በትግራይ እህል ረከሰ፤ የመቀለ ነዋሪዎችና የዴያስፖራው አቋም ተለያይቷል

– ስንዴ 3 ሺህ፣ ጤፍ ስምንት 8 ሺህ፣ ፕሪማ ማኮሮኒ 2 ሺህ ገብቷል

የፌደራል መንግሥቱና ትህነግ የደረሱትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ የምግብ ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ የሚባል የዋጋ ቅናሽ ታየ። ሕዝቡ የሰላም ሂደቱ እንድተባለው ተግባራዊ እንዲሆን “…ጦርነቱ በሚደረግበት ቦታ የምንኖረው እኛ ነን። መሬት ላይ ምን እንዳለ የምናውቀው እኛ ነን…” በሚል ዳያስፖራው ክፍል ከሚለው ፍጹም የተለየ መሆኑ ተመልክቷል።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ ከመቀለ በአይኑ ያየውን ጠቅሶ እንደዘገበው የጤፍ ዋጋን ጨምሮ የእህልና ሌሎች ዋጋ ንረቶች አሁን ድንገተኛ ቅናሽ አሳይተዋል። በማህበራዊ ሚዲያም ይህንኑ የሚያጠናክር መረጃ እየወጣ ነው።

የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰላም እንደናፈቀው እማኝ ጠቅሶ የዘገበው ቢቢሲ “ሕዝቡ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ እምነት የለውም” ብሏል። ቢቢሲ ይህን ቢልም መከላከያ በደረሰባቸውና በተቆጣጠራቸው አብዛኛው የትግራይ ከተሞችና አካባቢዎች ሕዝብ እንደተቀበለው በምስል የተደገፈ መረጃ ሲሰራጭ መክረሙ ይታወሳል። የትግራይ ታጣቂዎች ሳይቀሩ መከላከያ አለበት ድርስ እየመጡ ምግብ መብላትና አብረው ሲጋራ እየተጋሩ ማጨስ መጀመራቸውንም ቢቢሲ በዘገባው አላካተተም።

የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ቢቢሲ ምስክሮቼ ያላቸው የመቀለ ነዋሪዎች ስምምነቱ እንዳስደሰታቸውና በበጎ እንደተመለከቱት ተናግረዋል። ብዙዎች ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ፍላጎታቸው መሆኑንም ተናግረዋል። በርካታ ሰዎች መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ጠቅሷል።

የሰላም ስምምነቱ ዜና መሰማቱን ተከትሎ የእህል እና የጥርጥሬ ገበያ የዋጋ ቅናሽ አሳይቷል። በተለይ ቅናሹ በመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ላይ በይበልጥ ተስተውሏል። ቢቢሲ እማኝነቱን ሲሰጥና አሃዝ ጠቅሶ የእህል ዋጋ መቀነሱን ሲያስታውቅ፣ የቀነሰበትን ምክንያት አላብራራም።

ቀደም ሲል የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ 14ሺህ ብር የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ መንግሥትና በትህነግ አማጺ ቡድን መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ወደ 8ሺህ ብር ዝቅ ብሏል። ስንዴም በተመሳሳይ ከፍተኛ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን በአንድ ጊዜ ከ9ሺህ ብር ወደ 3ሺህ ወርዷል። በተመሳሳይ የዘይት፣ የስኳር እና የበርበሬ ዋጋም መጠነኛ ቅናሽ እንደታየበት የመቀለ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ይፋ አያድርገው እንጂ መከላከያ ይፋ ባደረጋቸው የቪዲዮ ማስረጃዎች በተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ መጠን ያለው እህል በመጋዘን ተከዝኖ መገኘቱንና ይህንኑ እህል ለህዝብ ማከፋፈሉ ገበያውንም እንዳረጋጋው ነዋሪዎች አመልክተዋል። ቀደም ሲል እህሉ ለትህነግ ታጣቂዎች የሚውል፣ ህዝብም ልጁን ሲያቀርብ ብቻ መጠነኛ እርዳታ ይሰጠው እንደነበር የተማረኩ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

የቢቢሲ ዘጋቢ “ተዘዋውሬ እንደታዘብኩት” ሲል እንደጻፈው በመቀለ የበርካታ ሰዎች ዋናው መነጋገሪያ ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ነው።

የመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የሁለት ልጆች እናት ወ/ሮ ራሔል አባይ በሰላም ስምምነቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል። “…ጦርነቱ በሚደረግበት ቦታ የምንኖረው እኛ ነን። መሬት ላይ ምን እንዳለ የምናውቀው እኛ ነን። አሁን ቢያንስ የድሮን ጥቃት ሳያሳስበን መንቀሳቀስ ጀምረናል” ብለዋል ወ/ሮ ራሔል። እንደዘጋቢያችን ከሆነ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደ ወ/ሮ ራሔል ያለ አመለካከት ነው ያላቸው።

የ32 ዓመቱ በላይ ታከለ የመቀለ ነዋሪ ሲሆን፣ በሰላም ስምምነቱ ዙርያ ተጠይቆ ሲመልስ “እኛ የትግራይ ሕዝቦች እንደተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በሰላም መኖርን ነው የምንሻው። ጦርነቱ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን እኛ ነን የምናውቀው። አሁን የምንሻው ፈራሚዎቹ ወገኖች ስምምነቱን እንዲያከብሩ ነው።” ብሏል።

የቢቢሲ ዘጋቢ ያነጋገራቸው በትግራይ የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ አማራ እና ሌሎች ከተሞች የሚወስዱ መንገዶች ሁሉ እንዲከፈቱና የሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ ፍላጎት እንዳላቸውም ዘጋቢው አመልክቷል። በነካ እጁ መቀለ ተዘዋውሮ ያየውን ሲያስታውቅ ዳያስፖራው የትግራይ ተቆርቋሪ በትግራይ ሃይሎች ትጥቅ መፍታት ጉዳይ ስምምነት እንደሌለው ጽፏል።

በመቀለ ሕዝብ የሰላም ናፍቆት እንዳለበትና መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን ተሳፋውን እንደገለጸለት የመሰከረውና የኑሮ ውድነቱ በሚገርም ፍጥነት ጋብ ማለቱን አሃዝ ጠቅሶ የዘገበው የቢቢሲ ዘጋቢ፣ የዳያስፖራውን የሩቅ ምኞትና የሰላም ሂደቱን ካለመረዳትና ከጦርነቱ ለመነገድ ባሰላ መልኩ የሚሰነዘረውን ቅስቀሳ ከመቀለ የሰላምና የብሩህ ተስፋ ጋር ለምን ማገናኘት እንደፈለገ ግልጽ አላደረገም።

You may also like...

Leave a Reply