ትህነግ ላረደው ሰራዊት “ኤርትራን ውጋልን”ሲል ማልቀሱ የ”እንበትናችኋለን” አዲስ ዘመቻ?

ትልቁን ሚስጢር ጻድቃን ነግረውናል። ይህ ሂደት “የተሰበሰቡትን መበተኛ ነው” ሲሉ ነው የነገሩን። የተሰበሰቡትና ይበተናሉ የተባሉት ሃይሎች ደግሞ ኤርትራ፣ አማራና አፋር ናቸው። እነዚህን ሃይሎች ይበተናሉ የተባሉት ደግሞ በትግርኛ ቋንቋ ለትግራይ ህዝብና ተወላጆች ነው። ይህ የተባለው የሰላም ስምምነቱን ለምን ፈረማችሁ በተባሉ ቅጽበትና ማብራሪያ እንዲሰጡ ተገፍተው ነው። ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ እንደ ዘዴ የተያዘው ፕሮፓጋንዳ ነው። የተናበበ ዘመቻም ተከፍቷል። ዘመቻው በፕሬቶሪያው ስምምነት መሰረት ያልተካተተ አዲስ አሳብ በማዋላድ የሚተገበር ነው። እሱም ኤርትራን፣ አፋርንና አማራን ከመንግስት ጋር የሚያጣላ ነው። ይህም አካሄድ ከናይሮቢው ቀጣይ የትግበራ ውል በሁዋላ “የአማራና የአፋር እንዲሁም የኤርትራን ሃይሎች መከላከያ ከትግራይ አስቀድሞ ያስወጣ” በሚል እንደ ቅድመ ሁኔታ ማልቀስና በማስለቀስ የታጀበና መከላከያ እነዚህ ሃይሎች ላይ ጥይት እንዲተኩስ፣ እና እንዲጋጭ ምኞት መሆኑ ነው። መከላከያ ያደቀቅወና ጥምር ጦሩ አልሞ የወቀጠው ትህነግ በዚች የጉሊት ፖለቲካ ኤርትራና ኢትዮጵያን አጣልቶ፣ አማራና መንግስትን አቃቅሮ እሳት ሊሞቅና የወላለቀ ጥርሱን ሊጠግን ሚጎመዥም አይሆንም። የግል አስተያየቴ ቢሆንም መከላከያም መንግስትም፣ አማራም፣ አፋርም ሁሉም የኤርትራን ውለታ በቀጣይ ያሳድጉታል እንጂ ለአራጁ ትህነግ ሲሉ አያደበዝዙትም። ትህነግ ቅዠቱን ታቅፎ …


የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ ከለውጡ ጀምሮ ለውጡን ከሚቃወሙ በስተቀር ለኢትዮጵያ ቁልፍ ባለውላታ እንደሆኑ ስምምነት አለ። መንግስትም በግልጽ ዓለም እየሰማ ” በክፉ ጊዜ ገበናችን የሸፈኑ” ሲል አወድሷቸዋል። ” ከኤርትራ ጋር ሰላም ባንፈጥር ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡት” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በይፋ መናገራቸው ይታወሳል። ከዚሁ ጋር ተዳምሮ የዶክተር አብይን ፍጥነትና ቀድሞ አሳቢነት መካድም አይቻልም።

ከተገፉበት የተመለሱት ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌም ጦሩን ካዩ በሁዋላ ድርጊቱ እንዴት እንደተቀናበረና ውጤቱም ምን እንደሆነ ምንም ሳያስቀሩ ለህዝብ ደማቸው እየተንተከተከ ይፋ ሲያደርጉ ሕዝብ በያለበት ሃዘን እንዲቀመጥና ከንፈሩን እንዲመጥ አድርጓል። ትህነግን ስም እየሰጠ ” አጀብ” ብልሏል። ረግሟል። ክፉ ስሜት እንዲያረግዝ ሆኗል። ጥላቻው ከቁጥጥሩ አልፏል። በዚሁ ስሜትና እልህ ገፊነት ቤተሰብ ልጁን መርቆ መለዮ ለባሽ እንዲሆን በዕልልታ ሸኝቷል። ይህ እውነት ነው። ይህ አይካድም። ብዙ ማደናገሪያ ቢቀርብም ሕዝብ ” ጥሪ አይቀበልም” ብሎ ላይሰማ ምሏል።

