ግንብ ተደርምሶ እናት ከህጻን ልጃቸው ጋር ህይወታቸው አለፈ

በአዲስ አበባ ጎተራ አካባቢ ለመንገድ ድጋፍ የተገነባ ግንብ ተደርምሶ መኖሪያ ቤት ላይ በመውደቁ አንድ እናት ከ7 ዓመት ህጻን ልጃቸው ጋር ህይወታቸው አለፈ።
አደጋው የደረሰው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ጎተራ ወንጌላዊት ህንጻ ጀርባ ሲሆን በቤት ውስጥ ከነበሩት ቤተሰቦች መካከል የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገልጿል።
የግንቡ መደርመስ አደጋ የደረሰው ሌሊት 10:00 ላይ ሲሆን በቤታቸው ተኝተው የነበሩ የ35 ዓመቷ እናት ከ7 ዓመት ህፃን ልጃቸው ጋር ህይወታቸው አልፏል።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ፤ የግንቡን መፍረስ ተከትሎ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተኝተው የነበሩ ወገኖች ወድቆባቸው መሞታቸውን ገልጸዋል።
የመኖሪያ ቤቱ የሚገኘው ከግንቡና ከመንገዱ ጠርዝ አምስት ሜትር ገደማ  እርቆ በመሆኑ የፈረሰው ግንብ የወደቀበት መሆኑን ገልጸዋል።
የአደጋ  ጊዜ ሰራተኞቻችና የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም የጸጥታ አባላት የሟቾችን አስከሬን ከፍርስራሽ  ውስጥ ማውጣት መቻላቸውን አቶ ንጋቱ ተናግረዋል።
በአደጋው በቤቶች ውስጥ የነበሩ  አራት ሰዎች ከአደጋው  እራሳቸውን ማትረፍ ችለዋልም ነው ያሉት።
በደረሰው አደጋ ሶስት መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ታውቋል።
ህብረተሰቡ የአደጋ ተጋላጭነቱን ለመቀነስ የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሚሰጣቸውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በአግባቡ እንዲተገብር ተጠይቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

See also  "እብድ ውሻን ማባረር ከእብድ ውሻ ስጋት ነጻ አያደርገም" የአማራ ክልል

Leave a Reply