በኢትዮጵያ ሙስና ድርጅታዊ ቅርጽና አዋጅ ወጥቶለት የተገነባ የካንሰር ሃውልት ነው። ሌብነት ውስጥ መንግስት በልማት ድርጅቶችና በኢንዶውምነት ስም የታነጸ የሃብት ማካበቻ የካድሬዎች ፒኤልሲ ነው። ሙስና ወይም ሌብነት መንግስትን ለማይቃወሙና ሳይጠሩ አቤት ለሚሉ ሁሉ እንዲበሰብሱበት የሚፈቅድ ህጋዊ ተቋም ነው። ከፍለገ ቢሮውን ጸረ ሙስና ህንጻ ውስጥ ሊከፍት ይችላል። ሌብነት የፖለቲካ አመለካከትን መቀወሪያ መዶሻ ሆኖ ከገነገነ ብሁዋላ ዛሬ ለውጡ ተከትሎ በተነሳው አለመረጋጋት ውስጥ ከፍተናውን ድርሻ የያዘ ተቋም ሆኗል። ባለቤቶቹም አገርና ህዝብን ከርከረው ለመጣል የደፈሩት በዚሁ የአፈጣጠራቸው ህጋዊነት ሳቢያ ነው። ታዲያ ይህን ሁሉ ግብስብስ ይዞ ለውጥ ያወጀው ብልጽግና “ትብትቡ ከባድ ነው” ሲል በጥቂት አመራሮቹ አማካይነት ያስታወቀ ለዚህ ይመስላል። ከዜናው ሰዎች አንደበት የተወሰደ!!

በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ በሌብነት ሃብት ያካበቱና ” ሻርኮቹ” የሚባሉ ሌቦች የራሳቸው ታጣቂ፣ ሽፋን የሚሰጡ ባለስልጣናትና የሚቀልቧቸው ሚዲያ እንዳላቸው የሚታወቅ መሆኑንን ስማቸው እንዲደበቅላቸው የጠየቁ አስታወቁ። እነዚሁ ክፍሎች ሟቹ መለስ ያሉትን ጠቅሰው እንዳሉት ከሆነ ” ብልጽግና በስብሷል፤ ያልወደቀው በመከላከያውና በውስን ቁርተኞች ምክንያት ነው”

ብልጽግና ውስጥ ካሉ ከፈተኛ አመራሮች መካከል ሞል በሽርክና የገነቡ፣ የሪል እስቴት ሽርክና ያላቸው፣ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋሞችና ፋብሪካዎች ከፍተኛ ድርሻ የያዙና ህንጻ የገተሩ ጥቂት አይደሉም። ዘይት ለጥቂት ሰዎች ብቻ ተፈቅዶ ወደ አገር ቤት እንዲገባ ኢህአዴግ ፈቅዶ በነበረበት ወቅት ከየክልላቸውና ለትህነግ ቅርብ የሆኑትን መልምለው ሃብት ያፈሱም ድብቅ አይደሉም።

እነዚህ ወገኖች መንግስት እንዳይረጋጋ ሆን ብለው የሚያደቡ፣ የቀደመው ሲስተም እንዲመለስ የሚቦረቡሩ፣ ስንቅ በማቅረብ ሰበብ ወታደሩን ግንባር ድረስ ሄደው ልቡን ሊያሸፍቱ ሲሰሩ የነበሩ፣ በመንግስት ታላቅ መዋቅር ስርና በራሳቸው በጀት በተዘዋዋሪ ሚዲያ ከፍተው በስማቸው የሚያዘፍኑ እንደሆኑ እኒሁ ሰዎች ገልጸዋል።

” አሁን ላይ በብልጽግና ሌቦችን ለማነቅ ሙሉ ፍላጎት ያላቸው ጥቂቶች እንዳሉ እናውቃለን። እነዚህ ወገኖች ድጋፍ ያሻሉ” ሲሉ መረጃውን የሰጡት አመልክተዋል። አንዳንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከማይመጥኗቸው ጋር እንደሚውሉ፣ ለደረጃቸውና ለተቀመጡበት ወንበር በማይመጥን ደረጃ የመንግስትን ሃብት በገሃድ የሚከሰክሱ ታማኝ መሳዮች ለውጡ እየገዘገዙት እዚህ አድርሰውታል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን ደግመዋል።

“አገሪቱ ብትረጋጋ ከብልጽግና ውስጥ ስልጣን ሙሉ በሙሉ ለህዝብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በቀነገደብ ለማስረከብ ፍላጎት ያላቸው ቁልፍ ሰዎች እንዳሉ እንመሰክራለን። ይህ አድሮም ቢሆን የሚነገር እውነት ነው” ያሉት ክፍሎች፣ አሁን ላይ ነቀርሳ ሆነው አገሪቱን በኢኮኖሚና ታታቂዎች በመቀለብ ችግር የሚፈጥሩት እነዚሁ ክፍሎች እንደሆነ በግልጽ እንደሚታወቅ አመልክተዋል።