መተከያ የሌላቸውን ህይወታቸውን እርባነ ቢስ፣ የመሃይም፣ ኋላ ቀር፣ ክፋት የተሞላው፣ ድምሩ ኪሳራና ሸፍጥ ለሆነው የባድመ ጦርነት ከሰውት ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ተርፈው ሃያ ሁለት ዓመት የኢትዮጵያን ድንበር ሲጠብቁ የኖሩትን የመከላከያ አባላት በክህደት መታረዳቸው ሲሰማ፣ ለምስክርነት የተረፉ እያነቡ ምን እንደተፈጠረና ምን እንድተከናወነባቸው ሲመሰክሩ “ይህ የሆነው በማን? ማን ላይ? የት? ” የሚሉ ጥያቄዎች በማንሳት ለማመን የሚያቅት ትህንግርት ሆነ። ለመቀበል የሚከብድ፣ በግፍነት ታሪክ ትልቁና በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ልብ ታትሞ የሚቆይ የዘመኑ ጥቁር ጠባሳ ሆነ።

የክህደቱ ጦርነት ካሰናበታቸው መካከል አቶ ሴኮ ቱሬ በትግራይ ቴሌቪዥን ወጥተው “በአርባ አምስት ደቂቃ ኦፕሬሽን እንዳይሆኑ አደረግናቸው። የተደመሰሰውም ተደመሰሰ …” በኩራት መናገራቸውን ተከትሎ፣ ኤርትራ ራቁታቸውን የተሰደዱ፣ የቆሰሉና ውሃ ጥም ያነደዳቸውን ተቀብላ አልብሳና ውሃ አጠጥታ ዳግም እንዲደራጁ ማድረጓን ምክትል ኤታማዦር ሹም አበባው ታደሰ በዓይናቸው ሲያዩ ” አልመለስም” ብለው እዛው መቅረታቸውና አዝማች መሆናቸው ይፋ ሆነ። የተከዳውን ጦር ዳግም አደራጅተው ውጊያ እንደገቡ ተሰማ። ውጊያው ቀድሞ በሴራና በተንኮል ተዋቅሮ በተከዳው ጥቂት ጦርና ትህንግ በገነባው ግዙፍ ሃይል መካከል በመሳሪያ ብዛትም በማይመጣጠን ደረጃ ውጊያው ጋመ። ይህ በአደባባይ ያየነው፣ በመቀለ ስታዲየም የነበረውን የወታደር ዝግጅት ራሱ ትህነግ አስኮምኩሞናል። የአገር መከላከያን ሰራዊት ትጥቅ በሙሉ እጃቸው ማስገባታቸውንና አስቀድመው በአካል ኢትዮጵያን እየመሩ በመንፈስ “ታላቋን ትግራይ” ሲገነቡ ጋራ ምሰው የቀበሩትን መሳሪያ ሳይቀር መጠቀማቸው ከልሉ አልፎ አማራ ክልል ተራራዎች ያጋፈጡት ሃቅ ነው። ያም ሆኖ ይህ…

ስልጣን በያዙ ማግስት አየር ሃይልን የአይናቸው ብሌን ያህል ዋጋ የሚሰጡት አብይ አሕመድ፣ የኢትዮጵያ ጦር አንድ ለአምስት በቁጥርና መሳሪያ ብልጫ የገጠመውን ጦርነት በድሮን ከሰማይ በማጀብና ፋታ በመንሳት በሁለት ሳምንት “ጦርነት ባህሌ ነው” በሚል ፕሮፓጋንዳ አብጦ የነበረውን ትህነግ ሰባበሩት። ጻድቃንም ” ለማሰቢያና መልሶ ለመደራጀት እንኳን ፋታ አሳጡን” ያሉት ይህ ጦርነት የኢሳያስ አፉወርቅ ድጋፍ እንዳለበት አይካድም። ሊካድም አይችልም።

አቶ መለስ ኤርትራን በማዕቀብ አሽመድምዶ በማሟሟት እንደሚጠቀልሏት ሂሳብ ሰርተው በተከተሉት ስልት ክህደት እንደተፈጸመበት ደጋግሞ ሲገልጽና ሲጮህ የቆየው ኡኢሳያስ ሻዕቢያ፣ አጋታሚውን “እልል በቅምጤ” አድርጎት ትህነግን አዳሸቀው። ወደፊት ይፋ የሚሆኑ በርካታ ኪሳራ አደረሰበት። ዛሬ ላይ ትህነግ ለደረሰበት የከፋ ውድቀት ዳረገው። አቅም አልባና የተባለውን ሁሉ የሚፈጽም ልምሻ የያዘው ድርጅት እንዲህን ትልቅ ሚና ተጫወተ። ይህም አይካድም። ዛሬ ትህነግ ኢሳያስን ከስልጣን በሃይል ለማውረድ መሞከር ቀርቶ ማሰብ እንኳን ተስኖታል። ይህ እውነት ነው። “ቀድም ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፣ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማለቀስ” እንዲሉ!!

