የሰላም ስምምነቱና የአማራ ሁኔታ!

ለዚህም ሲባል ካለፈው ስህተት ተምሮ አማራ ካሁን በኋላ ከውስጥ (በዋናነት ከትግራይ) ለሚነሱ ጥቃቶች በወሳኝነት ራሱን ችሎ ለመከላከል የሚያስችል ቁመና መገንባቱን ማረጋገጥ አለበት። ይሄም ማለት የአገሪቱን ህገ መንግስትና ህጎች ባከበረ መልኩ በሁለንተናዊ መስኩ የተገነባ የፀጥታ ተቋም ሊኖረን ይገባል ማለት ነው። ለአማራ ዘላቂ ሰላምና ህልውና ሲባል ወጭ የማይሆን በጀት ?ይህ አጀንዳ ሲነሳ በበጀት እያሳበበ ፊቱ የሚጠቁር መሪ ካለ በጊዜ ጥጉን ቢይዝ ይመከራል፡፡ ቅድሚያ ለሕዝብ ደህንነት!

በቹቹ አለባቸው – ነጻ አስተያየት

በፌዴራሉ መንግሥትና በህወሓት መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት ከነ ጥርጣሬውም ቢሆን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ደስተኛ ነው። ይህ እውነታ ከአማራ አንፃርም የተለየ ነገር የለውም፤ ሊኖረውም አይችልም። ይሁን እንጅ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጎላ ባለ መልኩ በአማራ ሕዝብ ዘንድ ይሄንኑ ስምምነት በተመለከተ ያለው ስጋት ከፍ ያለ ሆኖ ይታያል። የአማራ ሕዝብ ይሄንኑ ስምምነት በጥርጣሬ የሚያይበት ሁለት የተሳሰሩ ስጋቶችን በማንሳት ነው።

እነዚህም:-

1. ስምምነቱ ወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን ሊያሳጣን ይችላል የሚል ሲሆን፤

2. ሕወሓት ከቀደመጥፋት የማይማር በመሆኑ፣ የደቡብ አፍሪካውን ስምምነት ተግባራዊ አያደርግም፤ይልቁንስ ጊዜ አግኝቶና ተደራጅቶ እንደገና ለማጥቃት (በዋናነት አማራን) መሞከሩ አይቀርም የሚል ነው።

በእኔ በኩል ሰዎች ለምን እንደዚህ አይነት ሰጋት ውስጥ ይወድቃሉ ብየ ለመተቸት አልፈልግም፤ ምክንያቱም ያለፈው እና ዛሬም ድረስ የቀጠለው የአገሪቱ ፖለቲካ፣ ሰዎች እንደዚህ አይነት ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደፋፍር እንጅ የሚገታ አይደለም።

ይሄም ሆኖ ሰዎች ሁለቱንም ስጋቶች ሲያነሱ ከተለያየ መነሻ እንደሆነ እገነዘባለሁ። አብዛኛዎቹ እውነትም ከልባቸው የአማራ ዕጣ ፋንታ እያሳሰባቸው ሲሆን፤ ጥቂቶች ደግሞ የብለን ነበር ፖለቲካን ለማራመድና የፖለቲካ ቀውሱን የማይነጥፍ የገቢ ምንጭ አድርጎ የመጠቀም ፍላጎት ስላላቸው ነው።

ለሁሉም ከላይ ባነሳሁዋቸው ሁለት ወቅታዊ ስጋቶች የኔ እይታ እንደሚከተለው ነው።

1. ‹‹ወልቃይት-ጠገዴ፣ጠለምትና ራያን እንነጠቃለን›› የሚለውን ስጋት በተመለከተ:-

እውነት ነው የፕሪቶርያው ስምምነት ስለነወልቃይት ጉዳይ ቁርጥ ያለ መፍትሄ አላስቀመጠም፤ያስቀምጣል ተብሎም አይጠበቅም። አንዳንድ ወገኖች በዚሁ መድረክ አጀንዳው መነሳትና መፍትሄም ማግኘት ነበረበት ብለው ሲተቹ ተመልክቻለሁ።

