ክብደትዎን መቀነስ ይፈልጋሉ? ቁርስ እንዴት መመገብ እንዳለብዎ እንንገርዎ

ቁርስዎን በደንብ መመገብ እና ቀለል ያለ እራት መብላት የረሃብ ስሜት እንዳይኖር በማድረግ ክብደትን ለመቀነስ ይረዳል ይላሉ ተመራማሪዎች።

ሳይንቲስቶች ከበድ ያለ ቁርስ ወይም ከበድ ያለ እራት በሰዎች ክብደት ላይ የሚያመጣውን ተፅእኖ ለማነፃፀር ሞክረዋል።

የቀኑን ዋነኛ ምግብ በየትኛው ሰዓት ቢመገቡ ሰዎች የሚያቃጥሉት ካሎሪ ተመሳሳይ ሆኖ እንደሚሆን የአበርዲን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል።

ነገር ግን በደንብ ቁርሳቸውን የተመገቡ ሰዎች በቀን ውስጥ ያላቸው የምግብ ፍላጎት አነስተኛ ሆኖ ታይቷል፤ ይህም ማለት የሚፈልጉትን አመጋገብ ለመከተል ቀላል ያደርገዋል።

አጥኚዎቹ በዚህ ምርምራቸው ‘ክሮኖ ኒውትሪሽን’ የተሰኘው ፅንሰ ሃሳብን በጥልቀት ለማየት ሞክረዋል።

[ክሮኖ ኒውትሪሽን በየትኛው ሰዓት ምግብ መመገብ የበለጠ ውጤታማ ያደርገናል የሚለውን የሚመረምር ሳይንስ ነው። የሰውነትዎን አካላዊ፣ አዕምሯዊ እና ስሜታዊ ዑደቶችን የሚቆጣጠረው ክፍል ምግብ ጋር ያለውንም ዝምድና ይገመግማል። ]

ከመሸ በኋላ መመገብ ለሰውነታችን መጥፎ ጊዜ ነው፣ ምክንያቱም የሰውነታችን ሰዓት ምግብን ወደ ኃይል የሚለውጠውን (ሜታቦሊዝም) ወደ እንቅልፍ ስለሚቀይረው ነው።

ተመራማሪዎቹ ያሳተፏቸው 30 በጎ ፈቃደኞች ከሁለት ወራት በላይ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት በቀን በአጠቃላይ እስከ 1 ሺህ 700 ካሎሪ የሚሆን ምግብ ተዘጋጅቶላቸው ነበር።

በአንደኛው ወር ለቀን የሚያስፈልገውን የካሎሪ መጠን ግማሹን ለቁርስ እንዲበሉ እና ምሳ እና እራት ደግሞ አነስ ያለ ምግብ እንዲመገቡ ተደርገዋል። በሁለተኛው ወር እነዚህ በጎ ፈቃደኞች ከቁርስ ይልቅ እራት ላይ ከበድ ያለ ምግብ እንዲበሉ ተደረጉ።

ለበጎ ፈቃደኞቹ የተሰጣቸው የምግብ አይነት

ሴል ሜታቦሊዝም በተሰኘው ጆርናል ላይ በታተመው ውጤት መሰረት የቀኑን ከባድ ምግብ በየትኛውም ሰዓት መመገብ ሰውነታችን በቀን ምን ያህል ካሎሪ ያቃጥላል የሚለው ላይ ምንም ልዩነት የለውም።

ዋነኛው ልዩነት ግን የታየው በምግብ ፍላጎት ወይም የረሃብ ስሜት ላይ ነው። ከፍተኛ ቁርስ የሚመገቡ ሰዎች በቀን ውስጥ አነስተኛ የምግብ ፍላጎት እንዲኖራቸው ማድረግና የረሃብ ስሜትንም እንዲቆጣጠሩ ያደርጋል።

ፕሮፌሰር አሌክሳንድራ ጆንስተን እንደሚሉት በርካቶች የሚመገቡትን የምግብ መጠን በማይቆጣጠሩበት ሁኔታ ውስጥ ጥናቱ ወሳኝ ሊሆን ይችላል።

“ጥናቶቹ እንደሚጠቁሙት የምግብ ፍላጎትን ለመቆጣጠር በደንብ ቁርስ መመገብ መሠረታዊ ነው” ይላሉ።

See also  ትግራይ ሥርዓት አልበኝነት የሰፈነባት የስቃይ ማዕከል ሆናለች

“ቀንዎን በጤናማ እና በትልቅ ቁርስ መጀመር ከቻሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዲሁም በተቀሩት ሰዓታት ያለውን የምግብ ፋላጎትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ዕድል ይሰጣል” በማለት ያስረዳሉ።

በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት የቁርስ ዓይነቶች የፍራፍሬ ጭማቂ፣ እርጎ፣ እንቁላል፣ ቋሊማ (ሶሴጅ) እና እንጉዳይ የያዘ ሲሆን፣ ይህም ሁሉም ሰዎች ጥጋብ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያለው ነው።

ከፍተኛ ቁርስ መመገብ ለምን የምግብ ፍላጎትን እንደሚቀንስ ግልፅ አይደለም። ነገር ግን ፕሮፌሰር ጆንስተን እንደሚሉት ይህ ሁኔታ ከአዕምሯችን የምግብ ፍላጎት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሃሳቦች አሉ ይላሉ።

“የአዕምሯችን የምግብ ፍላጎት የሌሊቱን ጾም የምንፈታበትና የመጀመሪያ ምግብ ጋር የበለጠ የተጣጠመ ነው” ይላሉ።

ነገር ግን ይህ ውጤት ከበርካቶች የአመጋገብ ልምድ ጋር ተቃራኒ ነው።

“በርካቶች የሚተኙበትን ሰዓታት ለመጨመር እየሞከሩ ባለበት ወቅት በማለዳ ተነስተው ምግብ ለማዘጋጀትም ሆነ ተቀምጠው በደንብ ለመብላት ጊዜ አይኖራቸውም። ይህ ማለት በርካቶች በደንብ የሚበሉት እራት ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ጆንስተን።

በአሁኑ ወቅት ሳይንቲስቶች በፈረቃ የሚሰሩ ሠራተኞች እኩለ ሌሊት ላይ ሲመገቡ ምን እንደሚፈጠር እየመረመሩ ነው።

በተጨማሪም ግለሰቦች እንደ ባህርያቸው የጠዋት ሰዎች ከሆኑ ጠዋት፣ ወይም ደግሞ የማታ ሰዎች ከሆኑ ማታ መብላት ይኖርባቸው ይሆን? የሚለውን ለማየት እየሞከሩ ነው።

“አመጋገብዎን ለመለወጥ እያሰቡ ከሆነና የሚራቡበትን ወይም ተጨማሪ መክሰስ ሰውነትዎት የሚፈልግበትን ወቅት ያስቡ” በማለት የሚናገሩት የአስተን ዩኒቨርስቲ የአመጋገብ ባለሙያ ዶክተር ዱዋን ሜሎር ናቸው።

“ረሃብ የሚሰማዎት ጠዋት ከሆነ በደንብ ቁርስ መመገብ ሊረዳዎት ይችላል። በተመሳሳይም የምሽት ተመጋቢ ከሆኑም በቀን ውስጥ አነስተኛ ምግቦችን ተመግበው እራት ላይ በደንብ መመገብ ሊጠቅምዎ ይችላል” ይላሉ።

ቢቢሲ አማርኛ

Leave a Reply