«አፍሪካ የአሜሪካ ድጋፍ አይለያትም»

አፍሪካ ከእርዳታ ተላቃ በአዳዲስ ሃሳቦችና ፈጠራዎች ላይ ተመስርታ ለማደግ በምታደርገው ጥረት አሜሪካ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሴክሬታሪ አንቶኒ ብሊንከን ገለጹ።

ሴክሬታሪ አንቶኒ ብሊንክን ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ የፈጠራ ባለሙያዎች መድረክ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ አፍሪካ የልጆቿን የፈጠራ አቅም ተጠቅማ ለመበልጸግ በምታደርገው ጉዞ የአሜሪካ ድጋፍ አይለያትም።

አፍሪካ በአሁኑ ጊዜ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝቧ ከሃያ አምስት ዓመት እድሜ ያነሰ ነው፤ ይህ ደግሞ ለማደግ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው። በአፍሪካ እያደገ የመጣው የሕዝብ ቁጥር ለአህጉሪቷ ብሎም በቀሪው ዓለም የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበርክት እምነታቸው መሆኑን ብሊንከን በንግግራቸው አንስተዋል።

በ2016 እ.ኤ.አ በአፍሪካ የሚገኙ የቢዝነስ ፈጠራ ሃሳብ አመንጪዎች ከ350 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ የኢንቨስትመንት እድገት እንዳስመዘገቡ አንስተው፤ ይህ ቁጥር ባለፈው ዓመት አድጎ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ገቢ እንዲመዘገብ ማስቻላቸውንም አንስተዋል።

አፍሪካ ያላትን የወጣቶች ሀብት ተጠቅማ እንድትበለጽግ አሜሪካ የምታደርገውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ያሉት ሴክሪታሪ ብሊንከን፤ አሜሪካ ይህን የምታደርገው አፍሪካውያን የቢዝነስ ፈጠራ ባለሙያዎች ከአህጉሪቱ ባለፈ ለአሜሪካ ብሎም ለመላው ዓለም የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ብለዋል።

‹‹አፍሪካ እርዳታ ሳይሆን ፈጠራን ትሻለች›› ይህ እንዲሳካ አሜሪካ በአፍሪካ የፈጠራ ሃሳቦች እንዲያድጉ በሶስት መንገዶች ድጋፍ እንደምታደርግ አንስተዋል።

አሜሪካ በአፍሪካ ለሚከናወኑ የፈጠራ ስራዎች እንዲጠናከሩ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ ታደርጋለች፣ ወጣት መሪዎች አቅማቸው እንዲጎለብት የሚያስችል ተግባራትን ታከናውናለች እንዲሁም አሜሪካውያን ካምፓኒዎች በአፍሪካ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ የሀገሪቱ መንግሥት ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

በአፍሪካውያን የቢዝነስ ፈጠራ ሃሳብ ባላቸው ዜጎች የተመረቱ ምርቶች በአሜሪካ ገበያ እየቀረቡ መሆኑን የገለጹት ሴክሬታሪ ብሊንከን፤ ይህ ተጠናክሮ እንደሚጥልም አስረድተዋል።

በአሜሪካ ዋሽንግተን ትናንት በጀመረው የአሜሪካ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ የተለያዩ የጎንዮሽ ውይይቶች ተካሂደውበታል።

የአፍሪካውያንና ዲያስፖራ ወጣት መሪዎች ፎረም፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም፣ የአፍሪካ ከቀረጥ ነጻ የንግድ ሚኒስትሮች ሰብሰባ፣ የአሜሪካ አፍሪካ ስፔስ ፎረም፣ ሰላም፣ ደህንነትና አስተዳደር ፎረም፣ ቀጣይነት ያለው የጤና ትብብር ፎረም እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረት ያደረጉ ውይይቶች ተካሂደዋል።

See also  የላሊበላ ሰላም የነዋሪዎቿ የልብ ትርታ - ከንቲባ ዲያቆን ተፋራ ሰይፉ

በመድረኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እየተሳተፉ ነው።

ጉባዔው በሁለተኛ ቀን ውሎው በአሜሪካና አፍሪካ የቢዝነስና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚመክር ይሆናል።

ጀማል ታመነ (ዋሽንግተን)

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6 /2015

Leave a Reply