መንግስት አመሰገነ – ሕዝብ ያለው “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” ነው

ከሊቅ እስከ ደቂቅ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ በመላው አገሪቱ በሚያስገርም መጠን፣ በባንዲራው ተውቦ ድምጹን አሰምቷል። መንግስትም “ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ድምፃችሁን ላሰማችሁ ለመላው ኢትዮጵያዊያን መንግስት ምስጋናዉን ያቀርባል” ሲል መግለጫ አውጥቷል። የሚገባ ነው። ግን ለዚህ ጨዋ ህዝብ ከመግለጫ በዘለለ ማስተንቀቂያውንም አብሮ መረዳት ቁል ጉዳይ ይሆናል።

ይህ ከዳር እስከዳር ተሞ በመውጣት ” አገሬን አትንኩ” ያለ ሕዝብ እድሜ ለትህነግ አፈና ሰላማዊ ትግልን ተለማምዷልና ነገ ብልጽግና ከታከተው በዚሁ መጠን ወጥቶ እንደሚፈነግለው ጥርጥር የለውም።

ይህን ሕዝብ በጨዋነት፣ በትጋት፣ በፍቅርና በእምነት ማስተዳደር ግድ ነው። ብልጽግና ተሸክሞት የመጣው በሽታው፣ አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ጋር ተዳምሮ ብሶበታል። ሌብነትና በባለስልጣናት ስም በትሥሥር መዝረፍ፣ በገሃድ ተገለጋዩ ኪስ መግባት፣ በየጎዳናው የሚታየው ስርዓት አልበኝነትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠገብ ሆነው በሚዲያ አደረአጅነት ዘርፊያ ላይ የተሰማሩትን መንግስት ሊቀነጥሳቸው ይገባል።

ይህ ሕዝብ “ከመንግስት ጎን ነኝ” ሲል ለትሀንግ ብቻ ሳይሆን ብልጽግና ውስጥ የተሰገሰጉትን ሌቦችና ሴረኞች ጭምር እንዲመታ በማሳሰብ ነው። ጠላት ጠላት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እየቆሙ፣ አስገራሚ ትቅስ እየተቀሱ በሚዲያ ማደራጃ ስም በሚልዮን የሚዘርፉ፣ በየመስሪያ ቤቱ የሚቀሙ፣ በዘርና በጎሳ የሚሰሩ፣ በተራ የተርኝነት ስሜት የሚወጠሩትን ሁሉ አስወግድ ሲል ነው ህዝብ አብሮ ያስታወቀ።

መንግስት ወይ የአገሪቱን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ያደረከው ገድል ክብር ይሰጠዋል። ህዝብም አመስግኗል። አሁን ደግሞ ሌብነት ላይ ዝመት፣ ዘረኛውን የሚያቅብ ህግ አውጣ። ዙሪያ ገባህን ታተራ ዘንድ ከህዝብ ጋር በገሃድ ተነጋገር። ህዝብ አታርቶ ይነግርሃል። ህዝብ መንገር ብቻ ሳይሆን ልክ ያግዝሃል። ይመካብሃል። ይጠብቅሃል። በትቅሉ ደጀንህ ይሆናል።

ህዝብ ትህነግን አክ እንትፍ ብሎ በዚህ ደረጃ ሲያወግዝና ጥላቻውን ሲገልጽ ብልጽግና ጮቤ ረግጦ ከሆነ ተሸውዷል። ይህ ሕዝብ እንዳይዞርበህ “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” እንዳለህ እወቅ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል ያንብቡ

ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ድምፃችሁን ላሰማችሁ ለመላው ኢትዮጵያዊያን መንግስት ምስጋናውን ያቀርባል!!

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገሩ ጉዳይ እንደማይደራደር ዛሬም በይፋ አስታውቋል። ትናንት እና ዛሬ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄንም አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል በመላው ኢትዮጵያ ባሉ ከተሞች በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ህዝባችን በሀገሩ ሉዓላዊነት እና ክብር እንደማይደራደር ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰምቷል።

See also  ከአማራ ክልል አሳዛኝ ዜናዎች እየወጡ ነው፤ በአገው አዊ ዞን የጅምላ ጉዳት ተከትሎ የብሄር ይዘት ያለው ግጭት ተጀምሯል

በመላዉ የአገራችን ትልልቅ ከተሞች የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ሀገሩን ለማንም አሳልፎ እንደማይሰጥና ማንኛዉንም የዉጭጣልቃ ገብነት እንደማይቀበል ገልጿል። ይህ የህዝብ ድምፅ በሚገባ ሊሰማ ይገባል።

