ከባድ የሙስና ወንጀልና አስገድደው የደፈሩ የፖሊስ አመራራን አበረቻቸው ተከሰሱ

ዐቃቤ ህግ በአዲስ አበባ ፖሊስ የአየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ሀላፊን ጨምሮ ስልጣናቸውን አላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና እና አስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈፅመዋል ባላቸው 3 የፖሊስ አባላት እና ግብረአበሮቻቸው ላይ ክስ መሰረተ፡፡

ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተው 1ኛ ተከሳሽ ም/ኢንስፔክተር መንግስቱ ገብረሚካኤል አልባሞ (በአ/አ/ ፖሊስ የአየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ሀላፊ)፣ 2ኛ. ዋና ሳጅን ቦሴ ለምለሙ ሙልዬ (ቦሌ ኤርፖርት ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ)፣ 3ኛ. ሻለቃ ዮሀንስ አበበ (በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሰራዊት መኮንን)፣ 4ኛ. አደም ሰይድ መሀመድ (በግል ስራ የሚተዳደር) እና 5ኛ. ረዳት ሳጅን ተማም አቡራይ ልካሳ (በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መከላከል አባል) ላይ ነው፡፡

የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያሳየው የግል ተበዳይ የሙዚቃ መሳሪያዎች ከውጪ ለማስገባትና ጉዳይ ለማስፈጸም አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ ከተባለ ሙዚቀኛ በሚያዚያ 6/2014 ዓ.ም ውክልና ወስዳ አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 4, ሚሊዮን 534 ሺህ 203 ብር የሆኑ እቃዎችን ካስገባች በኃላ 4ኛ ተከሳሽ የአቶ አረጋኸኝ ወራሽ ውክልና ስላለኝ ንብረቱን አስረክቢኝ በማለት የግል ተበዳይን ሲጠይቃት እሷም እቃውን ለማስገባት ለጉምሩክ የከፈለችውን 1ሚሊዮን 200 ሺህ ብር እና ስራውን የሰራችበትን 2 ሚሊዮን ብር በድምሩ 3 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር በቅድሚያ እንዲከፍላት ትጠይቃለች፡፡ 4ኛ ተከሳሽም ጉዳዩን በሕጋዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ከ1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር 3ኛ ተከሳሽ የመከላከያ ሰራዊት አባልነቱን በመጠቀም የወታደራዊ ደንብ ልብስ እንደለበሰ ካልተያዙት ግብራበሮቹ ጋር ወደ መኖሪያ ቤቷ በመሄድ በመዛት እና በማስፈራራት እንዲሁም በማሳሰር ብሎም ከታሰረችበት የፖሊስ ጣቢያ ሐምሌ 29/2014 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 10፡30 ሰዓት ሲሆን ወደ አየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ “ንብረቱን ካልመለስሽ ክሱን ወደ ሽብር ወንጀል እንቀይረዋለን እናሳይሻለን” በማለት ያስፈራሯታል፡፡

ቀጥሎም ከተበዳይ የግል ስልክ ላይ ንብረቱ ይገኝበታል ያሏቸውን ስልክ ቁጥሮች ከወሰዱ በኋላ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የአየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ የሴት እስረኛ ማቆያ እንደሌለው እያወቁ ሆን ብለው ለሌላ አገልግሎት ከሚጠቀሙበት መብራት እና መኝታ ከሌለው፣ በሩ ከውስጥ ከማይዘጋ እና ደህንነቱ ባልተጠበቀ ባዶ ክፍል ውስጥ እንድታድር ያደርጋሉ፤