See also  ሃብትና የገቢ ምንጭ "አናስመዘግብም" ያሉ 62 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ሰራተኞች በህግ ሊጠየቁ ነው

የትህነግ የፖለቲካ ሽንፈት ራሱ በለኮሰውና እንደ ለኮሰው ሊክድ በማይችልበት መልኩ የገባበትን ጦርነት ባላሰበው መልኩ አንጋፋ መሪዎቹን አስበልቶ፣ አቅሙን አመናምኖ ወደ በረሃ ገባ። የተቀረቀረው በር ተከፍቶላቸው በክብር ” ኢሱ “አዲስ አበባ ተጨብጭቦላቸው ጋለቡ። ደነሱ። ቤተመንግስት ተንሸራሸሩ። በፖለቲካውም መስክ ብዙ ጉዳዮች በሽርክና አከናወኑ። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ትህነግ ይከተለው በነበረው ፖለቲካ ሳቢያ የተለያዩ ቤተሰቦች ተገናኙ። ነገሮች ሁሉ በማይታመን ቅጽበት አብረቀረቁ። ይህ ያልተመቸው ትህነግ ክልል ሆኖ መኖር ሞት ሆኖበት ባፈረጠመው ጡንቻው መከላከያን አርዶ ዳግም ቤተመንግስት ሊገባ ቢጎመጅም፣ በስተመጨረሻ ራሱን በኪሳራ ቀድሞ በተፈጠረበት ቁርበት ላይ አገኘው። ደደቢት!!

ይህን አስልቶ ነው መሰል ቴዎድሮስ የሚባለው የርዕዮት ሚዲያ ባለቤትና የትህነግ አጥቂ ” ካርቶን ራሶች፣ ከካርቶናቸው ወጥተው ማሰብ የማይችሉ” ሲል ከአዲስ አበባ አኩርፈው መሄዳቸው ሲያልቅ ገብቶት የፖለቲካ ውድቀት ሲል ትህነግን ክፉኛ ነቀፈ። በነገራችን ላይ ቴዎድሮስ ትህነግን እንደቀጠቀጠበት ዓይነት ክፉ ቃላቶች ተጠቅሞ ትህነግን የደበደባቸው ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅምና ጉዳዩ የብስጭት መሆኑ ግልጽ ነው። ምን ይደረግ መቻል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይንም “አውሬ” ሲል ሰይሞ መዘናጠሉ የብስጭቱ ግለት ማሳያ ከመሆን አይልፍም። አብይን አብዛኞች ” እናት አንተን ትውለድ። ጀግና” ይሉዋቸዋል። ለያውም ባማስረጃ። እናም ቴዲን “ቻለው ቻለው” የሚለውን ዘፈን ከመስማት፣ “አይቼሽ ነው ባይኔ ወይስ…” የሚለውን ዘፈን ከመመረቅ በቀር ለጊዜው ሌላ ማራጭ የለም።

ይህ ከትህነግ ጥጋብና በልኩ መኖር አለመቻሉ ያመጣው የክህደት ጣጣ ( በነገራችን ላይ ክህደትን የምደጋግመው ሴኮ ቱሬ፣ ጻድቃንና በወቅቱ እንደ ትህነግ አመራሮች ተስፈኛ የነበሩ የካርቶኑ ውጤቶች ደጋግመው ጀግና ነን ለማለት ያረጋገጡትና ማስረጃው ሊደበቅ የማይችል በመሆኑ ነው) ሳይገባው ሲነዳ የከረመውና አሁንም ድረስ ገሃዱ እውነት እንዲገባው የማይፈልገው የትግራይ ተወላጆች እየተቀጣጠለና ሌሎች ልዩ አላማ ያላቸው የውጭ ሃይሎች በጋራ እያጋሙት የትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ የወደቀው ጦርነት ያደረሰው መከራ ያሳዝናል። ያስቆጫል። ያንገበግባል።

