ባይደን አፍሪካውያንን የዲጅታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግ አዲስ እቅድ ይፋ አደረጉ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በአፍሪካ ዜጎች የዲጅታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የ350 ሚሊዮን ዶላር እቅድ ይፋ አደረጉ። የአሜሪካ አፍሪካ መሪዎች የቢዝነስ ፎረም በዋሽንግተን ዲሲ ትናንት ተካሂዷል።

የአሜሪካ አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በሁለተኛ ቀን ውሎው በቢዝነስ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መክሯል በመድረኩ የተገኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባደረጉት ንግግር፤ አገራቸው በአፍሪካ አህጉር የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲመጣ በቀጣይ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በእቅድ ይዛለች ብለዋል።

ከዚህ ቀደም አሜሪካ በአፍሪካ አህጉር በመሰረተ ልማትና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ያላትን ተሳትፎ የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፤ ይህ ጉባኤ በቀጣይ አሜሪካና አፍሪካ ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚረዳ እንደሆነም አንስተዋል።

በመድረኩ ፕሬዚዳንት ባይደን በአፍሪካ ይተገበራል ያሉትን አዲስ እቅድ ይፋ አድርገዋል። ይህ እቅድ የዲጅታል ሽግግር ከአፍሪካ ጋር የተሰኘ ሲሆን 350 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚደረግበት ይሆናል ብለዋል።
እቅዱ በዋናነት አፍሪካውያን በዲጅታል ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲሳተፉ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ማይክሮሶፍትና ቪያሳት የተሰኙ የኢንተርኔት አቅራቢ ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን አምስት ሚሊዮን አፍሪካውያን የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላልም ብለዋል።

ጆ ባይደን የሚመሩት አስተዳደር ባለፉት ሁለት ዓመታት ከመጣ ወዲህ በአፍሪካ ከሚገኙ በርካታ ሀገራት ጋር ያለው የኢኮኖሚ ትብብር ማደጉን አንስተዋል። ይህ ግንኙነት በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት አሜሪካ አዲስ የተመሰረተውን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እድልን ለመጠቀም ትልቅ ስምምነት ማድረጓን አብስረው፤ ይህ ስምምነት በርካታ የአሜሪካ ድርጅቶች እድሉን ተጠቅመው በቀጠናው ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ትልቅ እድል ነው፤ እድሉም ለአፍሪካ መጻኢ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ወደ ተግባር እንዲቀየርም አሜሪካ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል። ይህም በተለይ አፍሪካና አሜሪካ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናክር የሚያደርግ ነው ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አሜሪካ በአፍሪካ ቀጠናዊ ንግድ እንዲስፋፋ ጥረት እያደረገች ስለመሆኑ ያነሱት ፕሬዚዳንት ባይደን፤ በተለይ ለንግድ ስራ አመቺነት የሚረዳ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሀገራቸው ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን አንስተዋል።

See also  ኢትዮጵያ የ24 ስዓት መረጃ – 3

የእርሳቸው አስተዳደር ከመጣ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ሚሊኒየም ቻሌንጅ ኮርፖሬሽን በተሰኘ ድርጅት አማካኝነት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በአፍሪካ ሀገራት ማስተዋወቁን አንስተዋል። ይህ ኮርፖሬሽን በቀጣይ ዓመታትም በአፍሪካ ተጨማሪ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ እንደሚያደርግ ይጠበቃል ብለዋል።

በተጨማሪ አሜሪካ በአፍሪካ አህጉር ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ለውጦች እንዲመጡ በኢኖቬሽንና ስራ እድል ፈጠራ ላይ የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች ያሉት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፤ አገራቸው በአፍሪካና በአፍሪካውያን ላይ የምታደርገው ኢንቨስትመንት አይቋረጥምም ብለዋል።

በቢዝነስ ፎረሙ ላይ 300 በዘርፉ የሚገኙ የአፍሪካና አሜሪካ የቢዝነስ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነትም አድርገዋል።

ጀማል ታመነ (ዋሽንግተን)
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7 /2015

Leave a Reply