አሊ ቢራ አረፈ –

ከግማሽ ዘመን በላይ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ የቆየው ድምጻዊ አሊ ቢራ ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በ75 ዓመቱ ማረፉን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን አስታውቋል።

የክብር ዶክተርነት ማእረግ የተሰጠው አብሪ ኮከብ አሊ ቢራ በ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ገንደ ቆሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው የተወለደ ድምጸ መረዋ፣ የህብረተሰብ ድምጽና አንደበትና የፍቅር ብቻ ሳይሆን የመብት ተሟጋች ነበር።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በድሬዳዋ ከተማ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴድራል ትምህርት ቤት ተከታትሏል። አሜሪካ አገር በሚገኘው የሳንታ ሞኒካ ኮሌጅም የሙዚቃ ትምህርት ስለመማሩም ነው የሚነገረው፡፡

ድምጻዊ ዓሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም በ13 ዓመቱ የኦሮሞን ሙዚቃ ለማስተዋወቅ ዓላማ አድርጎ የተቋቋመውን ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን “ አፍረን ቀሎ ”ን በመቀላቀል ነው የሙዚቃ ስራውን አንድ ብሎ የጀመረው።

በኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ ከ60 ዓመታት በላይ በጽናት የዘለቀ የሙዚቃ ንጉስ አሊ ቢራ ከ267 ሙዚቃዎችን መጫወቱም ይነገራል፡፡

በአፋን ኦሮሞ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የሆነውን አልበሙን በ1971 ከሰራው በተጨማሪ ለገበያ የቀረቡ 13 አልበሞችን ስርቷል፡፡

ድምጻዊ አሊ ከአፋን ኦሮሞ ቋንቋ በተጨማሪ፣ በሱማሊኛ፣ በአፋርኛ፡ በሐረሪ፣ በአማርኛና በሱዳን ቋንቋዎች በርካታ ዘፈኖችን መጫወት ችሏል።

ከሙዚቃ ስራዎቹ መካከልም ……..

“BIRRAA DHAA BARIHE” የመጀመሪያ ስራው

” Waa Malli nu dhibe “

” Jaalaluma teeti “

” Barnootaa “

” Ushuruururuu “

“Karaan Mana Abbaa Gadaa “

“Nin deema “

” Dabaala Keessan ” የሰርግ ሙዚቃ

” AMALELE ” ከብዙዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ድምጻዊ ዓሊ ቢራ “Birra Children’s Education Fund” የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከባለቤቱ ጋር አቋቁሞ ለሕፃናት ትምህርት ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

አርቲስት አሊ ቢራ ከድሬዳዋ እና ከጅማ ዩኒቨርስቲዎች የክብር ዶክትሬትን የተቀበለ ሲሆን በህይወት ዘመኑ ሌሎች በርካታ ሽልማትን እና እውቅናዎችን አግኝቷል፡፡

በዛሬው ዕለትም አርቲስቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። በአርቲስቱ ህልፈተ ህይወት ኢትዮ ኒውስ 12 የተሰማውን ሃዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡

See also  ትህነግ " ፈሪና ጀግና" በሚል እየፈረጀ ነው፤ እነ ዳኔል ብርሃኔ መተንፈሻ አላገኙም

ዜናው ከኢዜአ ተወስዶ መጠነኛ አሳብ የታከለበት ነው

Leave a Reply