በትህነግን መቀመጫው ውስጥ ሚጥሚጣ ነስንሰው የሚጋልቡት ክፍሎች ትግራይ ባሰማሯቸው “ወሬ ለቃሚ ጋዜጠኖችና” የስም ለጋሽ ድርጅት ሰራተኞች ለዓላማቸው ይበጅ ዘንድ ከትግራይ ሲያሰራጩት የነበረው ምስልና ፊልም ዛሬም ባይሆን ቆየት ብሎ ሃፍረቱ ለልጅ ልጅ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ነገ ሲሰክን ሃቅ ይዘው የሚነሱና ያዩትን የሚመስከሩ ከመንግስት ወገንም ሆነ ከትህነግ፣ እንዲሁም ከጋላቢዎቹ መንደር ያለውን ለህዝብ በሚገባው ቋንቋ የሚያቀርቡ እንደ ቴዎድሮስ አይነት የብስጭት ተሳዳቢዎች ሳይሆኑ በመረጃ የሚጽፉ መነሳታቸው አይቀርምና እዚያ ያድርሰን። እውነትና ጥራት አድሮ ነውና አሁን በገደምዳሜ የሚከላወሰው የልዩነት ወጀብ ምን አልባትም ማዕበል ሆኖ ሃቁን አፍጥኖ ሜዳ ላይ ያሰታውም እንደሆን የሚታይ ነው። ግን እንደ አያያዙ የሚቀር አይመስልም።

ለማንኛውም አሁን ላይ የሰላም ሂደቱ በፊርማ ተሰድሮ፣ አሜሪካ ” መፎረሽ የለም” ብላ ትግበራው በተጀመረበት ሰዓት ” ኤርትራ” የሚለው ዘፈን አሁንም የትግራይ ምስኪን ሕዝብ በንቃት ሊያየው የሚገባ ሃቅ ሆኖ ለዚህ አስተያየት አቅራቢ ይታየዋል። የኤርትራ ጦር ንጽሃን ላይ የሚፈጽመው ጥቃትና ዝርፊያ እውነት ከሆነ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። ግብ ሽሬ፣ አደዋና አክሱም “ህዝብ ምን አለ” ተብሎ ሲጠየቅ ሕዝብማ ይህን አለ” በሚል በሚዲያዎች የምንሰማቸው ምስክርነቶች “ይሄ ሌላ ያ ሌላ ” የሚያሰኙ ናቸው።

እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቼ የማነሳው ጉዳይ ቢኖር ማንም ሆነ ማን፣ ምንም ይሁን ምን፣ የተማረም ይሁን ያልተማረ፣ ዲያስፖራም ይሁን ትግራይ ውስጥ ያለ፣ ሃብታምም ይሁን ደሃ፣ አዋቂም ሆነ ጎላማሳና ህጻን … በባድመ ጉዳይ ቀሪውን የኢትዮጵያን ክፍል ህዝብና አሁን ያለውን መንግስት የመውቀስ፣ ትብብር የመጠየቅ ሞራል የላችሁም። ሊኖራችሁ አይችልም። ሞራል ካገናችሁም ከትህነግ ጋር በሚከተሉት ጉዳዮች ሂሳብ አወራርዱ ውይም በአካባቢው ቋንቋ ” ተገማገሙ፤ ሂስና ግለሂስ” አካሂዱ!!