አሁንም አጀንዳውን በቅንነት የሚያነሱትን ወገኖች አክብሮቴን ገልጨ፣ አንዳንዶች ግን ሆን ብለውና ብለን ነበር ለማለት ብቻ አጀንዳውን ሲያጮሁት እመለከታለሁ። ስለእውነት የሚከራከር ካለ የነወልቃይት አጀንዳ ፕሪቶርያ ላይ ሊቋጭ የሚችል አጀንዳ አልነበረም። በልኩና በሚገባው ልክ አጀንዳው ተነስቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ የተቀመጠው መፍትሄም የሚጠበቅ ነበር። እንዴውም ለተደራዳሪዎች ብስለት የተሞላበት አካሄድ አክብሮት አለኝ፡፡ ይህ ሁነት የገባቸው የትግራይ ዲያስፖራዎች ስምምነቱ ከተፈረመበት ዕለት ጀምሮ በተከታታይ ቀናት ድንኳን ጥለው ሲያለቅሱ እንደሰነበቱ ማህበራዊ ሚዲያው ምስክር ነው፡፡

በስምምነቱ የተቀመጠውን መፍትሄ (ህገመንግስታዊ) በተመለከተ ብዙውን ቅን ሰው ያስጨነቀው ነገር አካባቢዎቹ የተወሰዱት በጉልበትና ከህገ መንግስት መፅደቅ በፊት ሆኖ እያለ እንዴት ችግሩ በህገ መንግስቱ መሰረት ይፈታል ይባላል የሚል ነው። አንዳንድ ወገኖች ጉዳዩ ከህገ-መንግስቱ ወጣ ብሎ (በውይይት ጭምር) መታየት አለበት ይላሉ። አንዳንድ ወገኖች ደግሞ ጉዳዩ መፍትሄ ማግኘት ያለበት በህገ መንግስቱ መሰረት ሳይሆን “በፖለቲካዊ ውሳኔ” ነው መሆን ያለበት ይላሉ።

See also  አሮጌውን ወይን በአዲስ አቁማዳ ! የኖርንበት ፣ የቸከ የሰለቸ የፖለቲካ ...

ከዚህ ወጣ ያሉት አንዳንድ ወገኖች ደግሞ በጉልበት የተቀማነውን በጉልበት መልሰናል፣ ስለዚህ ጨዋታው አብቅቷል ሲሉ ይደመጣሉ። የሦሰተኛ ወገኖችን አባባል ለጊዜው ልለፈውና የመጀመርያ ሁለቱን አቅጣጫወች ግን መመልከት ጥሩ ነው። ለመሆኑ ፖለቲካዊ መፍትሄ ስንል ምን ማለታችን ነው? ዛሬም አንዳንድ ወገኖች ነገሩን አንድም ያለመገንዘብ ሁለትም ሆን ብለው ማዛባቱን ቀጥለውበታል። እኔ በተደጋጋሚ እንደምለው ዛሬም ጉዳዩ መታየት ያለበት በህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ ሰር ካሉት 3 አማራጮች መካከል ( በፌደሬሽን ም/ቤት ውሳኔ፣ በሕዝበ ውሳኔና በህገ መንግስታዊ ማሻሻያ) በፌደሬሽን ም/ቤት ውሳኔ መሆን አለበት ባይ ነኝ።

የማንነት ጥያቄው በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀዕ 48 (1) እና የፌደሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን እና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1261/2013 አንቀጽ 37 (1) እና (2) እንዲሁም አንቀጽ 38 (1) መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝቡን አሰፋፈር፣ ባህል፣ ሥነ-ልቦና፣… መርምሮ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል፡፡

ይህ አካሄድ በአማራና ትግራይ ልሂቃንና የሕዝብ ለሕዝብ በተለይም የሀገር ሽማግሌዎችን ውይይት ማካተቱ የሚቀር አይደለም። እንዴውም በእኔ ግምት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው እንደዚህ አይነት ውይይቶች መሆናቸው አይቀርም። ይሄም ሆኖ ግን የመጨረሻውን ህጋዊ ውሳኔ የፌዴሬሽን ም/ቤት መስጠት አለበት ነው እያልን ያለነው። ይሄንኑ አማራጭ መከተል ለዘመናት የዘለቀውን ጥያቄ በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት የተሻለው አማራጭ እንደሆነ አምናለሁ።

የአማራ ክልል መንግስትም ይሄኛውን ሕገ-መንግሥታዊ የመፍትሄ ሀሳብ ዋነኛ የትግል አቅጣጫ አድርጎ ወስዶ የወሰን ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቧል፤ ይህን አቋሙን አዝልቆ ጥያቄው በዚህ መንገድ እንዲፈታ መታገል አለፍ ሲልም ወሳኝ መድረኮችን በመፍጠር ሕዝብን አንቅቶ መንቀሳቀስ አለበት።

