የአዋሳ ዩኒቨርስቲ ድልድይ ከመውደቁ አወዳደቁ!

አንድ ግንባታ በንድፍ ችግር (Design Failure), በግንባታ ቁሳቁስ ጥራት ማነስ (Material Failure), በግንባታ ጥራት ችግር (Construction Failure) ወይንም ከአጠቃቀም ችግር (Misuse) ሊከሰት ይችላል። ከዚህ የተነሳ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነቱን የሚወስደው ነዳፊው (Designer), ሥራ ተቋራጩ (Contractor), አማካሪው (Consultant) ወይንም አስተዳዳሪው (Administrator) ሊሆኑ ይችላሉ። ይህንን ማረጋገጥ ያለበት ገለልተኛ የባለሙያዎች ምርመራ ብቻ ነው።

By አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን – Dire tube

የአዋሳ ዩኒቨርስቲ ሁለቱን ግቢ እንዲያገናኝ ታስቦ የተገነባው የብረት ድልድይ በዛሬው እለት በመውደቁ የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን እና በሌሎች ተማሪዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ልብን በሚሰብር ኀዘን ሰምተናል።

የሞተውን ነፍሱ በሰላም እንድታርፍ፤ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በፍጥነት እንዲያገግሙ እመኛለሁ። ይህ ያልተጠበቀ ክስተት ተማሪዎች መረበሻቸው ወላጆች መጨነቃቸው የሚጠበቅ ቢሆንም ያለፈውን መመለስ ስለማንችል ሁሉም ተማሪዎች ተረጋግተው ፈተናቸውን እንዲፈተኑ ማረጋጋት ይጠበቅብናል።

ከዚህ በተረፈ ግን አደጋውን መሸፋፈኑን ወይንም ማጋነኑን ትተን በጥንቃቄ በመመርመር ይህን የመሰለ ጉዳት ደግሞ እንዳያገኘን ሙያዊ መድኃኒት እንድናገኝ ሙያዊ ምርመራ ማድረግ ይገባል እላለሁ።

በጥቅሉ አንድ ግንባታ በንድፍ ችግር (Design Failure), በግንባታ ቁሳቁስ ጥራት ማነስ (Material Failure), በግንባታ ጥራት ችግር (Construction Failure) ወይንም ከአጠቃቀም ችግር (Misuse) ሊከሰት ይችላል። ከዚህ የተነሳ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነቱን የሚወስደው ነዳፊው (Designer), ሥራ ተቋራጩ (Contractor), አማካሪው (Consultant) ወይንም አስተዳዳሪው (Administrator) ሊሆኑ ይችላሉ። ይህንን ማረጋገጥ ያለበት ገለልተኛ የባለሙያዎች ምርመራ ብቻ ነው።

በሌሎች ሀገሮች ይህንን የመሰለ አደጋ ሲከሰት በፍጥነት የባለሙያዎች ፓናል በመመሥረት በዝርዝር የሚጠና ሲሆን ለጉዳቱ ኃላፊነት የሚወስደውን አካል ከመለየት ባሻገር “እንደ ሀገር ምን ተማርንበት?” ብለው በመጠየቅ አዳዲስ ንድፈ ሐሳቦችን፣ ኀልዮቶችን እና ቀመሮችን ያስተዋውቁበታል።

የተወሰኑ ተመሳሳይ አብነቶችን ከዓለም ዙሪያ በአጭር በአጭሩ እንመልከት።

1) ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ድልድይ
(ሚያሚ – አሜሪካ)

ኮሌጁን ከተማሪዎች መኖሪያ እንዲያገናኝ ታስቦ “accelerated bridge construction” በሚባል የግንባታ ዘዴ የተገነባው የእግረኛ መተላለፊያ ድልድይ ለመገጣጠም ስድስት ሰአታት ብቻ ነበር የፈጀው።

See also  ወያኔያዊ አማራነትን አማራ "አማራ ነኝ"

