“በጩኸት እና በጫጫታ የአማራ ክልል መንግስትን በማዳከም አማራውን ነጻ ማውጣት አይቻልም”

ችግርን በአንድ ፐርሰንት ለመቀነስ መንቀሳቀስ ግን ዳገት ያስወጣል፣ ቁልቁለት ያስወርዳል። ስለሆነም እነማን ለምን እና ለማን ነው የሚናገሩት ብለህ ጠይቅ። ራስህን ከአልፎ ሂያጅ ጠብቅ። አልፎ ሂያጁ ሁሉ ፖለቲካህን የሚያቦካበት ምክንያት ምንም አይደለም የአንተ አለመጠየቅ እንጅ። ከግርግር ምንም ማትረፍ አይቻልም። ቀደም ብዬ እንዳልኩትም በጩኸት እና በጫጫታ የአማራን ፖለቲካ ማዳከም ለተቀናቃኝ ኃይሎች ትጥቅ እና ስንቅ እንደማቀበል ያለ ነው። መንግስት መቀየር ካለበትም በተደራጅ እና በተቀናጀ ትግል እንጅ እንደ እያሪኮ በጩኸት መሆን የለበትም። እኔ ይህን የምልህ ከመሬት ተነስቸ አይደለም። በ1966 ልጆችህ የንጉሱን ስርዓት ገንድሰው ደርግን የመሰለ ጨካኝ ከመትከል በቀር አንተን የሚመጥን ስርዓት አላበጁልህም። በ1983 ተወካይ እንኳን ሳይኖርህ የተደራጁት ሁሉ የሚጫወቱብህ የዳማ ጠጠር ከመሆን አልዳንክም። በ1997 ልጆችህን ገብረህ ትግልህ ከመደፈቅ አልዳነም። በ2008 ያን ያክል እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገህ ያገኘኸው ውጤት አሁን ያለው ነው።

Gashaw Mersha

በነገራችን ላይ በጩኸት እና በጫጫታ የአማራ ክልል መንግስትን በማዳከም አማራውን ነጻ ማውጣት አይቻልም። የአማራ ክልል መንግስት በአግባቡ የማይሰራ ደካማ መንግስት መሆኑ እሙን ነው። አስፈላጊ ስላልሆነ እንጅ ለዚህ ደካማነቱ ስረ መሰረቶቹን መዘርዘር ይቻላል። ቦታው እና ጊዜው እዚህ ላይ ስላልሆነ ደካማነቱ ላይ ተነጋግረን ካለፍን በቂ ነው። የሆነው ሆኖ ባልተቋረጠ እና በተጠና መልክ የአማራ ክልል መንግስትን ደካማ እና የእለት ከእለት ስራውን እንኳን ተረጋግቶ እንዳይሰራ በማድረግ እና አድርጎ በማቅረብ ህዝባችን መጥቀም ይቻላል ብሎ ማሰብ ፖለቲካን ያለማወቅ ማሳያ ነው። የፉክክር ፖለቲካ ባረበበበት ሜዳ የአማራን መንግስት ለብቻው ኮስማና አድርጎ ሌላውን ሰማይ ላይ በመስቀል ሽንፈት እንጅ አሸናፊነት አይመጣም። የእስካሁኑ አካሄዳችንም ለብልህ ጥሩ ትምህርት ይሆናል።