ሌብነትን መቆጣጠር ሳይሆን በማበረታታት ላይ አተኩሮ ሲሰራ የነበረው ትህነግ በየመንደሩ የጎበዝ አለቃ ነን ያሉ ሌቦችን እየፈለፈለ መሆኑንን በመጥቀስ አስቀድመው ሲከራከሩ የነበሩ ሰሚ ማጣታቸው፣ የጸረ ሙስና ኮሚሽን የፖለቲካ ተቀናቃኝና አዲስ አሳብ አፍላቂዎችን መድፈቂያ ትልቅ ህንጻ የተሸከመ አስከሬን ተቋም መሆኑን፣ ጉዳዩ ካሁኑ ሃይ ካልተባለ አገር እንደሚበላ በይፋ ሲነገር መስሚያቸው ተደፍኖ የነበር ዛሬ ኔትዎርካቸውን ” መንግስት ወድቋል፣ ባይወድቀም በዳዴ እየሄደ ነው። እንኳን ሌባ ሊይዝ ለራሱም ዕድሜው ማምሻ ነው” እያሉ ዘርፈው በገነቡት ህንጻ ልዩ ክፍል እየተጀነጀኑ ሲናገሩ የሰሙ ምስክሮች እንደሚሉት አሁን የቁርጥ ጊዜ ደርሷል።

ከትግራይ ሕዝብ ላይ አርባ ከመቶ ኮሚሽን እየተቀበሉ ብር በወልደያ፣ቆቦና በአፋር በኩል ሲያመላልሱ የከረሙትና በሚሊዮኖች ሃብት የሰብሰቡትን ጭምር መንግስት እንዲይዛቸው የትግራይ ነጹሃን መረጃ መስተታቸውን፣ ይህንኑ ዝርፊያ ሲያከናውኑ የነበሩት በቲፎዞ ” አርበኛ” የሚባሉትን ጨምሮ ብልጽግና ውስጥ የተሰገሰጉ ተኩላዎች እንደነበሩ መታወቁን መረጃውን ያካፈሉን አመልክተዋል።

“በሚቀልቧቸው ሚዲያዎች ከውጭና ከውስጥ የሚዘፈንላቸውና ለስማቸው ካብ የሚገነባላቸው ሌቦችና ኔትዎርካቸው ይታወቃል። ድብቅ ሊሆንም አይችልም” ሲሉ ስጋታቸውን የሜገልጹት ወገኖች ” የትህነግና የመንግስት የሰላም ስምምነት ላይ ዳግም ልዩነትና ጥርጣሬን በማጉላት እስከ ኤርትራ ድረስ ዘለቀው የሚፈተፍቱት፣ ሰላም ከወረደ በመረጃና ማስረጃ የሚታወቁት ሌቦች ላይ በገሃድ ዘመቻው ስለሚከፈት ለማሰናከል ነው” በማለት በጭምጭምታ የሚነገረው እውነት እንደሆነ አስታውቀዋል። በቀታይም ዝርዝር ጉዳዮችን ለማቅረብ እንደሚጥሩ ጠቅሰዋል።

ቤተሰቦቹ ከሸኔ ጋር ሽርክ የሆኑና በብልጣ ብልጥ ቋንቋ የሚሙለጨለጩ ባለስልጣናትና ወኪል ባለሃብቶች በትህነግ መሸነፍ በምስጋታቸው ሌለውን ግንባር ባለ በሌለ ሃይል የማንቀሳቀስ ስራ ላይ መተመዳቸውንም ዝርዝር ሳይናገሩ እንዚህ ወገኖች አመልክተዋል።

ቀደም ባሉት አመታት የፌደራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሃላፊዎችና መርማሪዎች ሆነው “ጥገኛ” ተብለው የተገመገሙ መኖራቸውን ያወሱት ጥቆማ ሰጪዎች፣ አሁን ጉዳዩ የህልውና በመሆኑ አንዳንድ መዋቅሮች መፍረስ እንደሚገባቸው፣ አንዳንድ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ለጊዜው ሊዘጉ እንደሚገባ፣ ይህ ከተደረገ ህዝብ በቀናነት ተቀብሎ ድጋፍ እንዲሰጥ ከወዲሁ ጠቁመዋል። እንደ ስዩም ተሾመ ያሉ ደፋሮች ለአገሪቱ ህልውና ሲሉ ይህን ዘመቻ በገሃድ ሊቀላቀሉ እንደሚገባም አምልክተዋል።

ዝግጅት ክፍሉ በዚህ ዙሪያ አሳብና አስተያየት ካላችሁ ላኩልን። ሰእሉ ላይ ያለው የትህነግ የንግድ ኢምፓየር ከአፍሪካ አንደኛ የመሆኑን ጉዳይ ራሳቸው ስብሃት ነጋ እንዳሉት ለማመላከት እንጂ፣ ኮንጎ ጫማና የማዳበሪያ ዕዳ ተሸከመው ራሳቸውን ኢንዶውመንት ብለው የሚተሩት ትርፍራፊ ድርጅቶ ንጹህ ናቸው ለማለት አይደለም።

Leave a Reply