በመሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች

መግቢያ

የመሰረተ ልማት መኖር ለአንድ ሀገር ሕዝብ የተሻለ ኑሮ እጅግ ወሳኝ በመሆኑ መሰረተ ልማት የመገንባት ሥራ ሀገራት ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩት ሥራ ነው፡፡ በሀገራችንም ለዘመናት አቅም በፈቀደ መጠን መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ሆኖም እነዚህ በውስን የሀገር ሀብት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የሚደረጉ መሰረተ ልማቶች በየጊዜው ለተለያየ ጉዳት ሲዳረጉና ስርቆት ሲፈፀምባቸው እየተስተዋለ ነው፡፡ እነዚህ መሰረተ ልማቶች ጉዳት ደርሶባቸው ከሥራ ውጪ ሲሆኑ ለመጠገን የሚያስፈልገው ከፍተኛ ወጪ እንደተጠበቀ ሆኖ ተገልጋዩ ሕብረተሰብም ተገቢውን አገልግሎት እንዳያገኝ ይሆናል፡፡ በዚህ አጭር ፅሑፍ ስለመሰረተ ልማት ምንነት፣ በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ ስለሚኖረው የህግ ተጠያቂነት እንዳስሳለን፡፡

የመሰረተ ልማት ምንነት

በአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀፅ 31(2) ስልጣንና ተግባሩ ወደ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የተላለፈው የፌደራል የተቀናጀ መሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 857/2006 አንቀፅ 2(1) ስር “መሰረተ ልማት ማለት ከመሬት በላይ ወይም ከመሬት በታች ያለ መንገድ፣ የባቡር ሀዲድ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኤሌክተሪክ ኃይል፣ መስኖ፣ የውሀ መስመር ወይም የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ሲሆን ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎችንም ይጨምራል” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ ሕግ አተረጓጎም መሰረት “…ሌሎች ግንባታዎችንም ይጨምራል” የሚለው አገላለፅ የሚያሳየን በትርጉሙ ላይ የተካተቱት ብቻ ሳይሆኑ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ለሕዝብ መገልገያነት የተሰሩ ስራዎችም በመሰረተ ልማትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ መሆናቸውን ነው፡፡
መሰረተ ልማቶች እንደሚሰጡት የአገልግሎት ዓይነትና እንደተገነቡበት ዓላማ በርካታ ናቸው፡፡ በዚህም የትራንሰፖርት መሰረተ ልማት፣ የሀይል መሰረተ ልማት፣ የዉሃ መሰረተ ልማት፣ የመገናኛ መሰረተ ልማት፣ የቆሻሻ መስወገጃ መሰረተ ልማት ወዘተ ተብለው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

በመሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችና የሚስከትሉት የሕግ ተጠያቂነት

መሰረተ ልማቶች ከመገንባት ጎን ለጎን ጥበቃ ካልተደረገላቸው የታሰበላቸውን አገልግሎት ሊሰጡ አይችሉም፡፡ በመሆኑም በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል እና ጉዳት በሚያደርሱ አካላት ላይ የህግ ተጠያቂነት ማስፈን አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በወንጀል ሕጋችና በሌሎች አዋጆች ለመሰረተ ልማቶች የተሰጠዉን ጥበቃ እና በአጥፊዎች ላይ የሚያስከትሉትን ቅጣት እንመለከታለን፡፡

በወንጀል ሕጉ ለሕዝብ ጥቅም በተቋቋሙ ግዙፍ ስራዎችና አገልግሎቶች ላይ ጉዳት ማድረስ በሚልስ ርእስ ስር በአንቀፅ 505 ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ወይም ስራ ላይ የዋሉ የየብስ፣ የውሃ፣ የባህር፣ ወይም የአየር ማመላለሻዎች ወይም መገናኛዎች እንዲሁም እነዚህን ለማደስ፣ ለመጠገን፣ እንደገና ለመስራት ወይም አገልግሎት ላይ ለማዋል የሚጠቅሙ የግንባታ ስራዎችን ጭምር አስቦ መደበኛ አሰራር መከልከል፣ ማወክ ወይም ማሰናከል በቀላል እስራትና በመቀጮ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜም ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም ለፖስታ፣ ለቴሌግራፍ፣ ለስልክ ግንኙነት ወይም ለቴሌኮሙኒኬሽን በጠቅላላው ወይም የውሃ፣ የመብራት፣ የጋዝ፣ የኃይል ወይም የሙቀት አገልግሎት ለሕዝብ ለማቅረብ የተቋቋሙ ተቋማትን መደበኛ አሰራር መከልከል፣ ማወክ ወይም ማሰናከል ተመሳሳይ ቅጣት የሚያስቀጣ ነው፡፡

