ብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው እርምጃዎች በበጎ የሚታዩ ናቸው

የጦርነት ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገኘውን የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ለመታደግ ብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው እና እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች በበጎነት እንደሚታዩ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዛፉ እየሱስ ወርቅ ዛፉ ገለጹ።

አቶ ዛፉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በብሔራዊ ባንክ በኩል እየተወሰዱ የሚገኙት እርምጃዎች በበጎ የሚታዩ ናቸው። በመንግሥት በኩል በሕገ ወጥ የገንዘብ ክምችት እና ምንዛሪ ላይ እንዲሁም በፍራንኮ ቫሉታ ላይ የተወሰዱት እርምጃዎች በበጎ የሚወሰዱ እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

በመንግሥት በኩል የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት፤ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ (ፍራንኮ ቫሉታ) በጉምሩክ በኩል በቀጥታ እንዲገቡ የተፈቀደውን ውሳኔ ያለአግባብ ጥቅም ላይ የሚያውሉ አካላት ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ዛፉ፤ ሌሎች ቀዳዳዎች ሊኖሩ ስለሚችሉም መንግሥት በዚህ ረገድ ክትትል እንዲያደርግ መክረዋል።

እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሰሜኑን ጦርነት መቋጫ ማበጀት ይገባል ያሉት አቶ ዛፉ፤ ለሰላም መስፈን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎች ገጥሟታል። ይህንን ችግር በመገንዘብ መንግሥት እየሰራበት ይገኛል፤ ሆኖም ለመፍትሄው የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም ምክረሃሳብ ለግሰዋል።

በአገሪቱ ለሚስተዋለው የኢኮኖሚ ችግር ሃላፊነቱ የመንግሥት ብቻ አድርጎ መመልከት ትልቅ ስህተት ነው ያሉት አቶ ዛፉ፣ መንግሥት፤ ድርጅቶች በአንጻራዊ ሰላም ሁኔታ ስራቸውን እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኑሮ ውድነቱ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን በከፍተኛ ደረጃ ቢያጠቃም፣ የመንግሥትና የግል ዘርፉ ሰራተኞችንም ስለሚጎዳ ለመንግሥት ብቻ ሊተው አይገባም ብለዋል።

አቅርቦትን ከፍ ማድረግ በአንድ ሌሊት የሚሆን ጉዳይ አይደለም። ምርት ጊዜ የሚፈጅ፣ ሂደትን አልፎ የሚዘጋጅ ነው።

መንግሥት የወጭ ባጀቱን ያህል የውስጥ ገቢን ሊሰበስብ ይገባል። በአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ አቅም ላይ የሚስተዋለውን መመናመን ማስተካከል እንደሚገባውም ጠቁመዋል።

በሕገወጥ መንገድ የሚካሄዱ የውጭ አገር ምንዛሬ እና ክምችትን፣ የወርቅ ዝውውርና ክምችት፣ የሐሰተኛ የብር ኖቶች ሕትመትን ለመቆጣጠር ሕገወጥ ድርጊቶችን ለጠቆመም ብሄራዊ ባንክ ማበረታቻ አስቀምጧል። ፍራንኮ ቫሉታን በሕገ ወጥ መንገድ ተግባር ላይ በሚያውሉ ግለሰቦች ላይም የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ ማሳሰቡም ይታወሳል።

See also  ደቡብ ወሎ የሞርታር ተተኳሽ የደበቀው ግለሰብ እጅ ከፍንጅ ተያዘ

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም

Leave a Reply