የፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ መነሻ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን ገለጸ

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሪሲ ጃክኦፍሰንና የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ፍቃዱ ጸጋ በሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ጽ/ቤት በኩል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ወንጀሎችን መርምሮ ተጠያቂነትን ከማስፈን አንጻር እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ዙሪያ ተወያዩ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ደዔታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሪሲ ጃክኦፍሰን የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ጽ/ቤት ከሰብአዊ መብት ጥሰት፤ ወንጀሎችን መርምሮ አጥፊዎችን ተጠያቂ ከማድረግ አንፃር እየተከናወኑ ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ደዔታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ አምባሳደሯን ተቀብለው ያነጋገሩት በጽ/ቤታቸው ሲሆን በወይይቱ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በውይይት መድረኩም የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ደዔታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ የፍትሕ ሚኒስቴርን ተግባር እና ኃላፊነት አስመልክተው ለአምባሳደሯ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን መንግስት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት የተሰጡ ምክረ ሀሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ በማሰብ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለማጣራትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ብሎም ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋምና ለመደገፍ የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ጽ/ቤት እንዲቋቋም ማድረጉን በመጥቀስ ሚኒስቴር መስርያ ቤቱም ግብረ-ኃይሉን እንዲመራና እንዲያስተባብር ኃላፊት ተጥሎበት የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል፡፡

በግብረ-ኃይሉ ጽ/ቤት ስር የተቋቋመው እና የወንጀል የምርመራና ጥፋተኞችን ተጠያቂ የሚያደርገው ኮሚቴ በፍትሕ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአፋርና ከአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች የተውጣጣ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ፣ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በአፋርና አማራ ክልሎች በግጭቱ ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን የመመርመር ስራ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተው በተያዘው የታህሳስ ወር መጨረሻ የምርመራ ሥራው እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት ጥምር የምርመራ ቡድን የሽግግር ፍትህ አማራጭን ማጤን እና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ በሰጡት ምክረ-ሀሳብ መሰረት፤ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ መነሻ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡

See also  ቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናን ኢትዮጵያ አንደኛ

ሚኒስቴር ዴኤታው አክለውም አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደ ያለዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ፣ የምርመራ ሥራው አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ ለማድረግ ለምርመራ ቡድኑ አባላት ስልጠናዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ የምታደርገውን የሥራ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደንቁ ተናግረው ከሎጀስቲክስና ሰልጠና ጋር ተያይዞ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር ትሪሲ ጃክኦፍሰን በበኩላቸው አሜሪካና ኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ የተጠናከረና የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው በመጥቀስ የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ጽ/ቤትም የተቋቋመበትን ዓላማ ግብ እንዲመታና የጀመረዉን የሰብአዊ መብት ጥስት ወንጀል ምርመራ በፍጥነት በማጠናቀቅ አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ እንዲሁም ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋምና ለመደገፍ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀው፤ ከወንጀል ፍትህ ስርዓቱ ጋር በተያያዘም በአሜሪካ መንግስት በኩልም የሚደረገው ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው የወንጀል ምርመራ ሥራዉን ለመደገፍ 31 ታብሌቶችን ያበረከቱ ሲሆን በተጨማሪም ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችን በድጋፍ መልክ ለመስጠት በግዥ ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪ አምባሳደሯ የሽግግር ፍትህ አማራጭን ማጤን እና ተግባራዊ ማድረግ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን በመገለጽ በተለይም የአሜሪካ መንግስት ሰብዓዊ መብትን ከማረጋገጥ አንፃር ከሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ጋር ከምንጊዜውም በበልጠ በጋር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

Leave a Reply