ውሳኔው በምክር ቤቱ ድምፅ ብልጫ የሚወሰን በመሆኑ ምን ያክሉ የም/ቤት አባላት ይሄን ውሳኔ በሚዛኑ አይተው፣ እውነትን አሰቀድመው ይወሰናሉ የሚለውን አስልቶ መስራት ይጠይቃል፡፡ የኛ ተስፋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ለህሊናቸው በመገዛት ከእውነት ጎን ይቆማሉ የሚል ነው። ተስፋችን የፌ/ም/አባላት የተሳሳተ ውሳኔ ወስነው ሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነት ሲታመስ እንዲኖር አይፈቅዱም የሚል ነው። መቸም የፌ/ም/አባላት ሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነት እየታመሰ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ሰላም ያገኛል ብለው ያምናሉ ተብሎ አይጠበቅም።

ስለሆነም ሰሜን ኢትዮጵያ፣ በነወልቃይት የተነሳ ሰላም የራቀው ቀጠና ሆኖ እንዳይዘልቅ በታሪክ በእጃቸው የገባውን ህገ መንግስታዊ መብት ተጠቅመው ሀቀኛ ውሳኔ ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል።

እውነት ነው ጨዋታው ከብልፅግና ቤት መሆኑን አንረሳም። ቢሆንም የአማራ ብልፅግና የብልፅግና ቤተሰቦቹን የማሳመን ኃላፊነት አለበት። ሀቅን ይዞ አንድን የብልፅግና ቤተሰብ በዚህ ሀቅ ዙርያ ማሰባሰብ ካልተቻለ፣ የአማራን ብልፅግና የብልፅግና ቤተሰብ ሆኖ በመቀጠሉ ዙርያ ጥያቄ ያስነሳበታል።

ሌሎቹ የብልፅግና ቤተሰቦችም የአማራ ብልፅግና የሚያነሳውን ሀቅ ተገንዝበው ከጎኑ ካልቆሙ ቤተሰብነታቸውን ጥያቄ ውስጥ ያስገባባቸዋል።

ሌላው ተስፋችን የፌ/ም/አባላት አጀንዳው በሕዝበ ውሳኔ ይታይ ብሎ በመወሰን ወደተወሳሰበና አሰቸጋሪ ነገር ውስጥ አያስገባንም የሚል ነው። ለምሳሌ ‹ሕዝበ ውሳኔ ቢባል ማን ነው በሕዝበ ውሳኔው የመሳተፍ መብት የሚኖረው?› የሚለው ጥያቄ እንዲህ በቀላሉ ስምምነት የሚደረስበት ጥያቄ አይሆንም።

See also  "የግብፅ መሠረታዊ ችግርም ያለው ሱዳን ከግድቡ ለምን ትጠቀማለች ከሚል የሚመነጭ ነው"

ሲቀጥል ከ1,600 በላይ አማሮችን ጨፍጭፎ ወደሱዳንና ትግራይ ከወጣው ትግራዋይ መካከል ወንጀለኛውን ከንፁሀኑ ትግራዋይ እንዴት መለየት ይቻላል? ወልቃይት ላይ ሲፈጸም በነበረው የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ የወንጀሉ የሀሳብ ክፍል ብቻ ሳይሆን የዘር ማጥፋት ወንጀሉን በምክር፣ በተግባር፣ በገንዘብ፣… ወዘተ የደገፉና የተባበሩ ወንጀለኞች በምን አግባብ ተመልሰው የሕዝበ-ውሳኔው ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ? ይህ አማራጭ ተምኔታዊ እንጂ ገቢራዊ የመሆን እድሉ ዝቅተኘ ነው ብየ አምናለሁ፡፡

ብቻ ይሄኛው አማራጭ አንዱ ሕገ-መንግሥታዊ አማራጭ ቢሆንም ተግባራዊ ለማድረግ ግን እጅግ ውስብስብና አሰቸጋሪ እንደሚሆን በማመን የፌ/ም/አባላት እንደጥሩ አማራጭ እንደማያዩት ተስፋ አለን፤ አደጋውን ማሳየትም ብልህነት ነው፡፡

በመጨረሻም ‹መፍትሔው ፖለቲካዊ ነው› ለሚሉ ወገኖች ጥያቄ አለኝ። በናንተ እምነት ፖለቲካዊ መፍትሔ ማለት ምን ማለት ነው ? የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ከሆነ እርሱ ሕገ-መንግሥታዊ አማራጭ እንጅ ፖለቲካዊ ሊባል አይችልም፡፡ የዶ/ር አብይ ካቢኔ የነወልቃይትን ጉዳይ በድምፅ ይወስን ማለት ነው? አዎ! ካልን፤ ይህ መንገድ ዘለቄታዊ አዋጭነቱ በተለይም ዓለማቀፋዊ ቅቡልነቱ እምብዛም በመሆኑ ከዘለቄታዊ ጥቅም አኳያ ቢታሰብ ይመከራል፡፡ ሀቅ በእጃችን እስካለ ድረስ እሱን ሀቅ ተናግሮ ማስገንዘብ፤ በዚህም ኃይል ማሰባሰብ የኛ ኃላፊነት ነው፡፡

