ስለአስገድዶ መድፈር ወንጀል ድርጊት እና ቅጣቱ ምን ያህል ያውቃሉ?

ይህ “ይህን ያውቁ ኖሯል” በሚል ግንዛቤን ይፈጥራሉ ብለን በመረጥናቸው የህግ ጉዳዮች ላይ አጭር መረጃ የምናቀብልበት አምድ ነው፡፡

በዛሬው የ”ይህን ያውቁ ኖሯል” አምዳችን የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን በተመለከተ የወንጀል ህጉ የደነገገውን ድናጋጌ እና ድርጊቱን ፈጽሞ በተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ ስለሚጣለው ቅጣትን ይመለከታል፡፡

በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ ምዕራፍ ሁለት ርዕስ አምስት ስር በመልካም ጠባይና በቤተዘመድ መካከል የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚመለከት ከተደነገጉት እና በግብረ ሥጋ ነጻነት እና ንጽህና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ከሚመለተው ርዕስ ስር ካሉ ድንጋጌዎች መካከል የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል አንዱ ሲሆን በአብዛኛው ሴቶች እና ወንድ ህጻናት የዚህ በደል ተጠቂ ናቸው።

አስገድዶ መድፈር ወንጀልን የሚደነግገው የወንጀል ህጉ አንቀጽ 620 የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን ሲደነግግ “ማንም ሰው የኃይል ድርጊት በመጠቀም ወይም በብርቱ ዛቻ ወይም ህሊናዋን እንድትስት በማድረግ ወይም በማንኛውም ሌላ መንገድ ራሷን እንዳትከላከል በማድረግ ከጋብቻ ውጭ ከአንዲትን ሴት ጋር የግብረ ሥጋ በደል የፈጸመ ግለሰብ ከ 5 አመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል ።

ቅጣቱ ከብዶ እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችልበትን ምክንያት በአንቀጽ 620 ንዑስ ቁጥር 2 እና ተከታዮቹ ላይ የዘረዘረ ሲሆን እነዚህም የቅጣት ማክበጃ ምክንያቶች:-

1/ ወንጀሉ የተፈጸመው ከ13 ዓመት በላይ ሆና 18 ዓመት ያልሞላት ልጅ ላይ እንደሆነ
2/ በደፋሪው መሪነት፣ ቁጥጥር ወይም ሥልጣን ሥር ባለ እንደ ሕክምና ቦታ የትምህርት እና የማረሚያ ቦታዎች ላይ በምትገኝ ሴት ወይም በደፋሪው ጥገኝነት ወይም ቁጥጥር ስር ባለች ሴት ላይ የተፈጸመ እንደሆነ
3/ በአዕምሮ ሕመም ምክንያት ወይም በሌላ በማናቸውም ምክንያት የድርጊቱን ምንነት እና የሚያስከትለውን ውጤት ለማወቅ የማትችል ሴት ላይ የተፈጸመ እንደሆነ
4/ አስገድዶ መድፈሩ የተፈጸመው በማሰቃየት ወይም ቁጥራቸው ከ አንድ በላይ በሆኑ ወንዶች በህብረት የተጸመ እንደሆነ ቅጣቱ ከብዶ ከ 5 ዓመት እሰከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያሰቀጣ ይደነግጋል።

See also  በ60 ዓመቱ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈፀመዉ ግለሰብ የእድሜውን አመሻሸ ማረሚያ ቤት አድርጓል፡፡

እንዲሁም ቅጣቱ እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ የሚችለው አስገድዶ መድፈሩ ተበዳዩዋ ላይ ከባድ የአካል ወይም የአዕምሮ ጉዳት ወይም ሞትን ያስከተለ እንደሆነ ነው።ይህ ሆን ተብሎ የተፈጸመን የግድያ ወንጀል የሚያካትት እንዳልሆነ ልብ ማለት የሚገባ ሲሆን ይህ ሆኖ ከተገኘ ድርጊቱ በተደራራቢ ወንጀል የሚያስጠይቅ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል በአስገድዶ መድፈር ወንጀሉ ምክንያት ተበዳዩዋ ያረገዘች እንደሆነ ወይም ወንጀለኛው በበሽታ መያዙን እያወቀ ተበዳይን በበሽታው ያስያዘ እንደሆነ ወይም ተበዳዩዋ ወይም ተበዳዩ ከደረሰበት ከባድ ሀዘን ወይም ጭንቀት ወይም ሀፍረት ወይም ተስፋ መቅረጥ የተነሳ ራሷን/ራሱን የገደለች/ለ እንደሆነ ድርጊት ፈጻሚው ቅጣቱ ከብዶ ከ 5 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል።

በመሆኑም ይህንን በሚገባ ተረድቶ እራስን ከወንጀል ተጠያቂነት ለማዳን እንዲሁም በዚህ አይነት ወንጀል ምክንያት ለአካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት የሚጋለጡ ወገኖቻችንን ከዚህ ጉዳት ለመጠበቅ ሃላፊነታችንን እንወጣ፡፡

Ministry of justice

Leave a Reply