See also  የአሜሪካና የአዲስ አበባው የሰላም ንግግር በውጥረት ሰንብቶ ተጠናቀቀ

በዚያው ዕለት የአዳር ተረኛ ጥበቃ በመሆን ተመድቦ ሲሰራ የነበረው 5ኛ ተከሳሽ ከምሽቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ የፖሊስ መለዮውን እንደለበሰና የጦር መሳሪያ እንደያዘ የግል ተበዳይ ያለችበትን ክፍል በር ከፍቶ በመግባት ‹‹ብትጮሂም ምንም አታመጪም፣ ማንም አይደርስልሽም፣ የግቢውን በር ቆልፌዋለሁ፣ ብቻዬን ነኝ፣ እጮሀለሁ ካልሽ በዚህ ክላሽ እመታሻለሁ›› በማለት የግል ተበዳይን በብርቱ ዛቻ በማስፈራራት መከላከል እንዳትችል በማድረግ አስገድዶ ከደፈራት በኋላ በሩን ዘግቶ በመውጣት ከአንድ ሰዓት በኋላ ተመልሶ በመምጣት ተመሳሳይ ድርጊት የፈፀመባት ሲሆን የግል ተበዳይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ከተፈጸመባት በኃላም እዛው ክፍል ውስጥ ለ3 ቀን እንድታድር 1ኛ ተከሳሽ ትዕዛዝ በመስጠት፣ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ ንብረቱን ብትመልስ እንደሚሻላት በመዛት ንብረቱን አስቀምጦ የነበረው ግለሰብ በወንጀል ባልተጠረጠረበትና ክስ ባልቀረበበት ሁኔታ በማታለል ወንጀል እንደተጠረጠረ አስመስለው በ1ኛ ተከሳሽ ትእዛዝ ሰጪነት የብርበራ ትእዛዝ አውጥተው በመኖሪያ ቤቱ ብርበራ ካደረጉ በኋላ ለጊዜው ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች የግለሰቡ መኖሪያ ቤት ላይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 03-56045 ኦ.ሮ የሆነ ዶልፊን መኪና እስከ ለሊቱ 6፡00 በማቆም ጫና በመፍጠር፣ከፍተኛ ዛቻ እና ማስፈራሪያ በመፈጸም 4ኛ ተከሳሽ ንብረቱን የተቀበለ በመሆኑ፣ 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ እና 4 ኛ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል 5ኛ ተከሳሽ ደግሞ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

በተጨማሪም 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሽ ንብረቱ እሱ ጋር ይሆናል ብለው ያሰቡትን አቶ ቢኒያም ጳውሎስን ንብረቱን እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ሲዝቱና ሲያስፈራሩት ቆይተው በሐምሌ 30/2014ዓ.ም ሰዓቱ በውል ባልታወቀ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወንድማማቾች ስጋ ቤት አካባቢ 3ኛ ተከሳሽ ለጊዜው ካልታወቁ የመከላከያና የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ 5 ሰዎችና ሌሎች 2 ግለሰቦች ጋር በመሆን የግል ተበዳይ አቶ ቢኒያም ጳውሎስን ለመያዝ በመኪና በማባረር አራት ጥይቶችን በመተኮስ ከያዙት በኋላ 3ኛ ተከሳሽና ለጊዜው ያልተያዙት ተጠርጣሪዎች በመሳሪያ እየደበደቡ መኪና ውስጥ አስገብተው አይኑን በጨርቅ አሰረው ወደ ጎልፍ ክለብ በመውሰድ ከሀምሌ30/2014ዓ.ም እስከ ነሀሴ 13/2014ዓ.ም ድረስ በሕገ ወጥ መንገድ ጨለማ ክፍል ውስጥ ለ15 ቀናት አስረው ካቆዩት በኋላ ንብረቱን በሀይል ስላስመለሱ የግል ተበዳይን የለቀቁት በመሆኑ ሁለቱም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ህግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ጥቅምት 8/2015 ቀን ክስ መስርቶባቸው የክሱ ማመልከቻ ደርሷቸው ከጠበቃ ጋር ለመቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷቸዋል፡፡

See also  ዐቃቤ ሕግ በእነ ሙሉ ሐጎስ ላይ አቅርቦት የነበረው ክስ በችሎት ተሰማ

ጠቅላይ አቃቤ ህግ

Leave a Reply