ታምራት ላይኔ – የአማራን ሕዝብ ምን እያልከው ነው?

አማሮችን ለይቶ በመግደል ብቻ ሳይወሰን ፍጹም አጸያፊና ነውረኛ የሆነ ድርጊት ፈጸመባቸው። ከዚህም አልፎ ጎንደርና ባህር ዳርን በሮኬት ለማውደም ጥረት አደረገ፣ ይባስ ብሎም በአማራ ልሂቃን ላይ ሂሳብ እናወራርዳለን በሚል ሀሳብ ሰፊ ወረራ በማካሄድ የአማራን ሕዝብ በጅምላ ገደለ፣ ንብረቱን እንዳሻው ዘረፈ፣ የመሰረተ ልማቱን አወደመ፣ በአጠቃላይም የአማራን ሕዝብ ቅስም ለመስበር የሚችለውን ሁሉ አደረ

ሲሳይ መንግስቴ አዲሱ ዶ.ር – ነጻ አስተያየት

ታምራት ላይኔ ሆይ ወዴት እያመራህ ይሆን?!

የአማራ ሕዝብ ሆይ ከዚህ ጦርነት ምን ታተርፋለህ? በሚል ርዕስ ጽሁፍ ማዘጋጀትህን መነሻ በማድረግ የርዕዮት ሚዲያ አዘጋጅ ቴዎድርስ ጸጋዬ ቃለመጠይቅ አድርጎልህ በነበረ ጊዜ የሰጠኸውን ማብራሪያ ዛሬ አዳመጥሁት። እውነቱን ለመናገር የሰጠኸው መልስ ለአማራ ሕዝብ ከሚያስብ ሰው የቀረበ ማብራሪያ ሳይሆን ከአንድ ጠንካራ የትህነግ አመራር ወይም አባል ጋር የሚደረግ ውይይት ይመስል ነበር።

በዚህ አቀራረብህም በእጅጉ አዝኛለሁ፣ በ1989 ዓ.ም ስኳር አሸነፈው በሚል ምጸታዊ አነጋገር ተወንጅለህና አንተም በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፊት ቀርበህ ባደርግኸው ንግግር አምነህ መጸጸትህን እስከገለጽህበት ስአት ድረስ ውንጀላውን ለመቀበል በእጅጉ ከቸገራቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነበርሁ። በዛ ላይ በወቅቱ የኢህዴን ብአዴን ሊቀመንበር ስለነበርህ ለአማራ ሕዝብ መብት መከበርና ጥቅም መረጋገጥ በጽናት ትቆማለሁ የሚል እምነትም ነበረኝ።

ይሁን እንጂ ሴትና ገንዘብ አታሎህ ቃልህን በላህ፣ በአንተ መሪነት ላይ እምነት ጥለው የነበሩትን የኢሕዴን/ብአዴን አባላትን ሜዳ ላይ ጣልሀቸው። የትህነግ አመራሮችም ይህንን ድክመትህን ተጠቅመው ወደ እስር ቤት ወረወሩህ። ከዛም በካንጋሮ ፍርድ ቤታቸው የ18 አመት ጽኑ እስራት አስወስነውብህ 12ቱን አመት ቃሊቲ እንድታሳልፍ ተደረገና በአመክሮ ተፈታህ። በዚህ መሀል ስንቱ በይቅርታና ምህረት ሲለቀቅ አንተ ግን ይህን ዕድል ሳታገኝ ቀረህ።

ይኸ ሁሉ ግፍና በደል የተፈጸመብህ የኢሕዴን/ብአዴን ሊቀመንበርና የአማራ ተወካይ ከእስር ቤት ስትወጣ በፖለቲካው ትቀጥላለህ የሚል እምነት የነበራቸው ነባር የኢሕዴን/ብአዴን አባላትና ካድሬዎች ከአንተ ጎን ለመቆም ፍላጎት እንደነበራቸው አውቃለሁ፣ ሆኖም አንተ የመጽሀፍ ቅዱስ አስተማሪና የወንጌል ሰባኪ ለመሆን መዘጋጀትህን ይፋ ስታደርግ ተስፋ ቆርጠው አርፈው መቀመጥን መረጡ።

See also  “የፌደራል አወቃቀሩ የሃገራዊ ምክክሩ አጀንዳ ሊሆን ይገባል»

ይህም ሆኖ የተወሰነም ቢሆን ለአማራ ሕዝብ ሊቆረቆር ይችላል የሚል እምነትና ተስፋ ስለነበረን በዚህ ደረጃ ወርደህ የትህነግ ተላላኪ ወይም ቃል አቀባይ ትሆናለህ የሚል እምነት አልነበረንም። በእርግጥ ሶማሌ ክልል ሄደህ አማራን የሚያስጠቃ ንግግር ማድረግህን እና በደቡብ ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ስህተት መፈጸምህን ሳንሰማ ቀርተን አይደለም።

ሆኖም የሆነ ነገር በተከሰተ ቁጥር ትንሽ ጽሁፍ አዘጋጅተህ ትለቅና የርዕዮት ሚዲያ እንግዳ መሆንህን ስታዘወትር እኒህ ሰዎች (ትህነጎች) ምን ቢያስነኩት ይሆን አሁንም የእነሱን ሀሳብ ለማስተናገድ ጥረት የሚያደርገው ብየ መጠየቅ ጀመርሁ። በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው ይኸኛውንም ማብራሪያህን የተከታተልሁት፣ ማብራሪያህ ሰፊ በመሆኑ በዚህ አጭር ጽሁፌ ሁሉንም መዳሰስ አልፈልግም።

