አዲስ አበባን የኦሮሞና የአማራ ጉዳይ ብቻ እየተደረገ የሚቀርብበት መንገድ ፈፅሞ መቆም አለበት። አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ናት። ኗሪዎቿ ደግሞ ቁጥራቸው ይለያይ እንጅ ከሁሉም ብሔሮች የመጡና የሚኖሩባት የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መዲና የሆነች ከተማ ናት። በአዲስ አበባ ውስጥ አይን ያወጣ የሚጎረብጥ ነገር ካለ ምቾት የሚነሳው አማራውን ብቻ ሳይሆን ሶማሌውን ትግሬውን ጉራጌውን ወላይታውን አፋሩን ሲዳማውን …ጭምር ነው።
በወያኔ mindset በሚያስቡ ዘመኑን መዋጀት ባልቻሉ በመዋቅር ውስጥ ባሉ አንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን አሻጥር ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚጎረብጥ ከፍላጎታቸው ውጭ የሚጫን ነገር ካለ ሊቃወም የሚገባው ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪ (ሁሉም ብሔር) እንጅ በማንነቱ አማራ ነኝ የሚለው የአዲስ አበባ ነዋሪ ብቻ ሊሆን አይገባውም። በተመሳሳይ በመዋቅር ውስጥ ባሉ በአማራ ወይም በጉራጌ ወይም በሲዳማ ሶማሌ… ልሂቃን በሚሰራ አሻጥር ለአዲስ አበባ ነዋሪ የሚጎረብጥ ከፍላጎቱ ውጭ የሚጫን አላስፈላጊ እንቅስቃሴ ሲኖርም እንዲሁ ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪ ይመለከተዋልና መቃወም ይኖርበታል።

የአዲስ አበባ ጉዳይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ የሶማሌ የጉራጌ የሲዳማ የጋሞ የከንባታ የጋምቤላ ወይም የሽናሻ …የሁሉም ጉዳይ እንጅ በአዲስ አበባ የሚኖር የአማራና የኦሮሞ ጉዳይ ብቻ እየተደረገ የሚቆጠርና በአማራ ስም ተለጥፎ የራስን ጥያቄና ፍላጎት የሚያራምዱበት እንቅስቃሴ ሊሆን አይገባውም።
በአማርኛ ቋንቋ በአማራ ስም በመጠለል በየሚዲያው በአዲስ አበባ የሚጎረብጥን ጉዳይ የአማራ ጉዳይ ብቻ በሚያስመስል የሚደረገው የዘመቻ አካሄድ ከእውነት የተፋታ ለማንም የማይጠቅም አካሄድ ስለሆነ መስተካከልና መቆም ያለበትም ነው። የሁሉም ጉዳይ የሆነን አጀንዳ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሁለት ብሔሮች ጉዳይ አስመስሎ መንቀሳቀስም የወያኔን እኩይ አላማን ለማሳካት ከሚንቀሳቀሱት የተለየ አይደለም። የትግሬም ሆነ የጉራጌ ወይም የወላይታ የሶማሌ…. ልሂቃን አዲስ አበባ ላይ የሚያነሱትን ጥያቄና ፍላጎት በአማራ ስም በኩል ለማስፈፀም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለአማራ ከመቆርቆር የመነጬ ተገቢነት ያለው ጉዳይ አይደለም። አዲስ አበባ ላይ ያለን የራስን ጥያቄና ፍላጎት በአማራ ስም በሚደረግ ጩኸት ለማሳካት የሚደረግ ሙከራም ነው። ለራስ ጥያቄና ፍላጎት ራስን ችሎ በግልፅ ለመታገል ከመቆም ይልቅ በብልጣብልጥነት በአማራ ስም ተለጥፎ የራስን አላማ ለማሳካት የሚደረገው እንቅስቃሴም የትም የማያደርስ መሆኑም መታወቅ አለበት። በአማራና በኦሮሞ መካከል በአንደኛው ጎን በመሰለፍ ቤንዚን አርከፍክፎ የራስን ጥቅም የማስከበር የብልጣብልጥነት እንቅስቃሴም እንዲሁ ብዙ ርቀት የማይወስድ የሞኝ ስሌትም ነው።ብዙ ርቀት የማይወስድ ብቻ ሳይሆን የታሰበው እሳት ቢቀጣጠል በመሃል የሚተርፍ ብልጥ ነኝ ባይም እንደማይኖር መታወቅ አለበት። በአማራ ስም ከሚንቀሳቀሰው የወያኔ ጉዳይ አስፈፃሚ ጋር በዚህ አጀንዳ ዙሪያ አብሮ መቆምም በራሱ ጠላትነት ነው።

አዲስ አበባ ላይ የሐብትና ንብረት ክፍፍል ይደረግ እንኳን ቢባል በማልማቱ ሂደት እኔም አለሁበት ይህ ያ ይደርሰኛል አለኝ እያለ ማመልከቻ የማያስገባ የብሔር ልሂቅም አይኖርም።

Tomas jajaw

Leave a Reply