“በሽሬ፣ አላማጣ፣ ኮረምና በሌሎች የትግራይና አማራ ክልል አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ ነው

በሽሬ፣ አላማጣ፣ ኮረም እና ሌሎች በአማራ እና በትግራይ ክክልል ያሉ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለፀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በፈፀመው ጥቃት ሳቢያ የትግራይና የአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች እስካሁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት አልቻሉም።

ከአላማጣ እና ከሽሬ ሰብስቴሽን የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙ አካባቢዎች ለረጅም ጊዜ አገልግሎቱን ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ከአላማጣ ሰብስቴሽን የሚወጣውን ኃይል የሚጠቀሙ የላሊበላ፣ የሰቆጣና አብዛኛዎቹ የዋግህምራ ዞን ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ አይደለም።

በወልቃይትና ሁመራ ያሉ አካባቢዎችም እንዲሁ የኤሌክትሪክ ኃይል አለማግኘታቸውን አቶ ሞገስ አክለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የተወሰኑ የትግራይ ክልል ከተሞችን መቆጣጠሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎች ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ወደ ስፍራው በመላክ የደረሰው ጉዳት ላይ ጥናት በማድረግ ላይ ናቸው።

ወደ ስፍራው ያቀናው የባለሙያ ቡድን የደረሰውን ጉዳት በማጥናት በሚያቀርበው ሪፖርት ላይ የተመርኮዘ የጥገና ስራ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

የጥገና ስራውን ለማከናወን የጥናቱን ሪፖርት መጠበቅ የግድ አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ባለሙያዎቹ እስካሁን እስከ ቆቦ ያለውን መስመር ጥናት ጨርሰዋል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በነበረው ሂደት እስከ ቆቦ ያለው መስመር የጥገና ስራ ተሰርቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም በአሸባሪው ህወሓት መልሶ ጉዳት ስለደረሰበት ዳግም ማጥናት ማስፈለጉን አክለዋል።

ከወልዲያ አልውሃ ከሚባለው አካባቢ ጀምሮ እስከ አላማጣ ድረስ ሰፊ ስራ የሚጠይቅ የኤሌክትሪክ መስመር መኖሩን መገንዘብ ተችሏል ብለዋል።

በሁመራና በአላማጣ መስመር አሁን ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ባለሙያዎች ጥናት እያደረጉ መሆኑን ገልፀው ጥገናውን የሚያከናውን ቡድን መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ይህ ቡድን የሚጠብቀው የጥናቱን ውጤትና ትዕዛዝ ብቻ መሆኑን ገልፀው የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደነበረበት ለመመለስ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መስመሮች ከዋና መንገድ ርቀው በተራራና ሸለቆ አካባቢ እንደመገኘታቸው ከፈንጂ ያልፀዱ አካባቢዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ከሀገር መከለከያ ሰራዊት የደህንነት ማረጋገጫ ሲሰጥበት ስራው እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

See also  አፓርታማዎችን በሳምንት የሚያጠናቅቅ የፈጠራ ውጤት ይዞ በፋይናንስ የሚፈተነው ወጣት

እንደ ኢዜአ ዘገባ፤ ከዚህ ቀደም በሽሬ በኩል የወልቃይት መስመርን ለማገናኘት የተጀመረው ስራ 40 ኪሎሜትር ሲቀረው በአሸባሪው ህወሓት ዳግም በተቀሰቀሰ ጦርነት ስራው መቋረጡን አስታውሰዋል።

መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትንና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል ከሰሞኑ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

Leave a Reply