የድልድዩ ንድፍ ደረጃ አምስት አውሎ ንፋስን እንዲቋቋም እና ለ100 ዓመታት እንዲያገለግል ታስቦ ቢዘጋጅም እድሜው ግን አንድ ሳምንት ሳይደፍን በ6ኛው ቀን በመውደቁ 6 ሰዎችን ገድሎ፣ ዘጠኝ ሰዎችን አቁስሎ፣ ስምንት መኪናዎችን ደፍጥጧል።

በኋላ በጥናት እንደተረጋገጠው ችግሩ የንድፍ ጉድለት ጋር የተያያዘ ነበር።

2) ኒለም ሸለቆ – ድልድይ
ካሽሚር – ፓኪስታን

በፓኪስታኗ ካሽሚር ግዛት በካሽሚር ወንዝ ላይ ከእጨት የተገነባ ድልድይ በአንድ ጊዜ ከአራት ሰው በላይ መሸከም እንደማይችል ማስጠንቀቂያ ተለጥፎበት ነበር።

በፈረንጆቹ 2018 ፋይሲላባድ እና ላሆሬ ከተባሉ የግል ኮሌጆች ለልምድ ልውውጥ የተሰባሰቡ የሕክምና ተማሪዎች በድልድዩ ላይ የተለጠፈውን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለው 20 በመሆን በቡድን ፎቶ ሲነሱ ድልድዩ በመውደቁ አምስት ተማሪዎች ወዲያው ሲሞቱ ሃያ ተማሪዎች በወንዙ ተወስደው ጉዳት ደርሶባቸዋል።

3) ባውቺ ድልድይ
ባውቺ – ናይጄሪያ

በናይጄሪያ ATBU ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ማደሪያን ከመማሪያ ክፍሎች (Lecture Halls) እንዲያገናኝ ታስቦ ከብረት የተሠራው ዩኒቨርሲቲው ድልድይ በፈረንጆቹ August 2019 በአካባቢው የጣለውን ዝናብ ተከትሎ በመውደቁ ስምንት ተማሪዎች ሲሞቱ በርካቶች የደረሱበት አልታወቀም።

4) ታኮማ – ድልድይ
(ዋሽንግተን – አሜሪካ)

በአሜሪካ ዋሽንግተን ከተማ በፈረንጆቹ 1940 ዓ.ም ተገንብቶ ለትራፊክ ክፍት ተደረገ። በዓይነቱ (በተገመደ ብረት የተወጠረ) በዓለማችን የመጀመሪያው የሆነው ይህ ድልድይ አገልግሎት መስጠት የቻለው ለአራት ወራት ብቻ ነበር። በወቅቱ በሰአት 70 ማይል በሚከንፍ ነፋስ በመመታቱ ድልድዩ በመውደቁ በርካታ የፊዚክስ፣ የሒሳብ እና የምሕንድስና ሊቃውንት ጥናት እና ምርምር አድርገውበታል። ለምሳሌ በምሕንድስናው ስለ mechanical resonance አዲስ ኀልዮት እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል።

ማጠቃለያ

በተለያዩ ጊዜያት፣ በልዩ ልዩ ሀገሮች፣ በተለያዩ ንድፎች (Design)፣ በተለያዩ የግንባታ ቁሳቁሶች (Materials) እና የግንባታ ጥበብ (Method) በተለይ ለተማሪዎች አገልግሎት የተገነቡ ድልድዮች በተለያዩ ምክንያቶች ወድቀው ጉዳት አድርሰዋል።

ጋዜጠኞች ስለመውደቁ አጋንነው ወይንም ሸፋፍነው ዜና መሥራታቸው የተለመደ ነው። ቢያንስ የዘርፉ ምሑራን ግን ስለመውደቁ ሳይሆን ስለ አወዳደቁ እንዲያጠኑ እና ከስህተታችን የምንማርበትን መድኃኒት እንዲያገኙልን እንጠብቃለን።

Leave a Reply