙን በተመለከተ እንኳንስ በአደባባይ ቆሞ ስለ ሕልሙ ፍቺ ለመሟገት ቀርቶ ጀርባውን ያጎበጠው የውሸት ቁስሉ ጠረን ስለማያስቀርብ የሚሻለው አንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የቡድኑን እስትንፋስ አጨልሞ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አየር እንዲተነፍስ መርዳት ነው።

ሕልሙና ራእዩ በርግጥም «ሕዝቤ» እያለ ጋሻ ላደረገው ወገን የእንቆቅልሽ መፍቻው ቢሆን ኖሮ የተዘረጋለትን የሰላም እጅ ስሞ ወደ ድርድርና ውይይት በገባ ነበር። ለወያኔና ለጀሌዎቹ እንዲህ ዓይነቱ ምክር ከእንቆቆም የመረረ ስለሚሆንባቸው እንኳንስ አክብረው ሊቀበሉት ቀርቶ ገና ሲያስቡት እያጥወለወለ ያስገዝፋቸዋል። ይህንንም ባህርያቸውን ደጋግመው በሚሰጧቸው መግለጫዎች ማረጋገጥ ይቻላል።

See also  አሜሪካና አውሮፓ ሲፈልጉ እንጂ ስንፈልግ ረድተውን አያውቁም! (በድሉ ዋቅጅራ)

«ትህነግ ኢትዮጵያን ዘርፏል» ከማለት ይልቅ «አጥንቷን ግጦ ከጨረሰ በኋላ በአጥንቱ ውስጥ ያለውን አንጥብጣቢ መቅኒ ታሪካዊ ጠላቶቿ እንዲመጡ ሲያመቻችላቸው ኖሯል» ማለቱ ይቀላል። ደግመን ደጋግመን እንደተማጠንነው የትግራይ ሕዝብ ስለምን «በቃችሁ! ሞት ሰለቸን! ልጆቻችንን ገብረን ጨረስን! ምድራችን ወደ ባድማነት ተለወጠ! ከወንድም ሕዝቦች ጋር ደም እየተቃባን እስከ መቼ እንኑር?» በማለት ለመጠየቅ ለምን ፈራ ተባ እንደሚል ግራ ያጋባል።

እርግጥ ነው የቡድኑ የእብሪት ማብረጃ የንጹሐንን ደም በማፍሰስ መፎከር እንደሚሆን አልጠፋንም። የለከፈው የበረሃ ጅኒም ያሰክነዋል ተብሎ አይታመንም። ግን እስከ መቼ? ምንስ እስከሚሆን? የትግራይ እናት የልጅ መካን የምትሆነው፣ የትግራይ አባትም በዛለ መንፈስና በጠወለገ አካሉ ተስፋ ቆርጦ በቁም የሚያነባው ምን እስከሚፈጠር ድረስ ነው? እንደምንስ የወያኔን መሪዎች ሰንጎ በመያዝ ሕልማቸውንና ፍቺውን የሚጠይቅ ጀግና ይጥፋ?

እርግጥ ነው ከቡድኑ የውልደት ጊዜ ጀምሮ «ሕልሙንና ፍቺውን» እንዲያሳውቅ ሲወተውቱ የኖሩትን በሙሉ በረቀቀ ስልትና ዘዴ፣ ገፋ ሲልም በአደባባይና በፀሐይ ፊት ሲያርዳቸውና ሲያሳድዳቸው እንደኖረ በሚገባ ይታወቃል። ከእነርሱም አልፎ ተርፎ በቤተሰቦቻቸው ላይ ሳይቀር ሕወሓት ይሉት የግፍ ቋፍ ሲያድርስ የኖረውን መከራ ሲተረክ የኖረው ልክ እንደ ጀብድ እያወራው ነበር። ግን እስከ መቼ? እኮ ምን እስከሚሆን? ምላሹን የምንጠብቀው ከትግራይ ወገናችን ነው። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከትግራይ ወንድሞቹና እህቶቹ ጎን ቆሞ ይህን የናቡከደነፆር መንፈስ ተሸካሚ የሆነውን ቡድን ግባ መሬት ለማፋጠን ኃይሉን ሊያስተባብር ይገባል። ሰላም ይሁን።

 (ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን  መስከረም 9/2015 ዓ.ም

Leave a Reply