2. ‹ሕወሓት ለሰላም ስምምነቱ አይገዛም ይልቁንስ እንደገና ሊያጠቃን ይችላል› የሚለውን ስጋት በተመለከተ:-

በዚህ በኩል ያለው ስጋት ውሀ የሚቋጥር ይመስለኛል። በከባድ የሞራል ልሽቀትና የሥነ-ልቦና ስብራት ውስጥ የሚገኘው የትግራይ ፖለቲካ ወዴት እንደሚያመራ አይታወቅም። በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ መሆን ይቻላል፤ቀደም የምናውቀው ሕወሓት ከነ‹ግሬሱ› ትግራይ ላይ አይኖርም። የትግራይ ፖለቲካ እንደድሮው የተረጋጋ የመሆን እድሉ አናሳ ነው። የአንጃ ቡድኖች ከዚህም ከዚያም ሊፈለፈሉ ይችላል፡፡ በተለይም ወታደራዊ ክፍሉ የሚመራው የፖለቲካ አመራር እስካገኘ ድረስ ወደአስመራም፣ ወደጎንደር-ባህርዳርም፣ ወደሸገርም ከመተኮስ ወደኋላ አይልም (ስም መዘርዘሩ ፋይዳ ባይኖረውም፣ ዛሬም የደም ጥማት ያለባቸው የትግሬ ጀኔራሎች የቀደመ የጦርኝነት ስሜታቸው የበረደ አይመስልም)

በአጭሩ፣ ትግራይ ውስጥ የሰላም ስምምነቱን ተቀብሎ ለመኖር የሚፈልግ ኃይል እንዳለ ሁሉ፤ ከዚህ በተፃራሪ የሚቆም ኃይልም መኖሩ አይቀሬ ነው። ይሄኛው ኃይል የትጥቅ ትግልን እንደአማራጭ መጠቀሙ አይቀርም። ዋነኛ የማታገያ አጀንዳው ደግሞ፡- ‹ትግራይን ለዚህ ውድት የዳረጋት አማራ ነው፣ ስለዚህ እንበቀለው› የሚል መሆኑ አይቀሬ ነው።

በነገራችን ላይ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ወጣ ባለ መልኩ፤ ይሄንኑ ስምምነት ለማስፈጸም ሲባል ናይሮቢ ላይ በጦር ጀኔራሎቹ መካከል የተደረሰው ስምምነት፤ ለዚህኛው አንጀኛ ሀይል እንደ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆንለት ይችላል፡፡ ይሄም ማለት ሁላችንም እንደምንገነዘበው፤ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ስለ ኤርትራም ሆነ የአማራ ኃይሎች “ከትግራይ መውጣት” የተባለ ነገር አልነበረም፡፡

ይሁን እንጂ ይህ አጀንዳ በናይሮቢው ስምምነት፤ የነዚህ ኃይሎች ከትግራይ መውጣት ከከባድ መሳሪያ ማስፈታት ጎን ለጎን ይፈጸማል መባሉ፤ በትግራይ ነውጠኛ ኃይሎች ዘንድ እንደቅድም ሁኔታ ሲተረጎም እያየነው ነው፡፡

See also  ህያው ምስክሮችን [ቤተሰብ] እንመን ወይስ ሀብታሙ አያሌውን?

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በተለይም የአማራ ኃይል (ከተከዜ ማዶ Tigray Proper የአማራ ኃይል ካለ) ከትግራይ መውጣት ያለበት፤ የሕወሓት ኃይሎች ትጥቃቸውን ከፈቱ በኋላ ነው የሚል ቅድመ ሁኔታ መቀመጥ ነበረበት፡፡ አሁን ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ለህዝቡ ግልፅ አይደለም፡፡ የናይሮቢው ስምምነት የፕሪቶሪያውን እናት ስምምነት ሊሽር አይገባም። አሸናፊው ሰላም እንዲሆን እስከተፈለገ ድረስ፣ ቀዳዳ መተው የለበትም፡፡

