በኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ላይ በተፈጸመ ስርቆት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ

ወንጀለኞች ላይ የፍትህ አካላት የሚጥሉት አስተማሪ ያልሆነ ቅጣት እና ግብዓት ለማግኘት ሲሉ ስርቆቱን የሚደግፉና የሚረከቡ የብረታብረት ፋብሪካዎችና ባለሀብቶች ድርጊት ሊፈተሸ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ላይ በተፈጸመ ስርቆት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳጋጠመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ

በ2014 ዓ.ም ብቻ ከኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ላይ በተሰረቀ 756 ቶን ብረት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳጋጠመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በተቋሙ የምስራቅ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንደገለጹት፥ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሚያስተዳድራቸው የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ ተደጋጋሚ ስርቆት እየተፈፀመ ነው።

በ2014 ዓ.ም ብቻ 24 የሚደርሱ ከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ የብረት ማማዎች ሙሉ ለሙሉ ተቆርጠው የወደቁ ሲሆን የብረትና የኮንዳክተር ዘረፋ እንደተፈጸመባቸው እና በቁጥር 30 ሺህ 257 የሚሆኑ የተለያዩ የታወር ብረቶች ደግሞ በቁማቸው ካሉ ማማዎች ተፈትተው መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

ከወደቁትና በቁማቸው ከተዘረፉት ማማዎች 756 ቶን ብረት መሰረቁን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም በገንዘብ ሲሰላ 72 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ኪሳራ መድረሱንና የተሰረቀውን ብረት መልሶ ለመተካት ተቋሙ 23 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ማውጣቱን አስታውቀዋል።

በ2014 ዓ.ም በስርቆት፣ በመልሶ ግንባታና ከአገልግሎት መቋረጥ ጋር ተያይዞ የባከነውን 2 ሺህ 396 ሜጋ ዋት ሰዓት ኃይል ጨምሮ ተቋሙ ከ100 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ኪሳራ እንዳጋጠመው ተናግረዋል።

የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው ስርቆትን ለመከላከል ከህብረተሰብ ተወካዮች፣ ከጸጥታ እና ከፍትህ አካላት ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች መካሄዳቸውንና ይህም ውጤት እያስገኘ መምጣቱን ተናግረዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች በህብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት ትብብር ወንጀሉን ለመከላከል ቢሞከርም በሌሎች አካባቢዎች አሁንም ችግሩ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተከሰው በሚቀርቡ ወንጀለኞች ላይ የፍትህ አካላት የሚጥሉት አስተማሪ ያልሆነ ቅጣት እና ግብዓት ለማግኘት ሲሉ ስርቆቱን የሚደግፉና የሚረከቡ የብረታብረት ፋብሪካዎችና ባለሀብቶች ድርጊት ሊፈተሸ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

(ኢ.ፕ.ድ)

See also  ትንሽ ብቻ ጠብቅ‼

Leave a Reply