የአማራ ህዝብ በመላ ሐገሪቱ ችግር ላይ ነው። ይኸ ፀኃይ የሞቀው ሐገር ያወቀው ሐቅ ነው። ይህ ችግር ግን በአንድ ጀንበር የመጣ አይደለም። መፍትሄውም በኪስ የተቀመጠ ስላልሆነ በአንድ ጀምበር የሚመጣ አይደለም። የአማራ ህዝብ ችግር የሚፈታው ወዳጅን በማብዛት፣ ጠላትን በመቀነስ፣ ተናቦ በመስራት እንጅ ከተማ ለከተማ በማውደልደል፣ በዩቱብ እና በሶሻል ሚድያ በመንጫጫት አይደለም። አንዳንዱ ሰው ይህን መሰሉ መራራ ሐቅ ሲነገር አይጥመውም። እንዲያውም መንግስትን ለመታደግ ምናምን እያለ ሊለፋደድ ሁሉ ይችላል። ከዚህ ቀደም እንዳየነው መንግስትን መጣል እጅግ ቀላል ስራ ነው። ህወሐትን የሚያክል ግድንግድ መንግስት ገንድሰን አይተነዋል። መንግስትን ከጣልን በኋላ እጃችን ላይ ምን አለ የሚለው ጉዳይ ነው ዋናው ቁምነገር። በተደጋጋሚ መታሰብ ያለበት ቁምነገር ባልተደራጀ ጩኸት እና ሑካታ የአማራን ክልል መንግስትን ካፈረስን በኋላ በእጃችን ምን አማራጭ ይዘናል የሚለውን አስበንበታል ወይ ነው? ነገሩን ወደ አማራ ብቻ ያወረድኩት የሌሎች ክልል ፖለቲካ ችግር ቢኖርበትም እንኳ ቢያንስ በሚድያ ጫጫታ እና ሁካታ ሲናጥ ስለማናስተውለው ነው። ችግሩ ግን ሁሉም ጋ ያለ ነው።

See also  ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የበርበራ ወደብን አልምቶ የመጠቀም ስምምነታቸውን አጸኑ

የአማራ ህዝብ ጠንካራ ሰራተኛ ህዝብ ነው። ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መስተጋብር ፈጥሮ በመላ ሐገሪቱ የሚኖር ህዝብ ነው። አሁን አሁን ግን በሚድያ በሚነገር የተጋነነ ትርክት አማራው ተቅበዝባዥ፣ ጠበቃ አልባ፣ ሊጠፋ የተቃረበ አስመስሎታል። በእርግጥ በየ አቅጣጫው ያለውን ጫና አጥቸው አይደለም። ይሁን እንጅ ነገሩ የሚስተካከለው መሬት ላይ በወረደ የተደራጀ ትግል እንጅ እዚሁ ሶሻል ሚድያ ላይ በመጯጯህ አይደለም። አንዳንዴ ስንናገር እና ስንፅፍ በእለቱ ከሚሰጠን እርካታ እና ድጋፍ ባለፈ ነገ ከነገ ወዲያ ለሚመጣው ትውልድ ምን አሉታዊ ችግር ይዞ ይመጣል ብለን ማሰብ ይኖርብናል። በዩቱብ እና በሶሻል ሚድያ በላይ በላዩ በሚዘንብበት የተበዳይነት ትርክት አማራው በስነ ልቦና የተሰለበ ትውልድ እንዳያፈራ እሰጋለሁ። ከሞት ሁሉ ትልቁ ሞት የስነ ልቦና መጎዳት ነው። ከዚህ አንጻር የትግራይ ብሔርተኞች ፅናት እጅጉን ይደንቀኛል። ምንም እንኳን የምንታገላቸው ቢሆኑም ፅናታቸውን እና ቁርጠኝነታቸውን አለማድናቅ ግን አይቻልም።

ቀደም ብለን እንዳልነው ህዝባችን ችግር አለበት። ይህ ችግር ግን የሚቆመውም ሆነ የሚታገሰው በመራራ ትግል ብቻ ነው። የህዝብን በደል በቃላት አሽሞንሙኖ፣ በውብ ፊደላት ቀምሮ ማቅረብ ቀላል ስራ ነው። እንዲያውም ሰነፎች የሚሰሩት የማዕድ ቤት ፖለቲካ ነው። እውነት እውነቱን ተነጋግሮ፣ ችግርን አስተካክሎ፣ በጋራ ቆሞ ችግርን መጋፈጥ ግን ድፍረትን የሚጠይቅ ነገር ነው። መፍትሄ የሚገኘውም ከመራራው ትግል እንጅ ከመራራው ጩኸት ስር አይደለም። አንዳንዱ ዩቱቡ ይታይለት እንጅ የምሰራው ዜና ምን መዘዝ ይዞ ይመጣል ብሎ የሚያስብበት፣ ነገን ተመልሶ የሚያይበት አንገት የለውም። በትውልዱ ላይ የተበዳይነት ናዳ በላይ በላይ ከማፍሰፍ በቀር የመፍትሄ ሰበዝ ሲመዝ አይታይም።