ህዝባችን ያሰማው ድምፅ የኢትዮጵያ ድምፅ ነው። ኢትዮጵያ በምንም መልኩ በውስጣዊ ጉዳይዋ ላይ ማንም ጣልቃ እንዲገባባት የማትፈልግ ሉዓላዊ ሀገር ናት። ኢትዮጵያዊያን ዛሬም እንደ ትላንቱ በማንኛዉም ሁኔታ በየትኛዉም የዉጭ ኃይል የሀገራቸዉ ሉዓላዊነት እንዳይደፈር ዘብ እንደሚቆሙ ዳግም አረጋግጠዋል፡፡

ሉዓላዊነታችን ይከበር፣ በሰብዓዊ መብት ስም ጣልቃ ገብነት ይቁም፣ የተልዕኮ ጦርነት ይብቃ፣ ወዘተ የሚሉ መልእክቶችንም አሰምተዋል፡፡ በማንኛዉም ሁኔታ ለኢትዮጵያ እንደሚቆሙም አረጋግጠዋል፡፡

አሸባሪው ህወሓት ሀገራችን ላይ የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ አንዳንድ ምዕራባውያን ተቋማት፣ ግለሰቦች እና ሚዲያዎች የሚያራምዱትን የተሳሳተ አቋም ህዝባችን በመላው ሀገሪቱ ተቃውሟል።

የትግራይ ህዝብ ጥቅም እና ፍላጎት ከወገኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ውጪ በህወሓት ሊከበር እንደማይችልም ህዝባችን በይፋ ተናግሯል። መከላከያ ሠራዊታችን ለግዛት አንድነት እና ለሉዓላዊነታችን የሚያደርገውን ተጋድሎም ደግፏል።

አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ተቋማት እና አመራሮች ሀገራችን ላይ የከፈቱት የሀሰት ዘመቻ በሀገራችን ሰላምን እንደማያመጣም የኢትዮጵያ ህዝብ በሰልፎቹ ተናግሯል። በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ያለውን መንግስት መደገፍ እና አሸባሪውን ህወሓትን ማውገዝ እንደሚገባም ህዝቡ በድምፁ አስተጋብቷል። ይህም መደመጥ ያለበት የህዝብ ፍላጎት ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎቱን የገለፀውና ለመግለፅ እየተዘጋጀ የሚገኘው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሃገራትም ጭምር ነው። በአውሮፓ፣ በአሜሪካ እና በአውስትራሊያ ከተሞች የሚገኙ የኢትዮጵያ ልጆችም የሀገራቸውን ድምፅ በከፍተኛ ደረጃ እያሰሙ ነው። ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የተናገሩት የሀገራቸውን ፍላጎት በመሆኑ ምዕራባዊያን መንግሥታት ይህንን ድምፅ በሙሉ ልባቸው ሊያዳምጡት ይገባል።

እነዚህ ሰልፎች የኢትዮጵያ ህዝብ በፖለቲካ አመለካከት፣ በኢኮኖሚ ደረጃ፣ በሀይማኖት እና በብሔር ሳይለያይ በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ መቆሙን የሚያመለክቱ ናቸው። በኢትዮጵያ ምድር በሀገሩ ሉዓላዊነት ከህፃን እስከ አዋቂ የሚደራደር አለመኖሩንም በተጨባጭ የሚያሳዩ ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በህዝብ የተመረጠ በመሆኑ ለሚንፀባረቁ የህዝብ ፍላጎቶች እውቅና እንደሚሰጥ ለመግለፅ ይወዳል። የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር ሉዓላዊነት እንደማይደራደር ሲገልፅ የቆየው ከዚሁ ህዝባዊ ፍላጎት በመነጨ እሳቤ እንደሆነ ወዳጅም ጠላትም ሊገነዘበው ይገባል። መንግሥት በምንም መልኩ በህዝብ ፍላጎት እና በሀገር ሉዓላዊነት ላይ እንደማያቅማማ ከዚህ ቀደም እንዳስታወቀው ሁሉ አሁንም ዳግም ያረጋግጣል።

See also  የክረምቱ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ የተናጠል ተኩስ አቁም መታወጁን መንግስት አስታወቀ

የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገሩ ሉዓላዊነት እና ክብር ያለውን ቀናዒነት በትልልቅ ህዝባዊ ሰልፎችና ትዕይንቶች በመግለፁ መንግሥት ያለውን አድናቆት እና ክብር እየገለፀ፤ ወደፊትም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያንን በጋራ በሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አንድነቱን እንዲያሳይ ጥሪውን ያቀርባል።

ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Leave a Reply