“ወያኔ አማራ በመኾናችን ከ40 በላይ ሰዎችን በድብደባና በእስራት አካላችንን አጉድሏል” የጠለምት ነዋሪዎች

“አሸባሪው ወያኔ አማራ በመኾናችንና ለሕወሓት አንታገልም በማለታችን ከ40 በላይ ሰዎችን በድብደባና በእስራት አካላችንን አጉድሏል” በቡድኑ የተጎዱ የጠለምት ነዋሪዎች

ተጎጅዎቹ “ለሕወሃት የማትታገሉ አማራ ስለኾናችሁ ነው በማለት ዋሻ ውስጥ በማሰር ለ12፡00 ሰዓታት በሰደፍ፣ በስለትና በዱላ በመደብደብ አካለ ጎደሎ አድርጎናል ሲሉ በቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸው 4 የጠለምት ነዋሪዎች ተናግረዋል።

አሸባሪው ወያኔ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በ 27 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ በአማራ ሕዝብ ላይ የፈጸመው በደል አልበቃ ብሎት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮም በአማራ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል። ቡድኑ በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም በሰሜን ጎንደር ዞን ከፊል ጠለምትና ከፊል አዳርቃይ ወረዳዎች ወረራ ከፈጸመ በኋላ የአማራ ተወላጅ በኾኑ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ግፍ ፈጽሟል።

ቡድኑ አለሙ አበባው፣አብረሃ አለሙ፣አስፋው አለሙና ደስታ ታከለ በሚባሉ የሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ ሰራኮ ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ የፈጸመው ግፍ በዞኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ ሲፈጽም ለነበረው ግፍ ትልቅ ማሣያ ናቸው።

3ቱ ወጣቶች በሽብር ቡድኑ ከተያዙ በኋላ በእያንዳንዳቸው ላይ ከፍተኛ ድብደባ ፈጽሞባቸዋል።

ወጣቶቹ “ቡድኑ የአማራ መታወቂያ ይዘህ ከትግራይ መሬት ምን ትሠራለህ፤ ለሕወሃት የማትታገሉ አማራ ስለኾናችሁ ነው፤ የደበቃችሁትን መሣሪያ አምጡ በማለት ዋሻ ውስጥ እጅና እግራችንን አስረው በዱላ፣በሰደፍና በስለት በመደብደብና በመውጋት እጅና እግራችንን ከጥቅም ውጭ አድርጓል” ብለዋል።ወጣቶቹ ሠርተው ያጠራቀሙት ገንዘብም በቡድኑ እንደተዘረፈ ገልጸዋል።

ይውጋህ ብሎ ይማርህ እንዲሉ ድብደባውን ከፈጸሙ በኋላ ሽሬ ከተማ ለሕክምና ወስደዋቸው እንደነበር የሚናገሩት ተጎጂ ወጣቶቹ ገንዘባችን ዘርፈውን ስለነበር መታከሚያ ገንዘብ በማጣታችን ሳንታከም ቀርተናል። ከሽሬ ከተመለስን በኋላም ጠለምትን ለቃችሁ ካልወጣችሁ እንጨርሳችኋለን እያሉ ያስፈራሩን ነበርም ብለዋል።

ሌላኛው ተጎጅ አቶ አለሙ አበባው የአብርሃ አለሙና የአስፋው አለሙ አባት ናቸው።እንደ አቶ አለሙ ገለጻ “ልጆቼን ጫካ ውስጥ በደብቄ ልጆችህን አምጣ እያሉ በየጊዜው ያስሩኝ ነበር፤ ልጆቼ በጎረቤት ጥቆማ ከተያዙብኝ በኋላ እኔን ጨምሮ 9 ቤተሰቦቼ ላይ ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመውብኛል።ልጆቼን አካላቸውን በማጉደል ወልጄ እንዳልወለድኩ አድርገውኛል” በማለት እንባ እተናነቃቸው በደላቸውን ነግረውናል።

See also  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በግል ባንኮች የከፈቷቸው የባንክ ሒሳቦች እንዲዘጉ ታዘዙ

አቶ አለሙ “አማራ የኾነ የጠለምት ነዋሪ ኹሉ በተወለደበት ርስቱ ‘አማራ ነህ’ እየተባለ ግድያ፣እሥራትና ድብደባ ተፈጽሞበታል።ከ ሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሰራኮ በተባለችው ቀበሌ ቤቻ ከ 40 በላይ አማራዎች በተፈጽሞባቸው ድብደባ አካለ ጎደሎ ኾነዋል” ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑ አካባቢውን ከለቀቀ በኋላ የወገን ጦር አባላት እንደተንከባከቧቸው ተጎጅዎች ገልጸዋል። በተፈጸመብን በደል ማዘን ብቻ ሳይኾን ቀለብ በመስጠትና ሕክምና አግኝተን ከጉዳታችን እንደምናገግም በመናገር ተስፋ ሰጥተውናል ብለዋል።

አማራ ናችሁ ተብለው በአሸባሪው ወያኔ ከፍተኛ የአካል ጉዳትና የንብረት ዝርፊያ የተፈጸመባቸው እነዚህ ወገኖች መንግሥት የሕክምና እና የምግብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋ። ደባርቅ፡ ጥቅምት 22/2015 ዓ.ም (አሚኮ)

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

Leave a Reply