‘የእሳት ቀለበት’

‘የእሳት ቀለበት’ የመጽሐፍ ርእስ ነው። ለንባብ ከበቃ ገና አንድ ወር ‘ንኳ አልሞላውም። ከዋናው ርእስ ሥር ‘የሕግ ማስከበር ዘመቻ ንፍቀ መዋዕል- ቅጽ 1’ የሚል መግለጫ ታክሎበታል። የተዘጋጀው በቡድን ነው። ቡድኑ፤ የተለያየ ተዋረዳዊ ሚና ያላቸውን ኹለት አስተባባሪዎች (ኮሎኔሎች)፣ እና ሦስት አዘጋጆችን አካትቷል። የመጽሐፉ ዋና አካል በ360 ገጾች ተቀንብቧል።

ይኽ መጽሐፍ ትሕነግ በሰሜን ዕዝን ላይ ያደረሰውን ጥቃት፣ ጭፍጨፋ፣ ወደር የሌለው ጭካኔና ክህደት ከጥንተ ታሪኩ እስከ ዕለተ ድርጊቱ ብሎም የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ምን ይመስል እንደነበር ይተርካል።

በምዕራፍ አንድ የትሕነግ  ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ያዘለውን ሰይጣናዊ እና መሰሪያዊ ዕሳቤ ያስቃኛል። የትሕነግን የ’68 ማኒፌስቶ ከሒትለር ‘ማይ ካምፍ’ መጽሐፍ በማነጻጸር ጭምር ያቀርባል። የክህደቱን፣ የባንዳነቱን፣ የፀረ ኢትዮጵያዊነቱን ታሪክ በአብነት ይዘክራል። ትሕነግ ‘ትግራዋይ’ የሚለውን አጠራር ለምን እንደፈጠረች ሰይጣናዊ ምክንያታቸውን የቃሉን ድብቅ ይዘትና ምንነት ያብራራል።

በምዕራፍ ኹለት፣ የትሕነግን ከምሥረታ ጀምሮ እስከ አራት ኪሎ፣ አራት ኪሎ ኾነ የፈጸመውን ግፍ በጨረፍታ፣ መቀሌ መሽጎ ስለፈጸማቸው ግፎችና በደሎች፣ ስላቀዳቸውና ስለሞከራቸው መፈንቅለ መንግሥቶች፣ የጦርነት ዝግጅቶች፣ የጥቅምት 24 ጥቃት እና የሕግ ማስከበር ዘመቻው ተጀምሮ መቀሌ እስኪደረስ የነበረውን ታሪክ ይዘግባል። በዚህ ክፍል ከእዚህ ቀደም ያልተነገሩ (ቢያንስ በሚዲያ) ታሪኮችንም አካትቷል።

በተለይ ከትሕነግ ዝግጅት አንጻር እና መከላከያ ሠራዊቱ ከተዋቀረበትና ከተደራጀበት እንዲኹም ከሰው ኃይል ስብጥሩና ቁጥር እንድኹም ከትጥቅ አኳያ የነበረውን አስቸጋሪና ፈታኝ ኹኔታ ምን ይመስል እንደነበር በዝርዝር ይተርካል።

ከ250 ሺ በላይ የሚገመተው የትሕነግ ልዩ ኃይል፣ ከመከላከያና ከፌደራል ፖሊስ ተመላሽና ጡረተኛ፣ የዞባ ሚኒሻ ወዘተ ፤ እና በወገን በኩል በወቅቱ ከነበረው 44ሺ የማይበልጥ የመከላከያ ሠራዊት አንጻር የተፈጸመውን ጀብድ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ትሕነግ ጥቅምት 27 ሰሜን ዕዝን ለማጥቃት አቅዳ፣ ለምን ወደ 24 እንደቀየረችና በተመሳሳይ ስዓት በ200 ቦታዎች ጥቃት በመክፈት የደረሰውን ጉዳትና የወገን ኃይል አስደማሚ ተጋድሎዎችን ይተርካል። ከዚያም መልሶ በመቋቋም የፀረ ማጥቃት ዘመቻዎችን በማጧጧፍ መቀሌ እንዴት እንደተገባ ይዘግባል።

See also  "ህሊናን የሚፈታተን" የተባለ ሪፖርት ይፋ ሆነ - አማራ ክልል በተወረረበት ወቅት ግብረርሰዶም መፈጸሙ ተገለጸ

ምዕራፍ ሦስት፣ በየዐውደ ግንባሩ የተፈጸሙ ውጊያዎችን በአብዝኃኛው ዕዞችን፣ ክፍለ ጦሮችን፣ ብርጌዶችና ሻለቃዎችን እንዲሁም የእግረኛ፣ የሜካናይዝድ፣የዓየር ኃይልና የሎጂስቲክስ (ስንቅ፣ትጥቅ፣የሰው ኃይል፣ ሕክምና ወዘተ) አቅራቢ የሥራ ክፍሎችን መሠረት በማድረግ ዜና መዋዕላቸው ቀርቧል። መቀሌ ከተገባ በኋላም ሠራዊቱ ትግራይ ውስጥ በቆየባቸው ጊዜያት ሲያከናውናቸው የነበሩ ዘመቻዎችን (ከመደበኛ ውጊያ እስከ ሽምቅ ውጊያ እና የፀረ ሽፍታ ለቀማና አሰሳ) ዘርዘር ባለ መልኩ ይተርካል።

በሦስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ የቀረበው ይኽ ‘የእሳት ቀለበት’ የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ከጥንተ መነሻው ጀምሮ መከላከያ ሠራዊቱ የትግራይ ክልልን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት የነበረውን ጊዜ ይሸፍናል። ብዙ ቋጠሮዎችን ያፍታታል። ስለገጠሙን ፈተናዎችና እንዴት እንደታለፉ፣ ወደፊትም ምን መደረግ እንዳለበት ጭምር ጠቋሚ ነው።

[በመጽሐፉ ምዕራፍ ሦስት ውስጥ የተካተቱት ታሪኮችን የመከላከያ ሠራዊቱን የተለያየ አደረጃጀት መሠረት አድርጎ ከማቅረብ ይልቅ ዓውደ ውጊያዎችንና ግንባሮችን መሠረት በማድረግ የተሳታፊዎቹን ማንነት፣ የፈጸሙትንና የተፈጸመባቸውን ኹነት በመግለጽ ቢተረክ የተሻለ ነበር፤ የሚል ብጣቂ ግላዊ አስተያየት አለኝ።]

ይኽን መጽሐፍ የማንበብ አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ ኹሉ ሊያነበው ይገባል። የተካኼደውን ጦርነት በተሻለ ኹኔታ ለመረዳት ወሳኝ መጽሐፍ ነው። ሥነጹሑፋዊ ለዛውም ግሩም ነው። የዚህ መጽሐፍ ቅጽ -2 በቅርቡ ለንባብ ይቀርባል ብለን እንጠብቃለን።

Wobeshet

Leave a Reply