  • ሰባ ሺህ የሚገመት የኢትዮጵያዊያን ደም የተገበረበት ጦርነት እንዴት ተቋጨ። መለስ ምን አቋም አራመዱ?፡ለምን? እንዴት?
  • መጀመሪያ ባድመ እንደሚወረር ራሳቸው የትህነግ ሰዎች መረጃ ሲሰጡ ማን ዝም አለ? ለምን ዝም አለ? እንዴት ….
  • ሕዝብ ክተት ሲጠራ፣ የደርግ ተብሎ ለልመና የተዳረገው የኢትዮጵያ ሰራዊት ምላሽና ሚና ምን እንደነበር መርመሩ፤
  • በአልጀርሱ ስምምነት እነ መለስ ይዘው የሄዱት መከራከሪያ “አያዋታም፣ ትረታላችሁ” ሲባሉ ለምን ጆሯቸውን ዘግተው በማይረባ መከራከሪያ ለመደራደር ወሰኑ?
  • ውሳኔው “ለኢትዮጵያ ድልን አስገኘ” በሚል ስዩም መስፍን ለምን ዋሹ። ህዝብ ሰልፍ እንዲወጣ ለምን ተደረገ? ይህ ቁማር ለምን አስፈለገ?
  • ውሳኔው ኤርትራን አሸናፊ አድርጎ መቋጨቱ በሰነድ ይፋ ሆኖ ሳለ በሰባ ሺህ ህዝብ አስከሬን ላይ ዳንኪራ መምታት የተፈለገው ለምድን ነበር? ይህንን ያጋለጡ ሲታሰሩና ሲሰደዱ እናነተ የት ነበራችሁ? ለምን ይህ ሁሉ ሲሆን አደባባይ አልተንከባለላችሁም?
  • ይግባኝ የሌለው ውል ተዋውለው አቶ መለስ አስርት ዓመታት ሲመሩና ይህን የተቃወሙ ሲባረሩ ተመረናል የምትሉ የተ ነበር የተኛችሁት?
  • ለውጡ ከመምጣቱ በፊት ኢህአዴግ ቁጭ ብሎ በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት ይፈጸም ብሎ መስማማቱን በቲቪ ሲያስታውቅ የትግራይ ልጆች፣ ምሁሮች፣ ዲያስፖራዎች ጆሮ በአዋጅ እንዲዘጋ ተደርጎ ነው?
  • ይግባኝ የሌለው ውል የፈረመው ትህነግ ሆኖ ሳለ፣ ሰባ ሺህ የሚልቅ ህዝብ ያስጨረሰው ትህነግ ሆኖ ሳለ፣ ተወሰነልን ብሎ የዋሸው ትህነግ ሆኖ ሳለ፣ አሁን ባድመን በሃይል ይዟል የተባለው የኤርትራ ጦር እንዳይገባ ሲከላከል የነበረውን የሰሜን ዕዝ ያረደውና በጅግንነት የክህደት ዕርድ መፈጸሙን የገለጸው ትህነግ ሆኖ ሳለ፣ በምን ሂሳብ ነው ዳግም መከላከያ ባድመ ሄዶ እንዲዋጋ የሚጠበቀው? ማንንስ ነው የሚወጋው? ትህነግ ሲያርደውና እርቃኑን ሲያስቀረው ሃፍረቱን የሸፈነለትን? ብዙ የሚመረመሩ ጉዳዮች አሉ ላብቃ። ግን ያማል። በትህነግ ያልታመመ የለም። ስለምን ትህነግ የአንድ ትውልድ እድሜ ሙሉውን አገር ያውካል? ለምንስ በትግራይ ሕዝብ ስም ያውካል? እንዴት ነው የትግራይ ህዝብ “በስሜ አትግደል፣ አትውረር፣ አታውክ” የሚል ትውልድ ያጣው? ይህ ትውልድስ ምን ፈርዶበት ነው በትህነግ እድሜ ልኩን ሲታወክ የሚኖረው? የትግራይ ህዝብስ እንዴት የተለየ አማራጭ እንዲመለከት አይደረግም? በቀደምው ትግል የትግራይ ልጆች ሞቱ። ቤተመንግስት ተገባና ለሞቱት ምክንያት ሆነ። በባድመ ላላቁት ሰባ ሺህና ከዚያ በላይ ዜጎች ለምን ምክንያት አይጠየቅም? ሰባ ሺህ ህዝብ አስጨርሶ በኪሳራ መጨባበጥ ለትህነግ ጨዋታው ነው። በዚህ አራት ዓመታት አማራ ክልል ድረስ፣ አፋር ክልል ድረስ ዘልቀው ስንት የትግራይ ልጆች አለቁ? ካለቁስ በሁዋላ ምን ተገኘ? ይህ እንዴት አይጠየቅም? በሶሰተኛው ጦርነት ስድስት መቶ ሺህ የላማት ሃይል የሚሆኑ ወታቶች አልቀዋል እየተባለ ነው ለምን ህዝብ አይጠይቅም? የትግራይ እናት የምትወልዳቸውን ልጆች ትህነግ እንዲያስገድላቸው ውል ገብታም ከሆነ ይፋ ይሆን። ለማንኛውም ከካርቶኑ መውታት ግድ ነው።
See also  ከሳኡዲ «ሀቁን ከመንግሥት ችግር ጋር ለይቼ ምንም ሳልደብቅ ልንገራችሁ»

