የትግራይ ተወላጅ የማህበረሰብ ተወካዮች”አሸባሪው የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለን ለመታገል ዝግጁ ነን”

  • በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ የማህበረሰብ ተወካዮች

”አሸባሪው የሕወሓት ቡድንን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍለን ለመታገል ዝግጁ ነን” ሲሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ የማህበረሰብ ተወካዮች ገለጹ።

አሸባሪው ሕወሓትን ማገዝ የትግራይ ሕዝብ ስቃይ እንዲራዘምና የትግራይ ወጣት አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዲከፍል ማድረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የትግራይ ሕዝብ መቼም ቢሆን በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ሕዝብ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል።

ከከተማ አስተዳደሩ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ የማህበረሰብ ተወካዮች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣትም የህወሓት ሽብር ቡድንን አውግዘዋል፤ የጥፋት ቡድኑ በቃህ ሊባል ይገባል ብለዋል።

በውይይቱ በከተማ አስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙን ጨምሮ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የአሸባሪው ሕወሓትን የጥፋት መንገድና እስካሁን ያስከተላቸውን ችግሮች የተመለከተ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ የትግራይን ሕዝብ ከአሸባሪ ቡድኑ የጥፋት በትርና ግፍ ለማላቀቅና የትግራይን ወጣቶች ከጦርነት ለማትረፍ ሁሉም የትግራይ ተወላጅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ተብሏል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች አሸባሪ ቡድኑ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ለትግራይ ሕዝብ ምንም የፈየደው ነገር የለም ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብ ከአሸባሪው ሕወሓት ያተረፈው ችግርና መከራ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሕዝቡ መሰረታዊ አገልግሎት እንኳን ያላገኘ መሆኑን አንስተዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ክልሉን በመራበት ዘመንም አመራሮቹ በወረዳና በዞን ተከፋፍለው አገር ሲዘርፉ፤ ሕዝቡን ሲያሰቃዩ ነበርም ነው ያሉት።

ቡድኑ በስልጣን ቆይታው ሌብነት፣ ዘረፋና አድሏዊ አሰራር እንዲንሰራፋ ከማድረግ የዘለለ ስራ አልሰራም ብለዋል።

ይህም በመሆኑ በአሸባሪው ሕወሓት አፈና ውስጥ ሆኖ ለሚሰቃየው የትግራይ ሕዝብ ሊደረስለትና ሊታገዝ ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም የትግራይ ተወላጆች ከመንግስት ጎን ሆነው አሸባሪውን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት መታገል አለባቸው ብለዋል ተሳታፊዎቹ።

አሸባሪው ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ከጎረቤቱ ጋር እንዳይኖር ማሕበራዊ ኪሳራ አድርሶበታል፤ መሰረተ ልማትም እንዲወድም ማድረጉን ገልጸዋል።

ሕወሓትን ማገዝ የትግራይ ሕዝብ ስቃይ እንዲራዘምና የትግራይ ወጣት አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዲከፍል ማድረግ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህ ሂደት የትግራይ ተወላጅ በአመለካከትም፣ በአስተሳሰብም ውስጡን ማጥራት እንዳለበትና ቡድኑን መታገል ይገባል ነው ያሉት።

ቡድኑ ጊዜ እያገኘ በሔደ ቁጥር የሕዝቡ ስቃይ እየተራዘመ በመሆኑ በተለይም አንዳንድ ዳያስፖራዎች ለአሸባሪው ቡድን የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያቆሙ አሳስበዋል።

የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን ጠንቀቆ የሚያውቅ፤ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ መሆኑንም ያረጋግጣልም ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታዋ ወይዘሮ ሁሪያ አሊና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ያስሚን ወሀብረቢ እንዳሉት፤ ሕወሓት የስልጣን ጥሙን ለማርካት ትውልዱን ሲያስፈጅ የኖረ ነው።

ቡድኑ ይህ አልበቃ ብሎት አሁንም የትግራይ ሕዝብ ከመከራና ስቃይ እንዳይወጣ መንግስት የዘረጋውን የሰላም መንገድ መግፋቱና ለሕዝቡ ምንም ደንታ እንደሌለው ማሳያ ነው ብለዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው የትግራይ ተወላጆች የመንግስትን ጥረት መደገፍ እንዳለባቸውና አሸባሪ ቡድኑ ችግር የሚፈጥረው በተልዕኮ እንደሆነ መረዳት አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።

አንዳንዶች የትግራይ ሕዝብና ሕወሓትን ቀላቅሎ ማየታቸው ተገቢ አለመሆኑም መታወቅ አለበት ሲሉም አክለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ባወጡት ባለ ሰባት ነጥብ አቋም መግለጫ የሽብር ቡድኑን አውግዘው፤ አሸባሪ ቡድኑ በትግራይ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው በደል እንዲያቆም እንደሚታገሉትም ወስነዋል።

የትግራይ ሕዝብና ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ምንም ግንኙነት እንደሌላቸውና የትግራይ ሕዝብ ሰላም ፈላጊ መሆኑን እንዲታወቅም በመግለጫው ተካቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን የትዊተር ገጽ ይከተሉ
https://twitter.com/PressEthio

Leave a Reply