“ትህነግ እደራደራለሁ ቢልም ለሌላ ጦርነት መዘጋጀቱ አይቀርም”  

አሸባሪው ትህነግ ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው ቢያሳውቅም ከበስተጀርባው ለሌላ ጦርነት መዘጋጀቱ የማይቀር መሆኑን የቀድሞ ሠራዊት አባል እንዲሁም የዲያስፖራ ምክር ቤት መስራችና አባል የሆኑት ኮር ዳዊት ጌታሁን አስታወቁ።

ኮር ዳዊት ጌታሁን ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ትህነግ ካለጦርነት መኖር የማይችል ድርጅት ነው። በተለይ የጁንታው አመራሮች ራሳቸውን ማዳንና ዳግመኛ ሥልጣናቸውን ለማግኘት የሚችሉት በጦርነት ውስጥ ሲኖሩ በመሆኑ በሃሰት ለሰላም የተዘረጋ እጃቸው ለሌላ ጦርነት መዘጋጀቱ የማይቀር ነው።

‹‹በመሰረቱ መንግሥት ለእነሱ የሰጠውን እድል ለማንም አልሰጠም። ንብረታቸውም ሆነ ሀብታቸው አልተወረሰም፤ ወህኒ አልገቡም፤ በሰላም እንዲኖሩ እድል ተሰጥቷቸው ነበር›› ሲሉ ያስታወሱት ኮር ዳዊት፤ ይሁንና የትህነግ አመራሮች ዳግመኛ ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ መላውን የትግራይ ሕዝብ በጦርነት ውስጥ መማገዳቸውን አመልክተዋል።

እንደእሳቸው ማብራሪያ አሸባሪው ትህነግ ከሥልጣን ዘመኑ ጀምሮ ውጊያውን ለመክፈት የሚያስችለውን ስራ አስቀድሞ በደንብ ሰርቷል። ላለፉት 27 ዓመታት በጎሳ ሀገሪቱን መከፋፈሉን አብሮ ይኖር የነበረውን ሕዝብ ልዩነቱ ላይ ብቻ እንዲያተኩር አድርጓል። ኦሮሞው ከአማራው እንዳይናበብ፤ የትግራይን ታላቅነት መንገር፤ በሃይማኖት ሳይቀር መቃቃር እንዲፈጠር ሴራ ጠንስሷል። አሁን ላይ ለዓመታት ሕዝቡን ያስታቀፈው የጥላቻ መርዝ ተፈልፍሎ ሀገር በማተራመስ ላይ ይገኛል።

‹‹አሁን የመከላከያን አቅም ሳያውቀው ቀርቶ አይደለም እየተዋጋ ያለው። ሊያሸንፍ እንደማይችል በደንብ ያውቃል። ግን ደግሞ የእነሱን ሥልጣን ለማስቀጠል ሲል የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ቢያልቅ ደንታ ስለሌለው ነው›› ያሉት ኮር ዳዊት ከዚህም ባሻገር የትህነግ መሪዎች በሕይወት የቆየ ሕዝብ ካለ ‹‹ለምን?›› ብሎ ይጠይቀናል ብለው ስለሚሰጉም ሕዝቡን በጦርነት እየማገዱ መሆኑን አንስተዋል። አክለውም ‹‹በመጀመሪያ ልጆቻቸውን ወስደው አስጨፈጨፉ፤ አሁን ደግሞ እናትና አባቶቻውን አዘመቱ። ይህንን የሚያደርጉት ‹‹ልጆቻንን የታሉ?›› ብለው እንዳይጠይቋቸው ማለቅ ስላለባቸው ነው›› በማለት አብራርተዋል።

‹‹አሸባሪው ትህነግ ሁልጊዜም ቢሆን ሕዝብ በገፍ ካስጨፈጨፈ በኋላ እንደራደር ነው የሚለው›› በማለት ተናግረው ከዚህ ቀደም ሲሸነፍ ‹‹ስልታዊ ማፈግፈግ››፤ አሁን ደግሞ ‹‹ለአማራው ሰላም ስንል ለቀን ወጣን›› በማለት ሕዝብን ለማደናገር የሚያደርገው ጥረት መኖሩን አስረድተዋል። በተመሳሳይ ለአለም ሕብረተሰብ ሰላም ፈላጊ መስሎ በተለያዩ ጊዜ መግለጫዎች ቢያወጣም የኖረበትና የጦርነት ወዳድነት ማንነቱን በቀላሉ የሚተው አለመሆኑን መረዳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

See also  ነዳጅ? ግሪክና ቱርክ አለመግባባታቸውን በሰላም እንዲፈቱ አሜሪካ ጥሪ አቀረበች

‹‹ድርድር መልካም ቢሆንም ከሕወሓት ጋር የሚደረግ ድርድር ሀገሪቱን ስጋት ውስጥ ይከታል ብዬ ነው የማምነው። ቢሆንም እንኳን ዋነኛ መደራደሪያ መሆን ያለበት እነዚህ ሰዎች ወንጀለኞች ስለሆኑ ለሕግ ራሳቸውን አሳልፈው መስጠት ሲችሉ ብቻ ነው›› በማለት ኮር ዳዊት አቋማቸውን አስቀምጠዋል። ይህንን ሁሉ ሕዝብ አስጨፍጭፈው በሰላም ሊኖሩ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም ሲሉም አፅዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

እንደኮር ዳዊት ገለፃ፤ ትግራይ ነፃ የምትወጣው እነዚህ ሰዎች ለፍትህ ሲቀርቡ ነው። ኢትዮጵያም ሰላሟ የሚጠበቀው ወንጀለኞቹ በሕግ ጥላ ስር ሲሆኑ ነው። እነሱ ድርድር የሚሉት ልክ ሲወቀጡና የማጥቂያ እድሉን ሲያጡ ነው። አሁንም የተስማሙ የመሰሉት ሴራቸውን ለመፈፀም፤ የውጭ ድጋፍ ለማግኘት አየር ለመሳብ ነው። ይህንን ሲሉ ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጁ መሆኑን ማጤን ይገባል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን መስከረም 28 ቀን 2015 ዓ.ም

Leave a Reply