በጋምቤላ የሽብር ጥቃት ፈጽመዋል ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

ከኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በመቀናጀት በጋምቤላ ከተማ በሰላማዊ ዜጎችና የጸጥታ አካላት ላይ የሽብር ጥቃት ፈጽመዋል፤ በንብረት ላይም ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ክስ የተመሰረተባቸው 9 ተከሳሾች የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ/ም ከኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በመቀናጀት በጋምቤላ ከተማ በሰላማዊ ዜጎችና የጸጥታ አካላት ላይ የሽብር ጥቃት ፈጽመዋል በንብረት ላይም ጉዳት አድርሰዋል ባላቸው 9 ተከሳሾች በፈጸሙት የሽብር ወንጀል ላይ ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስታውሰው ተከሳሾች እራሱን የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) በማለት በሚጠራው ቡድን አባል በመሆን እና ከኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን ጋር በመቀናጀትና መሰረታዊ የውትድርና ስልጠና ለ3 ወራት በመውሰድ እና የጦር መሳሪያ በመታጠቅ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ/ም ከንጋቱ 11:30 ጋንቤላ ከተማ በመግባት በክልሉ ምክር ቤት አካባቢ እና የፌዴራል ፖሊስ መኖሪያ ካምፕ እንዲሁም በክልሉ ልዩ ኃይል ላይ በጦር መሳሪያ ተኩስ በመክፈት የ6 ንፁሃን ህይወት እንዲያልፍ ያደረጉ ሲሆን ሌሎች 8 ንፁኃኖች ደግሞ መቁሰላቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም በዚህ የሽብር ጥቃት ላይ 8 የመንግስት ታጣቂዎች ህይወት ማለፉን 28 የሚሆኑ የመንግስት ታጣቂዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ብሎም የዋጋ ግምታቸው 3 ሚሊዬን 212 ሺህ ብር የሆነ የመንግስትና የግለሰብ ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ በክሱ ተጠቅሷል።

ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀርበው ክሳቸው ከተነበበላቸው በኋላ ወንጀሉን መፈጻማቸውንና አለመፈጸማቸውን የዕምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ለህዳር 8 ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም የችሎቱ የስራ ቋንቋ አማረኛ በመሆኑ ከ9ኙ ተከሳሾች 2ቱ ብቻ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሲሰጡ 7 ደግሞ የኑዌር ቋንቋ ተናጋሪ በመሆናቸውና አስተርጓሚ ባለመኖሩ ቃላቸውን ሳይሰጡ በመቅረታቸው ፍርድቤቱ ለዛሬ አስተርጓሚ ተመድቦ ቃለቸውን እንዲሰጡ ትዕዛዝ በሰጠው መሰረት በዛሬው እለት 7ቱም ተከሳሾች ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾች መብታቸውን ጠብቀው የክህደት ቃላቸውን ሰጠው የተከራከሩ መሆኑን ጠቅሶ ወንጀሉን መፈጸማቸውን ያስረዳሉ ያላቸውን 31 የሰው ምስክሮች አቅርቦ ለማሰማት ለምስክሮች መጥሪያ ወጥቶ እንዲደርሳቸውና የፌዴራል ፖሊስ እንዲያቀርባቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡

See also  የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ ምን እያሉ ነው? ምን አሉ?

ጉዳዩን የሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ-ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎትም የምስክሮችን ቃል ለመስማት ከህዳር 27 እስከ ታህሳስ 11/4/2015 ዓ.ም ድረስ ቀጠሮ ሰጥቷል፡

Federal justice minister

Leave a Reply