ከባለቤቱ ዕውቅና ውጭ ቤት በ11.5 ሚሊዮን የሸጡ የመሬት አስተዳደር ሰራተኞችን ጨምሮ ሶስት ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ

ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም የአንድን ግለሰብ ቤት ከባለቤቱ ዕውቅና ውጭ በ11.5 ሚሊዮን ብር የሸጡ የመሬት አስተዳደር እና ወሳኝ ኩነት ጽ/ቤት ሰራተኞችን ጨምሮ ሶስት ተከሳሾች ላይ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ፡፡

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ህግ 1ኛ ዳንኤል ተስፋዬ ፣ 2ኛ ያሬድ በየነ፣ 3ኛ አድማሱ ሙላቱ፣ 4ኛእስራኤል ደጀኔ እና 5ኛ ብርሃኑ ዳግም በተባሉ ተከሳሾች ላይ ፈጸመዋል ባለው ከባድ የሙስና ወንጀል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሙስና ወንጀል ችሎት ህዳር 21 ቀን/2015 ዓ.ም 4 ክሶችን መስርቶባቸዋል፡፡

የተከሳሾችን የዋስትና መብት ጥያቄ በተመለከተ የተከሰሱበት የህግ ድንጋጌ ዋስትና የሚያስከለክል በመሆኑ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ዐቃቤ ህግ በጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ አዟል፡፡

የዐቃቤ ህግ መዝገብ እንደሚያስረዳው በ1ኛ ክስ በ1ኛ፣ በ2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 05 ወሳኝ ኩነት ጽ/ቤት ሲስተም አድሚኒስትሬተር ሆኖ ሲሰራ እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ በክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት ውስጥ ረዳት የቅየሳ ባለሙያ ሆኖ ሳለ በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ በግል ስራ ከሚተዳደረውና በሙስና ወንጀል ልዩ ተካፋይ ከሆነው 3ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት በማሰብ በወረዳው የሚገኘውን የአቶ ግደይ ገብረእግዚያብሄርን ቤት በህገ-ወጥ መንገድ በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው ለማዋል 1ኛ ተከሳሽ ባልተሰጠው ስልጣን ለ3ኛ ተከሳሽ ከወረዳው በአቶ ግደይ ገ/እግዚያብሄር ስም ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ እንዲሁም ያላገባ ምስክር ወረቀት አዘጋጅቶ ይሰጠዋል፡፡

3ኛ ተከሳሽም የወጣለትን ሃሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም ከዳሽን ባንክ የሂሳብ ቁጥር ከከፈተ በኋላ አቶ ግደይ እንደሆነና ቤቱ የእርሱ መሆኑን ገልጾ ይዞታውን ለመሸጥ እንደሚፈልግ ተናግሮ ወሰን ሃ/ማርያም የተባለ የግል ተበዳይ ቤቱን ለመግዛት ይቀርባል፤ ሀሰተኛ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ኮፒ ቤቱን ለመግዛት ለቀረበው ለአቶ ወሰን በመስጠት የይዞታው ባለቤት መሆኑን እንዲያምን በማድረግ ይዞታውን በ11 ሚሊየን 500 ሺ ብር ለመሸጥ በመስማማት በዳሸን ባንክ በከፈተው የሂሳብ ቁጥር በተለያዩ ቀናት የቅድመ ክፍያ ብር 5,ሚሊየን 300ሺ ይወስዳል፡፡

