መንግስት በትግራይ የተቋረጠውን አገልግሎት ሊያስጀምርና ርዳታ ሊያቀርብ መሆኑን ይፋ አደረገ

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ አቅርቦት እና አገልግሎት ማስጀመርን በተመለከተ ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል ከሰሞኑ የተወሰኑ ከተሞች መቆጣጠሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።

አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ÷ ሰራዊቱ በከተሞች አካባቢ ውጊያን ለማስወገድ ጥረት ማድረጉንም አውስቷል።

በዚህም ንጹሃን እንዳይጎዱ ያደረገው ከፍተኛ ጥረት እንደተሳካላት ያነሳው መግለጫው፥ ሰራዊቱ አሁን ላይ ሽረ፣ አላማጣ እና ኮረም ከተሞችን ያለ ከተማ ውጊያ መቆጣጠር መቻሉን አመላክቷል።

ሰራዊቱ አንዳንዶች የአሸባሪውን ህወሓት ፕሮፓጋንዳ በማስተጋባት የተነበዩትን መጥፎ ሁኔታ ማስቀረት መቻሉንም ነው ያነሳው።

የኢትዮጵያ መንግስትም በሰራዊቱ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ስፍራዎች ከሚመለከታቸው ረጂ ድርጅቶች ጋር በትብብር ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ገልጿል።

በተጨማሪም ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የሰብአዊ ድጋፎች የሚቀርብባቸውን መንገዶች ለማስፋት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቅሷል።

መግለጫው ከሰሜን ጎንደር እስከ ሽረ ያለውን ጨምሮ ከኮምቦልቻ – ደሴ – ወልዲያ – ቆቦ – አላማጣ መንገድን ለመክፈት አስፈላጊው ሁሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን አንስቷል።

የሚደረገው ዝግጅት ቴክኒካዊ ዳሰሳና ምዘናዎችን ጨምሮ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች አገልግሎቶችን ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያስፈልጉ ሥራዎችን ያካትታል ነው የተባለው፡፡

You may also like...

Leave a Reply