አሁንም የኢትዮጵያ መንግስት ይሄንኑ ጉዳይ ተመልሶ ቢመለከተው ህጋዊ አሰራሩ ይፈቅድለታል፤ የአማራ ክልል መንግስትም ቢሆን ጉዳዩን በአንክሮ ሊመለከተው ይገባል እላለሁ፡፡

ስለዚህ ከአማራና ከክልሉ መንግሥት የሚጠበቀው ጉዳይ ይሄንን እውነታ ተገንዝቦ ሁሌ ዝግጁነትን ማረጋገጥ ነው። በዚህ በኩል ለደቂቃም ቢሆን መዘናጋት አያስፈልግም፤ ሁሌም በተጠንቀቅ መቆም የወትሮ ዝግጁነትና ተነቃነቃዊ አቅምን ማሳደግ የግድ ይላል፡፡

ከትግራይ ወገኖቻችን በኩል አማራን በክፉ ማየት እስካላቆመ ድረስ አማራ በተለይም አመራሩ ሁሌም ቢሆን ከትግራይ አክራሪ ወገኖች አደጋ እንዳለ አሰቦ፣ አመራርን ማረጋገጥ አለበት። በተለይም የፌደራል መንግሥቱንና የመከላከያን ሚና ዘንግቼ ሳይሆን ከትግራይ ጋር የምንጋራው ወሰን ስፋት፣ የጎረቤት አገራት ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ የከረመችበትና ያለችበት ውስብስብ ሁኔታ ፋታ የሚነሳ በመሆኑ ከክልልና ከሕዝብ የሚመነጭን አቅም ለከፋው አደጋ መመከቻ ቀድሞ ማዘጋጀት ከራስ አልፎ ኢትዮጵያን የመጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡

ለዚህም ሲባል ካለፈው ስህተት ተምሮ አማራ ካሁን በኋላ ከውስጥ (በዋናነት ከትግራይ) ለሚነሱ ጥቃቶች በወሳኝነት ራሱን ችሎ ለመከላከል የሚያስችል ቁመና መገንባቱን ማረጋገጥ አለበት። ይሄም ማለት የአገሪቱን ህገ መንግስትና ህጎች ባከበረ መልኩ በሁለንተናዊ መስኩ የተገነባ የፀጥታ ተቋም ሊኖረን ይገባል ማለት ነው። ለአማራ ዘላቂ ሰላምና ህልውና ሲባል ወጭ የማይሆን በጀት?

ይህ አጀንዳ ሲነሳ በበጀት እያሳበበ ፊቱ የሚጠቁር መሪ ካለ በጊዜ ጥጉን ቢይዝ ይመከራል፡፡ ቅድሚያ ለሕዝብ ደህንነት!

በመጨረሻም የሁሉ ነገር መፍትሄ ምድር ላይ ያለ ስራ ነው። መንግሥታችንና መከላከያ ሰራዊታችን ምድር ላይ የሚሰራውን ስራ በወቅቱ ባይሰሩ ኖሮ ዛሬ ላይ አገራችንም ሆነ አማራ በዚህ ደረጃ ባልተገኘን ነበር። ስለዚህ ሀገራዊ ድጋፋችን እንዳለ ሆኖ፣ አማራን በወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ ጉዳይ ለድል ሊያበቃው የሚችለው ምድር ላይ የሚሰራው ስራ ነው።

ምድር ላይ የሚሰራ ስራ ደግሞ በየቦታው አለ፣ ለምሳሌ ወልቃይት፣ጠለምትና ራያ ግንባሮች የሚሰራው ስራ እንዳለ ሁኖ፣ በፓርላማ፣ ፌ/ም/ቤት፣ ሚኒስትሮች ም/ቤት ውስጥ የሚሰራ ብዙ ሰራ አለ። አዲስ አበባና ከአማራ ክልል ውጭም ብዙ የሚሰራ ሰራ አለ። ቁም ነገሩ እያንዳንዱ አማራ በያለበት ለወገኖቹ አምባሳደር ሆኖ ከእርሱ ምን እንደሚጠበቅ አውቆ የድርሻውን ለመወጣት ምን ያክል ቁርጠኝነት ተላብሷል የሚለው ነው።

አማራ ሁሉን ነገር እንደጎረቤቶቻችን ‹‹በቅልፅምና›› አይልም። አማራ በያዘው ሀቅ እንደሚያሸንፍ እምነቱ የፀና ነው። ለዚህም ሲል ሁለት እግር በመሬት የሚለውን መርህ ይተገብራል።

ሁለት እግር በመሬት!!

Leave a Reply