See also  “ከኛ ጋር ታስረው የነበሩ እስረኞች ተፈተው እኛ የምንታሰርበት ምክንያት የለም“

2ኛ ተከሳሽም ይዞታው በይዞታው ትክክለኛ ባለቤት በአቶ ግደይ ገ/እግዚአብሄር አማካኝነት የይዞታ ይመዝገብልኝ አገልግሎት ጥያቄ ቀርቦ ሂደቱ በእሱ እንዲከናወን ሃላፊነት ተሰጥቶት በነበረበት ወቅት ያገኘውን መረጃ አሳልፎ ለ3ኛ ተከሳሽ በመስጠትና 3ኛ ተከሳሽ ከግል ተበዳይ ወሰን ሃ/ማርያም ጋር ባደረገው ውል መሰረት ካርታው ተመዝግቦ ሲመጣ የአጠቃላይ የሽያጩን ቀሪ 6,200,000 ሺ ብር እንደሚከፈለው በተዋዋለው መሰረት የካርታውን ዝግጅት በመጨረስ የአቶ ግደይ ገ/እግዚአብሄርን ይዞታ በህገ-ወጥ መንገድ እዲሸጥ በማድረግ ለዚህም ስራው ከ3ኛ ተከሳሽ 150,000 ሺ ብር፣ ከ4ኛ ተከሳሽ 200,000 ሺ ብር በአጠቃላይ ሶስት መቶ ሃምሳ ሺ ብር ያልተገባ ጥቅም የተቀበለ በመሆኑ፣ተከሳሾች እርስ በእርስ በመመሳጠር በፈጸሙት በስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን የዐቃቤ ህግ አንደኛ ክስ ያመላክታል ፡፡

2ኛ ክስ በ3ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ ሲሆን ተከሳሽ ከላይ በ1ኛ ክስ በዝርዝር በተገለጸው አግባብ የተዘጋጁትን ሀሰተኛ ሰነዶች ተጠቅሞ ተበዳይም ይህንኑ ካርታ ኮፒ ይዞ ወደ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት በመሄድ የይዞታውን ማህደር አስወጥቶ ሲመለከት ተከሳሹ አስቀድሞ ለግዜው ማንነቱ ባልተረጋጠ የጽ/ቤቱ ሰራተኛ አማካኝነት ትክክለኛውን ካርታ በማስወጣት እና በሃሰት የተዘጋጀውን ካርታ ማህደሩ ውስጥ እንዲገባ በማድረጉ የግል ተበዳዩ ተከሳሹ የይዞታው ባለቤት መሆኑን እንዲያምን በማድረግ ወንጀሉን በመፈጸሙ በሃሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶች መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡

ዐቃቤ ህግ በ3ኛ ክሱ ላይም 3ኛ፣4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን 3ኛ ተከሳሽ ከላይ በ1ኛ ክስ ላይ በዝርዝር በተገለፀው አግባብ በህገ-ወጥ መንገድ በተፈጸመው የቤት ሽያጭ ውል ከግል ተበዳይ ወሰን ሃ/ማርያም የተቀበለውን የቅድሚያ ክፍያ ብር ህገ-ወጥ ምንጭን ለመደበቅ እና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ገንዘቡን ወደ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች እንዲሁም ደጀኔ ተመስገን ለተባለ ግለሰብ የባንክ ሂሳብ ያስተላለፈ በመሆኑ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾችም ገንዘቡ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ የባንክ ሂሳባቸውን ለ3ኛ ተከሳሽ አሳልፈው በመስጠት በፈጸሙት በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

See also  ኢሳት ቴሌቪዥን የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

የዐቃቤ ህግ የ4ኛ ክስን በተመለከተም ክሱ 3ተኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ ሲሆን ተከሳሽ ትክክለኛ ስሙ አድማሱ ሙላቱ ፈቄ ሆኖ ሳለ ለወንጀል አፈጻጸሙ ያመቸው ዘንድ በሌላ መጠሪያ ስም ሀሰተኛ መታወቂያ በማውጣት ማንነቱን ለመደበቅ እና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ በህገ-ወጥ መንገድ እውነተኛ ስሙን የለወጠ በመሆኑ ያለፍቃድ ስምን መለወጥ ወይም በሌላ ስም መጠራት የደንብ መተላለፍ ወንጀል ተከሷል፡፡

ጉዳዩን የሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሙስና ወንጀል ችሎትም ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመስማት ከሌላቸው ደግሞ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ለመቀበል ለታህሳስ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ይህ ዘገባ በተከሳሾች ስለመከሰሳቸው የሚገልጽ መረጃ ነው፤

ተከሳሾች ከፍርድ በፊት እንደንጹህ የመገመት ህገ-መንግስታዊ መብት አላቸው

ፍትህ ሚኒስቴር

Leave a Reply