ወደ መቋጫ

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ዛሬም፣ ነገም ወደፊትም ለትግራይ ምስኪኖች ያዝናል። የትህነግ አመራሮች ያሰረጹት ማመዛዘን የሚባለውን የሰዎች መለያ መሳሪያ እንዴት ማምክን እንደሚቻል ሲያስብ ሃዘኑ ድርብ ይሆናል። ዘረኛነት በሚዛን እንዳናስብ የሚያደርግ መድሃኒት አልባ የልብና የአንጎል ተውሳክ ነው። የትግራይ ሕዝብ ከጎረቤቶች ሁሉ ጋር ጠላት ሆኖ እንዲኖር የተፈረደበትንና ይህን ፍርድ የሚፈረዱበት ሰዎች ዓላማ ምን እንደሆነ፣ ዓላማው ቅዠት ነው ወይስ የሚሳካ? ብሎ የሚያስብ ትውልድ እንዳይነሳ አንቆ የያዘው ይህ ተውሳክ እንዴት ይነቀል ይሆን?

የትግራይ ሕዝብ ውሳኔ ከሆነ ትግራይ አገርም ትሁን። ግን አማራ የሚባለውን ህዝብ፣ የኤርትራን ሕዝብ፣ የአፋርን ጎረቤት ህዝብ ጠላት አድርጎ እስከመቼ ይዘለቃል? ምን የሚሉትስ የፖለቲካ አተያይ ነው እንዲህ ያለው እውርነት። ትናንት ነፍጠኛ በሚል ስያሜ አማራን ፈርጆ በኖረበትን ሃብት ባፈራበት አካባቢ ሁሉ እንደ ዶሮ አንገቱ እየተቀነጠሰ፣ ንብረቱ እየተዘረፈ በቡድንና በተናጠል ሲፈናቀል የነበረው በማንና በምን ምክንያት እንደሆነ እየታወቀ፣ በፓርቲ መተዳደሪያ መርህ ሳይቀር ” አማራ ጠላት ነው፤ እሳትና ጭድ የሆነ ህዝብ ያልተጋደለው በእኛ ስህተት ነው ወዘተ” እየተባለ በመንግስት ሚዲያ ሲቀርብ እንዳልነበር፣ በቅርቡም “ሂሳብ እናወራድብሃለን” በሚል መከራውን ሲያይ የኖረን ህዝብ ” ከአማራ ጋር ችግር የለብንም” ብሎ ገመድ ሲያጥርና ማጣፊያው ሲጎመድ መሳለቅ እውን ለትግራይ ሕዝብ ነገ መላካም ጎረቤት እንዲያበጅ ይረዳዋል? እንዲህ ያለ ተራ ቁጭበሉነት እስከመቼ ይቀጥል?

ኢትዮጵያ ሲባል ትግራይም ነው። የኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም የኤርትራ ህዝብና የትግራይ ህዝብ ያለበት የኢትዮጵያዊያን ሰላም ማለት ነው። ሃቁ ይህ ነው። መንግስት በሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ በፈቀደ በሳምንታት ውስጥ በኮንቴነር ተጭኖ ፎርጅድ ናቅፋ ኤርትራ ተረጨ። ይህ ግንኙነቱን አበላሸው። ዛሬም ወደዛ ለማምራት ዋስትና የሚሆን አንዳችም ቀብዲ ትህነግ ሊከፍል አይችልም። እንኳን አሁን ድሮ መንግስት እያለም አልቻለበትም። እናም አጉል ለቅሶውን ” አቁም። ሰላም ናፍቆናል” ማለት ሲገባ ይህንኑ ማስተጋባት እንደ ድርጅት ለቦነነው ትህነግ ነብስ ከመዝራት ያለፈ ለትግራይ ህዝብ የሚፈይደው ነገር የለም።

ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ከኤርትራ ህዝብ ጋር ሌላ ደም መቃባት ውስጥ ሳይገባ መንግስት ከኤርትራ ጋር በያዘው አግባብ ሰላም እንዲያወርድና በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ድጋፍ ሊያደርግ ነው የሚገባው። “ሁለት አገር አፍርሼ፣ በሁለቱ አገሮች ፍርስራሽ ላይ ታላቋን ትግራዋይ እገነባለሁ” በሚለው ቅዠቱ አሁንም የምትጋለቡ ካላችሁ በግልጽ እነግራችኋለሁ መከላከያ ዳግም ህይወቱን አይገብርም። በዚህ ቁማር የሚበላ ሳይሆን ለመጫወት ስሜት ያላቸውም የሉም። ጨው ለራስህ ስትል ነው ነገሩ። ይህ የሁሉም አቋም ይመስለኛል።