ይህም ሆኖ ከመነሻህና ከመደምደሚያህ ላይ የተወሰኑ ሀሳቦችን በማንሳት ጥያቄህን በጥያቄ መልኩ ለመመለስ እሞክራለሁ። ስታስበው ጦርነቱን የጀመረው የአማራ ሕዝብ ይመስልሀልን? ወይስ ጦርነቱ ቢመጣብህም ዝም ብለህ የጦርነቱ ሰለባ ሁን እያልኸው ይሆን? ትህነግ በእብሪት ተነሳስቶ የሰሜን ዕዝን ሲያጠቃ በተመሳሳይ ስአት የጠገዴ ወረዳ ከተማ የሆነችውን ቀራቅርን ለመቆጣጠር ሞከረ።

ከዛም አልፎ በሠራዊቱ ውስጥ የሚገኙ አማሮችን ለይቶ በመግደል ብቻ ሳይወሰን ፍጹም አጸያፊና ነውረኛ የሆነ ድርጊት ፈጸመባቸው። ከዚህም አልፎ ጎንደርና ባህር ዳርን በሮኬት ለማውደም ጥረት አደረገ፣ ይባስ ብሎም በአማራ ልሂቃን ላይ ሂሳብ እናወራርዳለን በሚል ሀሳብ ሰፊ ወረራ በማካሄድ የአማራን ሕዝብ በጅምላ ገደለ፣ ንብረቱን እንዳሻው ዘረፈ፣ የመሰረተ ልማቱን አወደመ፣ በአጠቃላይም የአማራን ሕዝብ ቅስም ለመስበር የሚችለውን ሁሉ አደረገ።

ይኸ ሁሉ ሲሆን የአማራ ፖለቲከኞችም ሆኑ የአማራ ሕዝብ በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸሙት አንዳች በደል ወይም ጥቃት አልነበረም። ታዲያ ከዚህ በላይ ምን አይነት ሁኔታ እስኪፈጸምበት ድረስ ነው ይኸ ጦርነት አይመለከተኝም ብሎ ሊቀመጥ የሚችለው? በዛ ላይ ወገኖቹ በወልቃይት፣ ጠለምትና ራያ በትህነግ አገዛዝ ሲሰቃዩና ሲገደሉ ብሎም በግፍ ሲፈናቀሉ እየተመለከተ እንዴት አያገባኝም ይበል?

ዶ/ር ዐብይ አህመድ የኤርትራ መንግስትን ጋብዞ የትግራይን ሕዝብ አስጨፈጨፈ የሚለው ሀሳብ እውነት ስለመሆኑ ጥያቄ የሚነሳበት ሆኖ አንተ የነበርህበት የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራር የኢሕዴሪ መንግስትን ለመደምሰስ በታሰበ ጊዜ የሸአብያ ሠራዊት ከኢሕአዴግ ጋር ተሰልፎ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት እየወጋ አዲስ አበባ ድረስ መምጣቱን ረስተኸው ይሆን? ወይስ አሁን ሲሆን ነው ይኸ ሁኔታ የሚገለጽልህ? ቢያንስ የምታውቀውን እንኳ አስታውስ እንጂ!

See also  ደብዳቤ ለኢትዮጵያ - ከቢልለኔ ስዩም

እንዲሁም ሸአብያ አማራን እንዴት እንደሚጠላም በምሳሌ አስደግፈህ ልትነግረን ሞክረሀል፣ መልካም ትህነግስ አማራን በጠላትነት ፈርጆ ሊያጠፋው አልሞከረምን? በ1968 ዓ.ም ባወጣው የፖለቲካ ማንፌስቶው ላይ የአብዮቱ ጠላት አማራ በመሆኑ ማህበራዊ ረፍት እንዲያጣ እናደርገዋለን መባሉ የወዳጅነት መልዕክት መሆኑ ነው? ሌላው ቀርቶ በዘፈናቸው ሳይቀር አንተ የትግራይ ጀግና አሳደህ በለው ያንን ሞኝ አማራ ብሎ ያስጨፈረው ትህነግ መሆኑን ረስተኸው ይሆን?

ሌላው የመፍትሄ ሀሳብ እንድታቀርብ ስትጋበዝ ጀነራል ጻድቃን ቃል በቃል ያለውን እንዳለ በመድገም የትግራይ ህዝብ ካሸነፈ በቀጠናው የተሻለ ነገር ይፈጠራል፣ ኢትዮጵያም ከመፍረስ ትድናለች አይነት መልስ ሰጥተሀል። እውነቱን ለመናገር መደምደሚያህ እንዲህ መሆኑን ባውቅ ኖሮ ይህን ያህል ጊዜ ሰጥቼ ላዳምጥህ አልችልም ነበር። ወይ መረገም! በእርግጥም ትህነጎችማ ያስነኩህ ነገር አለ።

ፍሪቦርግ ከተማ፣ ስዊትዘርላንድ!

Leave a Reply