“በጦርነቱ የተነሳ የተከሰቱ የሥነልቦና ጉዳቶችን ለማከም ከወዲሁ መዘጋጀት ይገባል”

በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ጦርነት የተነሳ በርካቶች ላይ የደረሰውን የሥነልቦና ጉዳት ለማከም ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅትና ጥረት ማድረግ ይገባል ሲሉ የሥነ አዕምሮ ሐኪሙ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

የሥነ አዕምሮ ሐኪምና የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ጦርነት በተደረገበት አካባቢ የሚገኝ ማህበረሰብ ለከፍተኛ የአዕምሮ ጤና ችግር ስለሚጋለጥ መፍትሄውን ይዞ መቅረብ ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ ከደረሰው ጉዳት ይልቅ እኔን የሚያሳስበኝ ከሰው ሕይወት መጥፋትና ከአካል ጉዳት እንዲሁም ከንብረት ጋር ተያይዞ የደረሰው የአዕምሮ ስብራት መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

አካላዊ ጉዳት በቀን በወራትና በዓመታት ይታከማሉ፤ የአዕምሮ ጉዳት ግን በቶሎ የሚሽር ሳይሆን ከአንድ ትውልድ ወደቀጣዩ ትውልድ ሊሸጋገርም እንደሚችል ተናግረዋል።

እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ገለጻ፤ በአዕምሮ ጉዳት ላይ የደረሰው የሥነ ልቦና ችግር ከሌላው በተለየ ለማከም ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ችግሩን ለማከም የእናቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች የሐይማኖት አባቶች ከሁሉም በተለየ ደግሞ በአዕምሮ ጤና ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ቀጣይነት ያለው ጥረት ያስፈልጋል።

አሁን ላይ የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ መሆን በመጀመሩ የሥነልቦና ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች ማከምና ከችግሩ እንዲወጡ በቶሎ ማገዝ ይገባልም ብለዋል።

 በዚህ ረገድ እኔና መሰሎቼ በአዕምሮ ጤና ላይ የሰራን ሐኪሞች ብዙ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በዚህ ወቅት የሥነ አዕምሮ ሐኪሞች አስፈላጊነታቸው ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በጦርነቱ የተነሳ የተፈጠረው የአዕምሮ ቁስለት ገና አልደረቀም፤ ጥፋቶቹም የተከሰቱት በቅርብ ጊዜ በመሆኑ የሥነልቦና ችግሩን የማከሙ ሂደት ወቅቱን የጠበቀ መሆን አለበት፤ ችግሩም ለልጅና ለልጅ ልጅ እንዳይተላለፍ ሙያዊና ማህበረሰባዊ መፍትሄ ያሻዋል ብለዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን እንደሚያብራሩት፤ የአዕምሮ ስብራት በአንድ ትውልድ ላይ ብቻ የማይቆም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊሸጋገር የሚችል ትልቅ ጉዳይ ነው።

በመሆኑም የአዕምሮ ጉዳቱ የተወሳሰበና ጥልቅ እንደሚሆን በማሰብ የሥነልቦና ችግሮቹ ወደቀጣዩ ትውልድም እንዳይሸጋገሩ አስፈላጊው ትብብር መደረግ ይኖርበታል ብለዋል።

ችግሮቹ እንዳይዛመቱና እንዳይቀጥሉ ለሥነልቦና ሕክምናው ከሚሰጠው ጊዜ ባለፈ የአዕምሮ ስብራትን ይቅር ባይነት አስፈላጊ መሆኑንም ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል።

See also  ቦቆጣቦ - ዘረኝነትን በፍቅር የወጋች መንደር!

ይቅርታ ማድረግ አንድ ባህላችን ቢሆንም ውጤቱ የሰመረ እንዲሆን ግን በደንብ መያዝና መከወን አለበት። በተለይም ችግሮች እየተባባሱ ቶሎ ወደእርቀ ሰላም መሄድን፣ ስህተቶችን በሚገባ ተናዞ ወደካሳ መግባትን ይጠይቃል ብለዋል።

በጦርነቱ የተነሳ የተጎዱ ሰዎችን እንባ ማበስ፣ እንክብካቤ በመስጠትና ይቅር መባባል ዘላቂ ሰላምና ፍቅር እንዲነግስ ያግዛል ሲሉም ፕሮፌሰር መስፍን አስታውቀዋል።

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን  ኀዳር   1/ 2015 ዓ.ም

Leave a Reply