See also  አማራ ክልል በሚገደሉ ንጹሃን ጉዳይ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄና እንዲሰጥ አሳሰበ፤

አቅምን ማወቅ ግድ ነው። እውነታውንም መረዳት ያስፈልጋል። ቅዠት መከራ ውስጥ ነው የከተተን። ስድስት መቶ ሺህ በላይ አምራች ፣ ወታት፣ ታዳጊ ሃይል ማለቁን ኦባሳንጆ ነግረውናል። እንደ እውነቱ ዜናው አስደንጋጭ ሆኖ ሳለ፣ ዜናው የሚረብሽ ሆኖ ሳለ፣ ለምን ሰላም ሰፈነ ብለው አታሞ ከሚመቱ ሆድ አምላኩዎች ጋር አብሮ ማበድ ለየትኛው የትግራይ ሕዝብ ታስቦ እንደሆነ ለማሰብ ይቀፋል።ኦባሳንጆ የወደመውን ሃብት መልሶ ለማቋቋም የአንድ ትውልድ እድሜ እንደሚያሻ አስታወቀዋል። ትህነግ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ሲያጠፋና ሲያውክ ኖሮ፣ ሲዘርፍና ሲያዘርፍ ከርሞ፣ አገሪቱን ሲያመክናትና በጎሳ ፖለቲካ ሲንታት ኖሮ ሲያልቅ፣ እሱና እሱ ባመታው መዘዝ የአንድ ትውልድን ዕድሜ በሚጠይቅ ኪሳራ አከናንቦናል። ድፍን ትግራይን በዓለም ስም መሳለቂያ አድርጓል። ይህ እንዴት ለአንድ ትግራይ ለተፈጠረ ወይም እንደ ሰው ሰብአዊ ለሆኑ ወገኖች አይታይም። ያሳፍራል። ነጮቹ “ስጋው የት አለ” ሲሉ ሃምበርገሩን ከፍተው የስጋውን ትንሽነት እንደሚያሳዩ ሁሉ ትህነግን ክፈቱና እዩት። ቴዎድሮስ እንዳለው ” ያለስሙ ስም እየተሰጠው የኖረ” የባዶዎች ስብስብ ከመሆን ሌላ፣ ሃፍረት ያልዘራባቸው፣ ነብስና ስጋቸው የተፋታችባቸው መሆናቸውን ከማየት በቀር ሌላ ምን?

አሁን ላይ የሚሰማው የጦርነት ውጤት ሰፊ ቁጥር ያለው ሞት፣ ውድመት፣ ሰቆቃ፣ ስደት፣ ረሃብ፣ ጠኔ፣ ድቅድቅ ጨለማ፣ በጥቅሉ ከክፍለ ዘመናት በፊት እንደነበረው የዘመነ ድንጋይ ጊዜ ዓይነት ነው። ይህ ሁሉ እየታየ የትግራይ ህዝብ ከዚህ ሁሉ መከራ እንዲወጣ መትጋት ሲገባ፣ “ከኢትዮጵያ ጋር በቃኝ፤ ከኤርትራ ጋር ለመቀጠል እኔ አቅም ባይኖረኝም መንግስት ሆይ ጣልቃ ግባና ውጊያ ጀምር ” የሚል ጨዋታ ቴዎድሮስ እንዳለው ካርቶን ራስነት ነው። ሊሆንም አይችልም። አይደረግምም። በትግራይ ካሁን በሁዋላ የጥይት ድምጽ መሰማት የለበትም። ጨለማ ውስጥ ወድቆ እንደ ጋርዮሽ ዘመን ፍሬ የለቀመ መመገብ ለጀመረ ህዝብ፣ እሳት መጫሪያ ክብሪት ብርቁ ለሆነ ህዝብ፣ የራስ ምታት ኪኒን የቅንጦት ለሆነበትና የቁም ስቃይ ላይ ላለ ህዝብ ባለ በለኤለ አቅም ለካሳ መሮጥ፣ የህዝብ ለህዝብ ሰላም እንዲሰፍን ለት ተቀን ከመስራት ውጪ ሌላ ማራጭም፣ መፍትሄም እንደሌለ፣ ቢታሰብም እንደማይተቅም ሊታወቅ ይገባል። ምን ይሁን ታዲያ ለምትሉ

