መቀለ – ቀለበት ውስጥ ገባች፤ ትህነግ ሽሬና ቁልፍ ከተሞች መያዛቸውን አመነ

ራሱን የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ በሚል የሚጠራው ወገን ሽሬ በመንግስት እጅ ስር መውደቋን ብበይፋ አስታውቆ “ጀግናው የትህንግ ሃይል” ተጋድሎውን እንደቀጠለ አመልክቷል። የትግራይ ኮማንድ ይህን ይፋ ያደረገው መንግስት በትግራይ ያሉ ዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅና ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ካስታወቀ በሁዋላ ነው።

አሁን ላይ እንደሚሰማውና በምስል የተደገፉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት መከላከያ የሚመራው ጥምር ጦር በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ መቀለ መቃረቡን ነው። አላማጣ፣ኮረም፣መሆኒ፣ግራካሶ፣ማይጨውና ጨርጨር በመንግስት ሃይሎች ስራ ሆነዋል። ዋጃን የተቆጣጠረው ሃይል ከግራና ቀኝ አጥቅቶ ከመጣው ሃይል ጋር ወደፊት በመገስገስ መሆኒን ደርሷል። የትህነግ ሃይሎች የቦታ ስም ጠቅሰው ባያስታውቁም፣ መከላከያ የሚመራው ጥምር ጦር በመቀለ አርባና ሃምሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ተሰምቷል።

“ድርድር ብሎ ነገር የለም። ከማን ጋር ነው የምንደራደረው” በሚል የንግግር መድረክን እንደማይቀበሉ፣ አዲስ አበባ በሳምንት እንደሚገቡ ሲያስታውቁ የነበሩት የትህነግ መሪዎች አሁን ላይ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ቢወተውቱም መንግስት ንግግርን እንደሚፈልግ ይሁን እንጂ በትግራይ ከተሞች ያሉ የአየር ማረፊያዎችን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠርና በትግራይ ስቃይ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት ከማረጋገጥ ወደሁዋላ እንደማይል በመግለጽ ወደፊት መግፋቱን ቀጥሏል።

ጥምር ጦሩ ከባድ ማጥቃት እያደረገ ወደፊት ሲገሰግስ በርካቶች ለዳግም መፈናቀልና ሞት መዳረጋቸውን የትህነግ ሃይሎች ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። አያይዘውም “የትግራይ ሰራዊት የሞት እና የህይወት ትግል ይቀጥላል” ሲል አስታውቋል። አክሎም “በጦርነት ወቅት ከአካካቢዎች መገፋፋት ተፈጥሯዊ ነው” ካለ በሁዋላ “ኃይሎቹ ሽረ ከተማን ጨምሮ አንዳንድ አካባቢዎችን ለጊዜው ቢቆጣጠሩም የትግራይ ሰራዊት አቅሙ የፈቀደ ሁሉ እንዲታገል ” ሲል ጥሪ አቅርቦላቸዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጦርነቱን በማስቆምና ወደ ትግራይ የሚደርሰውን ሰብዓዊ እርዳታ በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማረጋገጥ ሃላፊንቱን ሊወጣ እንደሚገባም አመልክቷል። በተጨማሪም ዓለም ዓቀፉ ማህበረቡም በትግራይ እየተፈጸሙ ያሉ የአለም አቀፍ ህግ ጥሰቶችን ተረድቶ አፋጣኝ መፍትሄዎችን እንዲሰጥ ተማጽኗል።

ለትግራይ አማጽ ሃይሎች እጅግ ቅርብ የሆነው አሌክስ ዲዎል የትግራይ ሃይሎች መፈረካከሳቸውንና የሽሬ ከተማ መያዟን ከሶስት ቀን በፊት ይፋ ባደረገበት ጽሁፉ ቃል በቃል ባይገልጽም የትህነግ ዳግም ተደራጅቶ የመዋጋት አቅም ወደ ዜሮ ደረጃ መድረሱን ጠቅሶ ነበር። የሽሬ ከተማ መያዝ ከስትራቴጂ አንጻር ለትህነግ ሃይሎች ታላቅ ኪሳራ እንደሆነ በርካቶች አስታውቀዋል። መንግስት ሽሬንም ሆነ ማናቸውን አካባቢዎች ዳግም ስለመያዙ በይፋ ያለው ነገር የለም። ይልቁኑም “አማጺና ህገወጥ” ሲል የሚጠራው አካል በትግራይ አንዳችም ቦታ የማስተዳደር ህጋዊ ውክልና ማንዴት ስለሌለው ካሁን በሁዋላ ትህነግ ትግራይ ውስጥ ነጻ የመደራጃ ስፍራ እንደማይኖረው ነው።

አቶ ጌታቸው ሽሬ ልትያዝ በቋፍ ላይ እያለች በሰጡት መግለጫ አዲ አርቃይና አዲ ጎሹ ላይ ሃይላቸው ከባድ ምት አሳርፎ በድል እንደትወጣ አመልክተው ነበር።

መንግስት በትግራይ ከተሞች የሚገኙ የአየር ማረፊያዎች የፌደራል መንግስት ንብረት በመሆናቸው ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠራቸው ይፋ ባደርገው መሰረት ከመቀለና አክሱም በስተቀር ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ እጁ አድርጓቸዋል።

ይህ በንዲህ እንዳለ በትግራይ የተቋረጡ አገልግሎቶችን ለማስጀመር በሁሉም አቅጣጫ ባለሙያዎችና አስፈላጊ ቁሳቁሶች ከጥገና መርሃ ግብር ዝግጅት መጠናቀቁ ታውቋል። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አካላት እንደሚሉት አሁን በትግራይ ያለውን የእህል፣ መድሃኒትና የመሳሰሉትን ችግሮች ለመቅረፍ መንግስት ለዓለም ህብረትሰብም ሆነ ለዓለም ዓቀፍ የርዳታ ተቋማት የተቆጣጠራቸውን አየር ማረፊያዎች ለመክፈት ዝግጅት ማደረጉ ተሰምቷል።

You may also like...

Leave a Reply