ኢትዮጵያ ምርታቸውን ወደ ቻይና ከቀረጥ እና ከኮታ ነጻ እንዲያስገቡ የገበያ ዕድል ከተፈቀደላቸው አገራት መካከል አንዷ መሆኗን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

የቻይና መንግሥት አብዛኞቹ ከአፍሪካ ከሆኑ አገራት ጋር ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከር በሚል ባቀደው መርሃ ግብር መሠረት ነው ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ምርቶች ያለ ቀረጥ እንዲገቡ የፈቀደው።

ኢትዮጵያ በዚህ ነጻ ዕድል ለመጠቀም የሚያስፈልጉትን መረጃዎችን በወቅቱ ሳታሟላ በመቅረቷ በመርሃ ግብሩ ውስጥ ሳትካተት ቀርታለች ተብሎ ነበር።

ነገር ግን በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር ቁምነገር እውነቱ፣ የኢትዮጵያ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና እንዲገቡ መፍቀዱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ቻይና ከ1600 በላይ የኢትዮጵያ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ ወደ አገሯ እንዲገቡ መፍቀዷን ገልጸዋል።

ይህም አሐዝ በአጠቃላይ የንግድ ልውውጥ ከሚደረግባቸው 6,422 ምርቶች መካከል 1,644ቱን ምርቶች ከቀረጥ እና ከኮታ ነጻ ማስገባት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዳለው ይህ የገበያ ዕድል ከቻይና በኩል ብቻ የተሠጠ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዚህ ዕድል ተጠቃሚ ስትሆን የሚጠበቅባት ምንም ዓይነት ግዴታ የለም።

ከዚህ ቀደም ቻይና 10 አገራት ከቀረጥ ነጻ ወደ አገሯ ምርቶች እንዲያስገቡ ዕድል ስትሰጥ ኢትዮጵያ በዝርዝሩ ውስጥ አለመካተቷ ጥያቄ ሲያስነሳ እንደነበር የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ አሁን 1644 ምርቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መፈቀዱን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

“ኢትዮጵያ ብዙ ሀብትና ምርት እያላት እንዴት ልትገለል ቻለች? የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ሲነሱ ነበር። እኛም ስንጠባበቅ ነበር። አሁን 1644 ምርቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ተፈቅዷል” ሲሉ አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እነዚህን ሁሉ ምርቶች በአጠቃላይ ወደ ቻይና ትልካለች ማለት ሳይሆን “ከዝርዝሮቹ መካከል በእጇ ላይ የሚገኙትን ምርቶች” እንደምትልክ አክለዋል።

ለምሳሌ የብረታ ብረት እጥረት እያለ እንዴት ወደ ውጭ መላክ ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ እንደሆነ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፣ “ኢትዮጵያ ወደ ቻይና መላክ የምትችለው የታወቁ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ይሆናል” ብለዋል።

እነዚህም ኢትዮጵያ እስካሁን ለተለያዩ የዓለም ገበያዎች በማቅረብ የምትታወቅባቸው ከቁም እንስሳት፣ ከቅባት እህሎች እና ከግብርና ምርቶች ጋር የተያያዙ ሲሆኑ፣ በተጨማሪም በቻይና ፈቃድ ከተሰጣቸው ምርቶች ውስጥም ሌሎች ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና የሚላኩ እንደሚኖሩ ኃላፊዋ ተናግረዋል።

ቻይና ከቀረጥ ነጻ ወደ አገሯ እንዲገቡ ከፈቀደቻቸው በርካታ ዓይነት የምርቶች ዝርዝር ውስጥ አሁን ለመላክ የምትችላቸውን በቀዳሚነት የምታቀርብ መሆኑም ተገልጿል።

ነገር ግን በሂደት ለኢትዮጵያ ከተፈቀዱት ምርቶች ውስጥ በስፋት አምርታ ለገበያ ማቅረብ ከቻለች የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለማስገባት ዕድል እንዳላት ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።

“በዚህም ወደ ውጭ ምርቶችን በላክን ቁጥር እኛም ከቻይና ምርት የማስገባታችን ዕድል ሰፊ ይሆናል” ሲሉ በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚያመጣውን አዎንታዊ ተጽዕኖ ተናግረዋል።

ይህ ፈቃድ ከተሰጠበት ዕለት አንስቶ በቀረጥ ነጻ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ምርቶችን መላክ እንደሚቻልም አያይዘው ገልጸዋል።

ቻይና ይህንን ነጻ የንግድ ዕድል እንዲጠቀሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአስር አገራት ነው በአሁኑ ጊዜ ፈቃድ የሰጠችው።

ቀደም ሲል ለረዥም ጊዜ የቆየ ተመሳሳይ ዕድልን አሜሪካ አጎዋ በሚል ስያሜ ኢትዮጵያም ለተካተተችባቸው በማደግ ላይ ላሉ አገራት ሰጥታ ምርቶችን ከቀረጥና ከታሪፍ ነጻ እያስገቡ ይገኛሉ።

ነገር ግን ኢትዮጵያ በትግራይ ውስጥ ሲካሄድ ከነበረው ጦርነት ጋር በተያያዘ ከዚህ የነጻ ንግድ ዕድል ካለፈው ዓመት ጥር ጀምሮ መታገዷ ይታወሳል። BBC AMHARIC

Leave a Reply