የአውሮፓ ሕብረት የ38 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ


የአውሮፓ ሕብረት በግጭቱ የተጎዳውን የጤና እና የትምህርት ዘርፍ መልሶ ለመገንባት የሚውል የ38 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ::

የመልሶ ግንባታው በጤና ዘርፍ በጤና ሚኒስቴር እና በዩኒሴፍ ትብብር እንዲሁም በትምህርት ዘርፍ ፕላን ኢንተርናሽናል በተሰኘው ድርጅት በኩል ነው የሚተገበረው።

የጤናው ዘርፍ ድጋፍ በመንግሥትና በዩኒሴፍ (በተመድ ህፃናት አድን ድርጅት) በኩል ለሶስት ዓመታት የሚተገበር የ31 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ነው።

ስምምነቱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ እና የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ የኢትዮጵያ ፅህፈት ቤት ዋና ተወካይ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ተፈራርመዋል።

በዚህም ሕብረቱ በመንግስትና ህወሃት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በክልሎቹ የተጎዱ የጤና ተቋማትን ወደ አገልግሎት ለመመለስ እና የሴቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎት የማግኘት መብትን ለመደገፍ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ከ3 ሺህ በላይ የጤና ተቋማት ስለመጎዳታቸውና ከ700 ሺህ በላይ ህፃናት ከመደበኛ ክትባት አገልግሎት ውጭ መሆናቸው ተጠቅሷል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ በበኩላቸው የሕብረቱ ድጋፍ በወሳኝ ጊዜ የተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ድጋፉ መንግስት የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ለማስፋፋትና የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

በተለይም በጦርነቱ ለፆታዊ ጥቃት የተዳረጉትን ጨምሮ ለሌሎች የጤና ዕክሎች የተጋለጡ ዜጎችን ስነ-ልቦናዊ ችግር ለማከምና ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ እንደሚረዳ ነው የተናገሩት።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ድጋፉ በአማራ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ እና በደቡብ ህዝቦች ክልል በግጭት የተጎዱ ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በጤናው ዘርፍ ከሚሰሩ ተግባራት ውስጥ 60 የጤና ተቋማትን መልሶ መገንባት አንዱ ግብ ነው።

በሌላ በኩል ሕብረቱ በትምህርት ዘርፍ ፕላን ኢንተርናሽናል በተሰኘ ድርጅት በኩል በአማራ፣ አፋርና አማራ የሚተገበር 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ተፈራርሟል።

በቀጣይ ሕብረቱ በትምህርት ዘርፍ መሰረተ ልማት ለመገንባት 33 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለማድረግ ዕቅድ እንዳለውም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

ድጋፉ በአማራ፤ አፋርና ትግራይ ክልሎች 21 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ግንባታና መልሶ ማቋቋም ጨምሮ ዘርፉን ለመደገፍ የሚውል መሆኑ ተጠቅሷል።

See also  ትውልደ ኢትዮጵያዊው የፑንትላንዱ ዳኢሽ ታጣቂ ቡድን ኦፕሬሽን መሪ ተገደለ

(ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply