በባህር ዳር ፎረም ከሱዳን መሪ ጋር የጎንዮሽ ንግግር ተደረገ

ከሱዳን የሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጀነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር በጋራ ጉዳዮች መምከራቸውን፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ታላቅ ታሪክ ያላቸው አገራት በመሆናቸው ውደቀደመው መንገዳቸው እንዲያመሩ መነጋገራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስታወቁ።

ለጣና ፎረም ጉባኤ ባህር ዳር የገቡት ጀነራል አብዱልፋታህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቀባበል እንድተደረገላቸው ተገልጿል። 10ኛው የጣና ፎረም ጉባኤ በአፍሪካ የሰላም፣ ጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመክረው ስብሰባ ጎን ለጎን ባለ ስልጣኖቻቸውን ይዘው የመከሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዝርዝር ጉዳዩን አልጠቆሙምም። በጉቤው ላይ አብይ አህመድ ይህን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአየር ብክለት የፀዳ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚረዳ ፖሊሲ ቀርፃ ውጤታማ ሥራ እያከናወነች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

10ኛው የጣና ፎረም “የደኅንነት ሥጋቶችን መቆጣጠር፤ ተጽዕኖዎችን የመቋቋም አቅምን በአፍሪካ ለመገንባት” በሚል ቃል በባህርዳር እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መድረኩ የንግግር፣ የምክክርና የዕውቀት ሽግግር የሚደረግበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው ከተለያዩ ዓለማት የመጡ የተለያዩ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑ ልዩነትን ወደ ጋራ ተጠቃሚነት ለመለወጥ የሚያስችል ሀሳብ የሚንሸራሸርበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ለሁሉም የምትመች አፍሪካን ለመፍጠር አህጉር በቀል የሆነ መፍትሔ ማበጀት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

አፍሪካ የአየር ፀባይ ለውጥ፣ የሰላምና ደህንነት፣ የቴክኖሎጂና የኃይል አቅርቦት ፈተና እንደተደቀነባት አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ከፍ ያለ ሥራ እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

የኃይል አቅርቦት ልማቱ ከአገሪቱ ባለፈ ለጎረቤት አገራት የሚተርፍ ተግባር እየተከናወነበት መሆኑን በማስረዳት አፍሪካ በጋራ መልማት እንዳለባት አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና 30 በመቶ በዝናብ ላይ ጥገኛ በመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣቱን በመጥቀስ አሁን ላይ አገሪቱ ሰፋፊ የእርሻ ልማት ላይ መሰማሯቷን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ስኬት ደግሞ የተጠና የውኃ አጠቃቀምና ቴክኖሎጂን ስራ ላይ ማዋል መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በመታገዝ ባለፉት አራት ዓመታት ለመትከል ካቀደችው 20 ቢሊዮን ችግኝ በመሻገር 25 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል ከዕቅዷ በላይ ግቧን ማሳካቷን ተናግረዋል፡፡

See also  “መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ ሲሰጠው አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ በሚያስችል ቁመና ላይ ነው”

መርሃ-ግብሩ የደን መጨፍጨፍን ከማስቀረቱ በላይ የተራቆቱ መሬቶችን በደን መልሶ ለመሸፈን ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ አጋዥ የሆኑ 1 ሺህ የሚጠጉ የችግኝ ማፍያዎችን በማቋቋም 1 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር በየዓመቱ 8 ቢሊዮን ችግኝ ለማፍላት ማስቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት የአየር ብክለት ጉዳትን በመረዳቱ ከአየር ብክለት የፀዳ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚረዳ ፖሊሲ በማውጣት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ደህንነትና ቴክኖሎጂ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ጂኦ-ፖለቲካውን መሰረት ያደረገ ቴክኖሎጂ ማበልጸግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ቴክኖሎጂው የአፍሪካን እሴት ያልሳተና ፓን-አፍሪካኒዝምን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስን በማበልፀግ የፓን-አፍሪካ ዲጂታል ኢኮኖሚ እውን ማድረግም ጊዜው የሚጠይቀው ዋነኛ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የምንመኛትን አፍሪካ እውን ለማድረግ በጋራ ልንሰራ ይገባል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Leave a Reply