አንድ ሚስጢር

ዛሬ ኢትዮጵያ ትልቅ ሰራዊት ገንብታለች። ዕልህ የወለደው ጦር ነው። ገና ትግራይም ትጨምርበታለች። እየተሰራበት ነው። የሰላም ስምምነቱ አንዱም አካል ነውና። ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቃለች። ቁና ቋና የሚያስተነፍስ አየር ሃይል አላት። ትህነግ ያፈረሰውን የነበልባል ፓራ ኮማንዶና የባህር ሃይል ጦርም አዘጅታለች። የጦር መርከብም ባለቤት ሆናለች። የተገነባው ሰራዊት ለኢትዮጵያ ኩራት እንዲሆን ታስቦ የተሰራ ስለመሆኑ ስራውን ለመጎብኘት የታደሉ የሚረዱት እውነት ነው። ይህ ሃይል በቀጣናው ማናቸውንም አገራት ከሰላምና ከፍቅር በዘለለ በተንኮል ከመጡ መድፈቅ የሚችል ነው። ሱዳን ይህን አምና ተቀብላለች። ኬንያ አትሞክረውም። በሶማሌ የሚታስብም የሚፈራም የለም። ሌቦችና ተላላኪ ባንዳዎች የሚያሰማሯቸው ልክስክሶች ካልሆኑ በቀር አሁን ላይ ችግር ፈጣሪና አስፈሪ ሃይል የለም። ከኤርትራም ጋር ሰላም ነው። ቁመናችንን ያውቃሉ። ቁመናቸውን እናውቃለን። ስለሆነም የባድመን ጉዳይ መንግስት ከህዝብ ለህዝብ ጉዳይና ጥቅም፣ እንዲሁም አከላሉ ላይ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን በጋራ ከውዳጅ አገራ ኤርትራ ጋር በመከባበር እንዲጨርሰው አደራውን መስተት እንጂ አጉል ቀረርቶና ስልት ቀይሮ ማልቀስ አይጠቅምም።

ሚስጥሩ ነገሮች ሁሉ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲፈቱ ለማድረግ መንግስት ጫና እስከማሳደር የሚደርስ አቅም አለውና የትህነግን ቅኝት ቀይሮ የጀመረውን ለቅሶ ወግድ ማለቱ ይበጃል። ሰላም የሚሰፈነውም በዚሁ መንገድ ነው። ዛሬ ትናንት አይደለም። ዛሬ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት መንግስት እርቃኑን ሰላይ አልባ፣ ፖሊስ አልባና ሰራዊት ያጠረው ልፍስፍስ አይደለም። ምን አልባትም አሁን ላይ ኢሳያስ ለአብይ ከሚያስፈልጓቸው በላይ አብይ ለኢሳያስ ያስፈልጓቸዋል። ግን በጋራ መጠቀም መርህና ሰላምን መሰረት አድርጎ ማስኬድ የመንግስት ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑ ሊሰመረበት ይገባል። ልክ እንደዘፈኑ “አቋቋምሽማ” ነውና ነገሩ። ትህነግ ይህቺን ስለሚያውቅ ሃቁም ይህ ሆኖ ሳለ፣ ትህነግ ጥርሱን ጨርሶ በድድ ስለቀረ ኤርትራና ኢትዮጵያን አናክሶ እሳት እየሞቀ ጥርስ ለማብቀል ያሰላት የጉሊት ስሌት ለትግራይ ህዝብ ሌላ የጨለማ ዘመን ከመጋበዝ አታልፍም። ያንን ሁሉ የዓለም ጫናና ዱላ የተሸከመውና ያለፈው ብልጽግናም ይህቺን ተረት በቀበሌ አመራሮቹ ትንተና ጉልበት ሳያባክን ያውቃታልና አይሸወድም። ሚስጥሩ ይህ ነው። መንግስትን እመኑ። እሱ ይጨርሰዋል። ካልሆነም ምን እንደሚያደርግ ያውቃል። ሰላም!!

መላኩ ክንዴ ህሩይ –

አዘጋጁ – ይህ ነጻ አስተያየት የጸሃፊውን አሳብ ብቻ የሚወክል ነው

Leave a Reply