ፌስቡክ በኢትዮጵያ ግጭት በማነሳሳት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ክስ ተመሠረተበት

መጠሪያውን ወደ ሜታ የቀየረው ግዙፉ ማሕበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት በማነሳሳት ክስ ተመሠረተበት።

በሰሜኑ ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ፌስቡክ በገጹ ጥላቻ የሚነዙ እና ግጭት የሚያነሳሱ መልዕክቶችን አሰራጭቷል ተብሎ ነው ክስ የተመሠረተበት።

ሜታን ከከሰሱት መካከል አባቱ ፌስቡክ ላይ በተለጠፈ ጽሑፍ ምክንያት የተገደለበት አብርሃም ማዕረግ አንዱ ነው። በፌስቡክ ጽሑፍ ምክንያት አባቱ ጥቃት ደርሶበታል፣ በጥይትም ተገድሏል።

ከሳሾቹ በፌስቡክ ላይ ከተሰራጨው ጥላቻ ጋር በተያያዘ ለደረሰባቸው ጉዳት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲሁም የፌስቡክ አልጎሪዝም ላይ ለውጥ እንዲደረግም ይሻሉ።

ሜታ በበኩሉ በገጹ የሚንሸራሸሩ መልዕክቶችን ለማጥራትና ጥላቻ አዘል የሆኑትን ለማስወገድ በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት እንዳደረገ ይናገራል። የሜታ ወኪል እንዳሉት፣ የጥላቻ ንግግር እና ግጭት አነሳሽ መልዕክቶች ከገጹ መርህ ጋር ይጣረሳሉ። ክሱ የተመሠረተው በኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። ፎክስግሎቭ የተባለ የመብት አቀንቃኝ ቡድንም ይደግፈዋል። ሜታ በኬንያ፣ ናይሮቢ ይዘት የሚፈትሽ ቡድን አለው።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ረሃብ በሚመስል ሀኔታ ውስጥ እንደገቡ ሲነገር ቆይቷል። BBC AMHARIC

See also  ኦሮሚያ ለአማራ ክልል መቶ ሚሊዮን ብር ሰጠ፤ "ኑ የወደመውን የትውልድ ማረፊያ ተቋም አብረን እንገንባ"ዘመቻ በይፋ ተጀመረ

Leave a Reply