ማንኛውም ሰው በመንገድ፣ በባቡር ሀዲድ፣ በውሃ ወይም በአየር ላይ የሚደረግ የሕዝብ ወይም የዕቃ ማጓጓዝ አገልግሎትን ለግጭት፣ ከሀዲድ ለማስወጣት፣ ለስጥመት ወይም ለማንኛውም ሌላ አደጋ ለማጋለጥ አስቦ ድልድይን፣ ግድብን፣ የማዕበል ማገጃን፣ የተቋቋመ ግዙፍ ስራን ወይም የመቆጣጠሪያ ምልክት ማሳያና የመሳሰሉትን ያበላሸ፣ ከቦታው ያዛወረ፣ ያፈረሰ ወይም እንዳያገለግል ያደረገ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ይህ ድርጊት የሰውን ሕይወት፣ አካል ወይም ጤንነት አደጋ ላይ ከጣለ ወይም በንብረት ላይ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ከሆነ ወይም ድርጊቱን የፈፀመው ፈፃሚው የሙያ ወይም የውል ግዴታውን በመጣስ ከሆነ ቅጣቱ ከብዶ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ አስራት የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡ እንዲሁም ድርጊቱ ለበረራ ወይም ለባህር ላይ ጉዞ ደህንነት የሚያገለግሉ ተቋማት ወይም መሳሪያዎች ላይ ጉዳት በማድረስ በበረራ ላይ ያለ አውሮፕላንን ወይም በጉዞ ላይ ያለ መርከብን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ቅጣቱ ከ15 እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚሆን ከወንጀል ህጉ አንቀፅ 506 መረዳት ይቻላል፡፡ የእነዚህ ድንጋጌዎች ማክበጃ አንቀፅ 512 ላይ የሚገኝ ሲሆን ከላይ የገለፅናቸው ድርጊቶች ሲፈፀሙ የሰው ሕይወት፣ አካል ወይም ጤንነት ላይ ጉዳት ከደረሰ ቅጣቱ ከ10 እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት ብሎም ነገሩ ከባድ ከሆነ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡ እነዚህ ወንጀሎች ሆን ተብሎም ሆነ በቸልተኝነት ቢፈፀሙ የሚስጠይቁ መሆኑ በድንጋጌው ተካቷል፡፡

በተያያዘም በሕግ የተደነገጉትን የጥንቃቄ ደንቦችን በመተላለፍ በተለይም በባቡር መሰረት ልማቶች አቅራቢያ የሚከናወኑ የግንባታ፣ የቁፋሮ ወይም ተመሳሳይ ሥራዎችን፣ ወይም የባቡር መሰረተ-ልማቶችን ከላይ ወይም ከስር አቋርጠው ወይም በትይዩ የሚከናወኑ መሰረተ-ልማቶችን በተመለከተ የወጡ ሕጎችን በመተላለፍ በባቡር ትራንስፖርት ላይ የደህንነት ስጋት እንዲፈጠር ያደረገ ሰው ከ5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከብር 100,000 በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ በባቡር ትራንስፖርት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1048/2009 አንቀፅ 41 በግልፅ ተደንግጓል፡፡ የተፈፀመው የወንጀል ድርጊት የባቡር አደጋ እንዲደርስ በማድረግ ሞትን ወይም ከባድ የአካል ጉዳትን አስከትሎ እንደሆነ ወይም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ጉዳትን አስከትሎ እንደሆነ የእስራት ቅጣቱ እስከ 20 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚሆን ድንጋጌው ያመለክታል፡፡

በሌላ በኩል ማንም ሰው በሰዎች ወይም በንብረት ላይ አደጋ ለማድረስ አስቦ ኤሌክትሪክን ወይም ውሃን የሚመለከቱ ህንፃዎችን፣ የተፈጥሮ ኃይልን ለመከላከል የተሰሩ ስራዎችን፣ በተለይም ቧንቧዎችን፣ ቦዮችን፣ ማጠራቀሚያዎችን፣ የውሃ ማገጃዎችን፣ መልቀቂያዎችን ወይም ማዕበል ማገጃዎችን ያበላሸ ወይም ያፈረሰ እንደሆነ ከ10 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ በወንጀል ህግ አንቀፅ 496 እና 494 ላይ ተደንግጓል፡፡

በተለያየ ምክንያት ከዚህ በላይ በተገለፁት ድንጋጌዎች ስር ሊካተቱ የማይችሉ ማለትም በሕዝቡ ጠባቂነት በመተማመን ያለጠባቂ የሚኖር ሕንፃ፣ ሐውልት፣ ታሪካዊ የሆነ ስፍራ፣ ወይም ለሕዝብ አገልግሎት፣ ለአገር ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ የተተከለ የመሳሪያ ተቋም፣ የተዘረጋ የቴሌ ወይም የመብራት ኃይል መስመር ወይም እርሻ ያወደመ ወይም ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሰው ከ10 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ወይም ነገሩ ከባድ በሚሆን ጊዜ ከ10 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ በወንጀል ህጉ 690(2) ስር ተደንግጓል፡፡

የመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ከማድረስና ከማውደም በመለስ እንደስርቆት ዓይነት ወንጀሎችም ሲፈፀሙ በወንጀል ሕጉ በከባድ ሁኔታ ታይቶ በአንቀፅ 669(1)(ለ) ቅጣት ተቀምጦለታል፡፡ በዚህም የማይገባውን ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ለቴሌኮሚኒካሽን፣ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለውሃና ፍሳሽ ወይም ለማናቸውም ሌላ ድርጅት አገልግሎት የሚውል ጠባቂ የሌለውን መሳሪያ ወይም ዕቃ የሰረቀ ሰው ከ1 ዓመት የማያንስ ቀላል እስራት ወይም ከ15 ዓመት የማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የቴሌኮምንኬሽንና የኤሌክትሪክ አዉታሮችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፈጣን እድገት ከማምጣት አንጻርና ለማስፋፋት ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ በመላ ሀገሪቱ ተሰራጭተዉ የሚገኙና ለጥቃት የተጋለጡ ከመሆናቸዉ ጋር ተያይዞ ለአፍታ እንኳን ቢቋረጡ በብሄራዊ ጥቅም ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የተለየ ጥበቃ ለመስጠት በማሰብ የፈደራልና የክልል መንግስታት የመጠበቅ ሀላፊነት እንዲኖርባቸዉ ያደረገዉን አዋጅ ቁጥር 464/1997ን እናገኛለን፡፡ በዚህ አዋጅ ዉስጥ የሀገር ደህንነትን ወይም ኢኮኖሚን በሚጎዳ ሁኔታ በቴሌኮምንኬሽን ወይም በኤሌክትሪክ አዉታር ላይ የስርቆት ተግባር የፈጸመ ወይም ሆነ ብሎ ጉዳት ያደረሰ ወይም አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ያደረገ ማንኛዉም ሰዉ አግባብ ባለዉ የወንጀል ህግ የበለጠ የሚቀጣ ካልሆነ በቀር ከ5 ዓመት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ሲሆን ድርጊቱን የፈፀመው በቸልተኝነት ከሆነ ከ6 ወር እስከ 5 አመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ በአንቀጽ 4 ላይ ተደንግጓል፡፡

በመሰረተ ልማትን በማስፋፋት ሂደት አስፈፃሚ አካላት ያለባቸው ሀላፊነት

የመንግስት ተቋማትም የራሳቸውን የስራ ድርሻ ለመወጣት ሲሉ በሚያከናውኗቸው የልማት ስራዎች ምክንያት ሌላ መሰረተ ልማት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ሲደርስ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በአዋጅ ቁጥር 857/06 አንቀፅ 14(3) እና (4) እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀፅ 31(2) መሰረት እያንዳንዱ አስፈፃሚ አካል የመሰረተ ልማት ስራ ለማካሄድ በሌሎች የመንግስት አካላት የሚሰጡት የመሰረተ ልማት ፈቃዶች እንደተጠበቁ ሆነው ስራውን ከመጀመሩ በፊት ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ፈቃድ ማግኘት እንዳለበትና ስራውን በሚያካሂድበትም ወቅት ከሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ያልተጣጣመ ሆኖ ካገኘው በፍጥነት ለሚኒስቴሩ ማሳወቅ እንደሚኖርበት ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም አስፈፃሚ አካላት ይህንን የህግ ሂደት መከተል ይጠበቅባቸዋል፡፡

ማጠቃለያ

በዚህ ፅሑፍ የመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል የሚያስችሉ ደርሶም ሲገኝ ተመጣጠኝ ቅጣትን የሚጥሉ የወንጀል ሕጉን ጨምሮ የተለያዩ አዋጆች መኖራቸውን ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ ሆኖም የመሰረተ ልማቶችን በአግባቡ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ሕግ በማውጣት ብቻ ስኬታማ ስራ መስራት አይቻልም፡፡ ይልቁንም ሕብረተሰቡ የእኔነት ስሜት ተሰምቶት በአግባቡ መጠበቅና መጠቀም የሚኖርበት ሲሆን የመንግስት አካላትም እንዲሁም ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚመለከቱ መሰረተ ልማቶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አንድን መሰረተ ልማት ለመገንባት ሌላ መሰረተ ልማትን ከመጉዳት መቆጠብና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

You may also like...

Leave a Reply