በነገራችን ላይ ይህን ሁሉ ስድብ እና ዛቻ ችለን ለህዝባችን ያስፈልገዋል የምንለውን የምንናገረው የነገው የከፋ እንደሆነ ስለምናውቅ ነው። ህዝቤ ሆይ ስማኝ፣ ችግርህን በቃላት አጣፍጦ መናገር ቀላል ጉዳይ ነው። ሰከን ብለህ አስበው እስቲ የችግር ዜና መስራት ምኑ ይከብዳል። ችግርን በአንድ ፐርሰንት ለመቀነስ መንቀሳቀስ ግን ዳገት ያስወጣል፣ ቁልቁለት ያስወርዳል። ስለሆነም እነማን ለምን እና ለማን ነው የሚናገሩት ብለህ ጠይቅ። ራስህን ከአልፎ ሂያጅ ጠብቅ። አልፎ ሂያጁ ሁሉ ፖለቲካህን የሚያቦካበት ምክንያት ምንም አይደለም የአንተ አለመጠየቅ እንጅ።

See also  እስራኤል "በእጆቻችን ያሉትን የሉዓላዊነት ሥልጣኖች እንጠቀማለን"-ግጭት ወደ ሙሉ ጦርነት እንዳያመራ ተሰግቷል

ከግርግር ምንም ማትረፍ አይቻልም። ቀደም ብዬ እንዳልኩትም በጩኸት እና በጫጫታ የአማራን ፖለቲካ ማዳከም ለተቀናቃኝ ኃይሎች ትጥቅ እና ስንቅ እንደማቀበል ያለ ነው። መንግስት መቀየር ካለበትም በተደራጅ እና በተቀናጀ ትግል እንጅ እንደ እያሪኮ በጩኸት መሆን የለበትም። እኔ ይህን የምልህ ከመሬት ተነስቸ አይደለም። በ1966 ልጆችህ የንጉሱን ስርዓት ገንድሰው ደርግን የመሰለ ጨካኝ ከመትከል በቀር አንተን የሚመጥን ስርዓት አላበጁልህም። በ1983 ተወካይ እንኳን ሳይኖርህ የተደራጁት ሁሉ የሚጫወቱብህ የዳማ ጠጠር ከመሆን አልዳንክም። በ1997 ልጆችህን ገብረህ ትግልህ ከመደፈቅ አልዳነም። በ2008 ያን ያክል እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገህ ያገኘኸው ውጤት አሁን ያለው ነው።

ህዝባችን እና ባለ ድርሻ አካላት ሰከን ብለን ችግራችን ዘርዝረን አውጥተን መፍትሄውን አብረን ማበጀት ይጠበቅብናል። ፖለቲካችን በሌሎች ተገማች እና አልፎ ሂያጁ ሁሉ የሚያቦካው እንዳይሆን ሚስጥራዊነቱን መጠበቅ አለበት። የአማራ ፖለቲካ ለሐገራችን አላባ እንዲሆን እንጅ በየጊዜው በሚነሳ ግርግር ለሐገር ተጨማሪ እዳ እንዳይሆን መስራት ከፖለቲካ ማህበረሰቡ የሚጠበቅ የቤት ስራ መሆን አለበት። አሁን እንደሚታየው አይነት አውት ሶርስ የተደረገ የሚመስለው የአማራ ፖለቲካ በባለቤትነት መመራት አለበት። እውነት ለመናገር አብዛኛው ችግራችን የሚመነጨው ከራሳችን ነው። ወደ ሌሎች ጣታችንን ከመቀሰራችን በፊት ራሳችንን እና ፖለቲካችንን እናዘምን እላለሁ።

ማሳሰቢያ:- ምንም አይነት ሐሳብ ሲነሳ ስድብ የሚቀናችሁ ወንድሞች አባካችሁ አድቡ። ስድቡ ምንም የሚያመጣብን ችግር የለም። ፖለቲካችን በሌሎች አይን ሲታይ የስድብ እና የአሉቧልታ ስዕል እንዳይኖረው ግን ያሰጋኛል።

Leave a Reply