የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ሰራተኞች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መሰረተ

ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉ 7 የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ሰራተኞች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መሰረተ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ባካሄደው የወንጀል ምርምራ መሰረት የተሰበሰቡ ማስረጃዎችን መርምሮ ክስ ሊመሰርት ችሏል፡፡

የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው በአንድ የባንኩ ደንበኛ ስም የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ቦሌ 18 ቅርንጫፍ የተከፈተ ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ቁጥር የሚገኝ ገንዘብን 1ኛ ተከሳሽ አቶ ገብረመድኅን ፍሥሓ በባንኩ መመሪያ መሠረት የተዘጋጁትን የቼክ ቅጠሎች መዝግቦ በማስፈረም ማስረከብ እያለበት በእጁ የገባን ባለ 25 ቅጠል ቼክ በሲስተም ላይ አገልግሎት እንዲሰጡ ካፀደቀ በኋላ ለደንበኛው አስፈርሞ ሳያስረክብ በመቅረት ቼኩ ከማን እጅ እንደሚገኝ ባለመታወቁ እና ከደንበኛው ሒሳብ ቁጥር በቀን ሚያዚያ 17/2011 ዓ.ም በቼኩ ላይ 4 ሚልዮን 150 ሺ ብር ወጪ ተደርጎ ለሌላ ሰው በመከፈሉ፤

2ኛ ተከሳሽ አቶ ጌትነት ሙሉጌታ በፍቼ ቅርንጫፍ ክፍያ ሲፈጽም ለክፍያ የቀረበ ቼክ በፊደል እና በአኀዝ የተጻፈው ትክክለኛ ስለመሆኑ የማጣራት ኃላፊነት እያለበት መጀመሪያ የተፃፈው 1 ሚልየን 150 ሺህ ብር ተሰርዞ 4 ሚልዮን 150 ሺህ ብር ተብሎ በፊደል እና በአኃዝ የተስተካከለ ስለመሆኑ በግልጽ እየታየ እንዲሁም በእለቱ ክፍያውን በጥሬ ገንዘብ ለመፈፀም በቅርንጫፉ በቂ ጥሬ ገንዘብ ሳይኖር በፍቼ ቅርንጫፍ ለአንድ ግለሰብ እንዲከፈለው በማድረግ 4 ሚልዮን 150 ሺህ ብር በባንኩ ላይ ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ፤

በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ መዝገብ የባንኩ ሰራተኞች በሆኑት በ3ኛ ተከሳሽ ወ/ሪት ሄቨን መሀመድ፣ በ4ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ፋንታሁን፣ በ5ኛ ተከሳሽ አቶ መስቀሉ ዳጎ እና በ6ኛ ተከሳሽ ወ/ሪት ፍቅርተ አሥራት ላይ የቀረበ ክስ ሲሆን ማንነቱ የማይታወቅ ግለሰብ ሀሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም ከአንድ የባንኩ ደንበኛ የማይንቀሳቀስ ሂሳብ ወጭ ለማድረግ ቦሌ መድኃኒያለም ቅርንጫፍ ጥያቄ ሲቀርብ በባንኩ መመሪያ መሠረት የማይንቀሳቀስ ሒሳብ ወደ ሚንቀሳቀስ ሒሳብ የሚቀየረው ደንበኛው በተከታታይ 3 ጊዜ የገንዘብ ወጭ ካደረገ በኋላ መሆን እያለበት፣ እና ከማይንቀሳቀስ ሒሳብ ገንዘብ ወጪ ለማድረግ ደንበኛው ሒሳቡ ከተከፈተበት ቅርንጫፍ በአካል ካልቀረበ እንዳይስተናገድ የተከለከለ ሆኖ እያለ እንዲሁም ደንበኛው ሒሳብ ሲከፍት ሲስተም ላይ ፎቶ ያልተያያዘ በመሆኑ አጠራጣሪ የሂሳብ እንቅስቃሴ ሊሆን ስለሚችል ወጭ ለማድረግ ቦሌ መድኃኒያለም ቅርንጫፍ ጥያቄ ሲቀርብ ደንበኛው ሒሳቡን በከፈተበት በቦሌ 18 ቅርንጫፍ ሄዶ እንዲስተናገድ ማድረግ ሲገባቸው በስልክ በመደዋወል 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ሒሳቡ ተንቀሳቃሽ እንዲደረግ በስልክ በጠየቁት መሠረት 3ኛ ተከሳሽ ሂሳቡን ተንቀሳቃሽ ስታደርግ 4ኛ ተከሳሽ በማጽደቅ በእለቱ በቀን ሀምሌ 26/13 ዓ.ም 2 ሚልየን 850 ሺህ ብር እና 2 ሚልየን 700 ሺህ ብር በአንድ ግለሰብ የሒሳብ ቁጥር ሲዘዋወር 5ኛ ተከሳሽ ገንዘቡ እንዲተላለፍ በማድረግ 6ኛ ተከሳሽ ደግሞ በማጽደቅ በድምሩ ብር 5 ሚልዮን 500 ሺህ ብር ወጭ ሆኖ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ በዋና ወንጀል ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የሕዝባዊ ድርጅት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

See also  የእሽሙር ማህበር (JOINT VENTURE)

እንዲሁም 7ኛ ተከሳሽ በሆኑት በአቶ ሥራው ጥሩነህ ላይ በዚሁ ወንጀል የተገኘን ገንዘብ በግል ሂሳብ ቁጥሩ እንዲገባ በማድረግ በድምሩ ብር 150 ሺህ ብር ወስዶ በመጠቀም በፈጸመው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሷል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎትም በተከሳሾች መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Leave a Reply